ኢራን በምትገኝበት ቀጣና ውስጥ የተካሄደው "የመጀመሪያው ጦርነት" ምን መልክ ነበረው?

የንባብ ጊዜ: 8 ደቂቃ

መካከለኛው ምሥራቅ ለጦርነት አዲስ አይደለም።

ጦርነት የተወለደው ከሥልጣኔ ጋር ተይይዞ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጦርነትም ሜሶፖታሚያን እና አካባቢውን በሚያጠቃልለው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የተካሄደ ነበር።

ሰዎች የግብርና እና የእንስሳት እርባታ ቴክኒኮችን መማር የጀመሩትም በዚሁ አካባቢ ነበር። ይህ ደግሞ ከተሞች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነውን የአኗኗር ዘይቤ አስተዋውቋል።

በጠንካራ የሰው ኃይል መደራጀት፣ መከላከያን ማጠናከር እና የተሻለ የውሃ አቀርቦትን በመያዝ የበለጠ ሃብት እና መሬት ማግኘት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጣ።

የብሪታንያው የታሪክ ፀሐፊ ጆን ባይንስ ባደረጉት ጥናት መሠረት፣ ዛሬ ኢራቅን እና ኢራንን ባሉበት ቀጣና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3000 ዓመት ገደማ በከተሞች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች እንደነበሩ የሚያሳይ ማስረጃ አለ።

"ጦርነት ለምን ዓላማ?" በተሰኘው መጽሐፋቸው የሚታወቁት የብሪታንያው ታሪክ ፀሐፊ እና አርኪዮሎጂስት ኢያን ሞሪስም የመጀመሪያዎቹ በአነስተኛ መጠን የተደራጁ ጦርነቶች የተከሰቱት በተመሳሳይ ጊዜ እና ክልል እንደሆነ ይገልጻሉ።

ሌላኛው የብሪታኒያ የታሪክ ፀሐፊ ጆን ኪገን "የጦርነት ታሪክ" በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፣ "የጦርነት ታሪክ የሚጀምረው ከጽሑፍ ነው።"

"'ታሪክ' የሚጀምረው የሰው ልጅ መጻፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወይም አሻራውን አስቀምጦ ካለፈበት ጊዜ ጀምሮ ነው።"

በተቀመጡት መለኪያዎች መሠረት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ጦርነት እንደሆነ የሚታሰቡ ጦርነቶችን የጻፉት ሱሜሪያውያን ነበሩ።

ሱመር በመዳብ ዘመን እና በነሐስ ዘመን መካከል ማለትም ከክርስቶስ ልደት በፊት 3300 እና 1200 መካከል በሜሶፖታሚያ ደቡባዊ ክልል የተስፋፋ ሥልጣኔ ነበር።

ለ250 ዓመታት ያህል ማለትም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2600 እስከ 2350 መካከል የላጋሽ እና የኡማ ግዛት ሕዝቦች ጦርነት ያካሂዱ ነበር። ጦርነቱን የሚገልጽ የጽሑፍ መዝገብ አለ።

በአጠቃላይ 18 ጽሑፎች ያሉ ሲሆን፣ ሁሉም በላጋሽ ገዢዎች በሸክላ ገጾች ላይ እንዲቀረጹ የተደረጉ ናቸው።

የኡማ-ላጋሽ ግጭት በሁለት ግዛቶች መካከል የተደረገ የተደራጀ እና ስልታዊ ጦርነት እንደነበር በሰነድ ማስረጃዎች ላይ ተቀምጧል።

በሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ካትያ ፖዘር የመጀመሪያውን ጦርነት ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ አይቻልም ብለዋል።

"ጦርነት በሜሶፖታሚያ ዓለም ውስጥ በሁሉም ቦታ የሚገኝ እውነታ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ሰነዶች አሉ" ሲሉ አክለዋል።

"በሜሶፖታሚያውያን አስተሳሰብ ጦርነትን እንዴት መምራት እንደሚቻል ማወቅ የሰለጠነው ዓለም አንደኛው ባህሪ ተደርጎ ይወሰዳል።"

ወታደራዊ መዋቅር

"ከፍተኛ ፈተና፣ የፈላ ዘይት፣ ድንጋይ እና የቀስት ዝናብ ቢኖርም ሲታዘዙ ጠላትን ለመዋጋት እና ለመግደል የተዘጋጁ ወታደሮችን ያማከለ መንግሥታት ከተፈጠሩበት ጊዜ ጋር እንደሚገጣጠም" ሞሪስ ይጠቁማል።

ይህ የተከሰተው በመካከለኛው ምሥራቅ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3300 አካባቢ ነበር። ከዚያ ጊዜ በኋላ ግጭቶች በጦር ሜዳ፣ በታቀዱ ወረራዎች እና በከበባዎች መፈታት ጀመሩ።

ላጋሽ እና ኡማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ይራራቃሉ። ግጭቱም በድንበራቸው ላይ የሚገኘውን ጉዴና የተሰኘውን ለም ቦታ ለመቆጣጠር የተደረገ ነው።

ኡማ ያንን መሬት ሲይዝ ለላጋሽ የሚያቀርበውን የውሃ ፍሰት መቆጣጠር ቻለ።

ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታትም ሙከራ ተደርጓል። ይህንንም በደቡባዊ ሜሶፖታሚያ ሥልጣን በያዙት ንጉሥ በኩል ነው የተካሄደው። ላጋሽን ደግፈው ቆሙ።የኡማ ገዢ ፈቃድ ሳይኖር የተሰጠው የንጉሣዊው ፈቃድ ለጦርነቱ በምክንያትነት ቀርቧል።

"ወደ ጦርነት የተሸጋገረ የድንበር ግጭት ነበር" ሲሉ ደራሲ እና ጋዜጠኛው ሬይናልዶ ሆሴ ሎፔስ ገልጸውታል።

"ምክንያቶቹ በዋናነት የድንበር እና የኢኮኖሚ ነበሩ። በተለይም ለእርሻ የሚሆን የውሃ ቁጥጥር ላይ የተመሠረቱ አለመግባባቶች ናቸው" ሲሉ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ጉንተር ሩዚት ያስረዳሉ።

"የተገኘው ውጤት ደግሞ የላጋሽ ድል ሲሆን፤ ግብር መክፈል እና የድንበር ማካለልን ጨምሮ በኡማ ላይ ግዴታ እንዲጣል ምክንያት ሆኗል።"

አካባቢው ግን ሠላም አልሆነም። ቀስ በቀስ ግጭቱ ወደ ሌሎች የአካባቢው ሕዝቦች ተስፋፋ። አሁን ኢራን በምትባለው ግዛት ውስጥ የሚገኘው የሃማዚ መንግሥት እና በክልሉ ትልቅ ጉልበት የነበረው የኡሩክ መንግሥት ወታደሮች ተስበው ወደ ግጭቱ ገቡ።

በእነዚህ ተከታታይ ውጊያዎች የኡማ ንጉሥ ሉጋልዛጌሲ አሸንፈው በኋላም መላውን ሜሶፖታሚያን ጠቅልለው ያዙ። በኋላ ላይ ግን በአካድ ንጉሥ ሳርጎን ተሸነፉ። ኡማ እና ላጋሽንም በቁጥጥራቸው ስር አስገቡ።

"ግዛቱን በወታደራዊ መንገድ ለማስፋት በማሰብ ትልቅ ጦርነት የከፈተው የመጀመሪያው ሰው ነበር። በበርካታ የከተማ ግዛቶች የተገነባ ሰፊ ግዛት ላይ የፖለቲካ የበላይነትን መገንባትን ጀምረዋል" ሲል ፖዘር አስረድተዋል።

ታላቁ ሳርጎን በመባል የሚታወቀው ንጉሥ በጣም ኃይለኛ ስለነበረ 5,400 ሠራዊት እንደነበራቸው ሞሪስ ጠቁመዋል።

"ወታደሮቻቸው ሙሉ ጊዜ እንዲሰለጥኑ ምግብ፣ ሱፍ እና የጦር መሳሪያዎች አቅርበውላቸዋል" ብለዋል አርኪዮሎጂስቱ።

ለጦርነት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች

የዓለም ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ጨምሮ በላጋሽ እና ኡማ መካከል እስከተካሄደው ስልታዊ ግጭት ድረስ ጦርነቶች ብዙም የተለመዱ እንዳልነበሩ ኪገን ያምናሉ።

ምንም እንኳን የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ5 እስከ 10 ሚሊዮን መካከል ከነበረበት ወደ 100 ሚሊዮን ቢያድግም በጣም ጥቂት ቦታዎች ላይ ነበር ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት የነበረው።

"አዳኞች ለመኖር በአንድ ሰው ከ2.5 እስከ 10 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚደርስ ክልል ያስፈልጋቸው ነበር። ገበሬዎች እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በጣም በትንንሽ አካባቢዎች መደገፍ ይችላሉ" ሲሉ ጽፈዋል።

"በእነዚያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የመዋጋት አስፈላጊነት እምብዛም ነበር። መሬቱ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን በእግር ተጉዞ ማረስ ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው ነፃ ነበር ማለት ይቻላል" ሲሉ ኪገን ይገልጻሉ።

ምርት በጣም ዝቅተኛ ስለነበር "ከመኽር በኋላ" ካልሆነ በስተቀር ዝርፊያን የማደራጀት ሁኔታም ብዙም አልነበረም ሲሉ አክለዋል።

በትራንስፖርት ረገድም ሁኔታዎች አልተመቻቹም። ይህም ሃሳቡን ውጤታማ አያደርገውም።

ይህንን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በለምነቱ የሚታወቀው የፈርታይል ክረሰንት ክልል ለጦርነቱ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶችን በተሻለ ሁኔታ ያጣመረው እንደሆነ ያምናሉ።

"የሰው ልጅ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአውሮፓ እርሻ በሚስፋፋበት እንዲሁም በሰው ያልተያዙ ቦታዎች በሚወረሩበት ወቅት ከፍተኛ ትርፍ የሚያመርተው አካባቢ ነበር" ሲሉ አስቀምጠዋል።

ይህ የጢግሮስ እና የኤፍራጥስ ወንዞች ሜዳማ አካባቢ ነበር። በጥንታዊ የታሪክ ምሁራንም ሱሜሪያ በመባል ይታወቃል።

በማኬንዚ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት የታሪክ ምሁሩ ቪክቶር ሚሲያቶ በዚህ ቀጣና ውስጥ መረጋጋትን የማስፈን ውስብስብነት ይኖራል ብለዋል። "የውሃ እና የመሬት ከፍተኛ ፍላጎት ያለበት እና የተለያዩ ሕዝቦችን እና ጎሳዎችን የያዘ ቀጣና ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

"እኛ የጦርነትን ባህሪ እና 'የሰለጠነ' ጦርነት ባህሪያትን ማስተዋል የምንችልበት የመጀመሪያው አስተማማኝ ማስረጃ ማግኘት የጀመርነው ከሱመሪያውያን ነው" ሲሉ ኪጋን ይደመድማሉ።

በአንድ ሌሊት የዳበረ ክህሎት አልነበረም።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ9500 ገደማ በደቡብ ምዕራብ እስያ ተራራማ አካባቢዎች ላይ ገብስ እና ስንዴ ማልማት የጀመሩት "በግልጽ ደካማ በሆነ መልኩ የተደራጁ እና በቴክኖሎጂ የላቁ ተዋጊዎች" እንደሆኑ ሞሪስ ተናግረዋል።

"አርኪዮሎጂስቶች ከመቃብሮቻቸው እና ከመንደሮቻቸው ያገኙት ነገር ሁሉ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ማኅበረሰቦች ጋር በተመሳሳይ መንገድ እንደተዋጉ ያሳያል" ይላሉ።

"በጣም ገዳይ የሆኑት የጦር መሣሪያቸው የተቀረጹ የድንጋይ ሰይፎች ነበሩ።"

እንደ ሞሪስ ገለጻ፣ እነዚህ ያለ ስልት የሚደረጉ ጦርነቶች ነበሩ። እንዳሻቸው ጥቃት ሰንዝረው ይሸሻሉ።

"ምግብ ስለሚያልቅባቸው ጥቃታቸውን ከጥቂት ቀናት በላይ ለማራዘም እምብዛም አልቻሉም" ሲል ያስረዳል።

የመደምደሚያቸውም ጦርነትን የሚወዱ ሰዎች እንዳልነበሩ ነበር። የጦርነት እንቅስቃሴያቸው የተበታተነ ነበር። የጠላት ቡድንን ለማሸነፍ ኃይላቸውን ሲያንቀሳቅሱ በጥቂት ደርዘን የሚቆጠሩ ወንዶች ብቻ ደካማ በሆነ መልኩ ያሰልፉ ነበር።

ጦርነቱ ቀኑን ሙሉ ሊቆይ ወይም በመጨለሙ፣ የምሳ ሰዓት በመድረሱ፣ አንድ ሰው ሲጎዳ ወይም ዝናብ ሲሆን በማንኛውም ምክንያት ሊቋረጥ ይችላል።

የሱሜሪያን ሕዝብ በኢራቅ ሜዳ ላይ ሲሰፍር "ዝናብ የሚያገኘውን እና ከኮረብቶች ግርጌ የሚገኘውን እንዲሁም አሁን ሶሪያ፣ ቱርክ እና ኢራን ያሉበትን አካባቢ በመተው እህል ለማብቀል እና እንስሳትን ለማርባት ሙከራ ማድረግ እንደጀመሩ" ኪገን ይገልጻሉ።

"በወንዞች መካከል ያለው የሜሶፖታሚያ መሬት ለቅኝ ግዢዎች ትልቅ ጥቅም ሰጥታለች" ሲል ተናግረዋል።

እንደተጠበቀው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3000 የሱሜሪያን ማኅበረሰቦች በከተማ ግዛቶች ተደራጅተው ነበር።

የካህናት ነገሥታት ከንብረት የተገኘ ኃይል ነበራቸው። ንብረቱ የሚገኘው ከተፈጥሮ መስኖ በተገኘ ሃብት ነው።

ምርቱ ለጊዜው አስደናቂ ነበር። ትርፍ አብቃይ አካባቢ ነበር።

የውሃ አቅርቦትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ አካባቢ ነበር። ወንዞቹ ለእርሻው ዋስትና ነበሩ። በምሥራቅ እና በሰሜን ያሉት ተራሮች ለሕዝቡ ለምለም መሸሸጊያ ሆነው አገልግለዋል።

"የዚህ አካባቢ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች ለመግለጽ ቀላል ናቸው፡ የሱሜሪያ ከተሞች ድንበሮችን፣ የውሃ መብቶችን እና የግጦሽ መሬቶችን ተከትሎ ውጥረቶችን ማስተናገድ ጀምረዋል።"

"የሱሜሪያ ነገሥታትም የራሳቸውን ከተሞች የመሠረቱ ከተራራ አካባቢዎች በመጡ ስደተኞች ሥልጣናቸው ፈተና እንደገጠመው ማሰብ ጀመሩ" ሲሉ የታሪክ ምሁር ኪገን ገልጸዋል።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3100 እስከ 2300 መካከል በሱሜሪያውያን ሕይወት ውስጥ ጦርነት ተጽዕኖ ማደግ ጀመረ።

ቀደምት የተጻፉ መዛግብት በዚህ የጦርነት ሁኔታ የተከሰቱ ለውጦች እንዳሉ ያሳያሉ። ነገሥታት ካህናት ከመሆን ይልቅ ወታደራዊ ተዋጊዎች ሆኑ። ይህም ስያሜያቸው ላይ ለውጥ ማስከተል ጀመረ።

በዚያ አውድ ውስጥ ንጉሥ የሚለው ሃሳብ ለአማልክት መሰጠትን፣ የምግብ አቅርቦትን እና የጦር ጀግንነትን ሚና የሚያካትት ሰው መሆኑን ያብራራል ብለዋል ፖዘር።

"ጦርነትን ለመጀመር [ምክንያት የሚሆነው] የበለጠ ሃብት ያላቸውን ግዛቶች መፈለግ ነበር፤ ይህም ወንዝና ለም መሬት ነው" ይላሉ ፖዘር።

በተመሳሳይ ጊዜ የሱሜሪያውያን ማኅበረሰብ የጦር ዘዴዎችን አሻሽሎ መሳሪያዎችን አዘጋጅቷል። እናም ጦርነቶች በተሻለ ሁኔታ መደራጀት ጀመሩ።

ጦርነቶቹ ምን ይመስሉ ነበር?

የታሪክ ምሁራን ጦርነቶቹን ለመግለጽ ለእነዚያ ሕዝቦች ከነበሩት የቴክኖሎጂ እድገት፤ ከተቀረጹ ጽሑፎች እና ቅርጻ ቅርጾች ጋር ​​የተገኙ የአርኪዮሎጂ መላምቶችን መሠረት በማድረግ ነው። ሌላ ምንም መረጃ የለም።

"ሠራዊቶቹ ሥርዓት፣ ድንበሮችን እና ንጉሣዊውን አስተዳደር በመጠበቅ ላይ ብቻ ​​ሳይሆን፣ የረጅም ርቀት ነጋዴዎችንም እንደ ማጀብ ያሉ አስፈላጊ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም የተዋቀሩ ነበሩ" ይላሉ ፖዘር።

በሪዮ ዴ ጄኔሮ ፌዴራል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት የታሪክ ምሁሩ አንድሬ ሊዮናርዶ ቼቪታሬዝ በጥንት ዘመን የነበሩ ጦርነቶች ስልታዊ አደረጃጀት ነበራቸው ይላሉ።

ከጥቃቶቹ በተጨማሪ፣ ከበባዎችን በማካሄድ የውሃ እና የምግብ አቅርቦት ወደ ጠላት ግዛት እንዳይገባ ይከለክላሉ።

አንዳንድ ስምምነቶችም ነበሩ።ፖዘር አክለውም በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነቶች ዓመቱን ሙሉ አይካሄዱም ነበር።

"የአየር ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገባሉ" ብለዋል።

"በጎርፍ ወቅት ወታደሮች ለማንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ጎርፍ ሲሆን ወታደራዊ ግጭቶችን አስወግደዋል። ሕዝቡም ፊቱን ወደ ግብርና ያዞራል።"

በሌላ በኩል ደግሞ "የጥንት ጦርነቶች እንደ እግረኛ እና ፈረሰኛ ያሉ አሁንም ጥቅም ላይ የሚያውሉ ብዙ ነገሮችን አካትተዋል" ሲል ሚሲያቶ ጠቁመዋል።

"ከጥንት ጀምሮ አንዳንድ ስልታዊ መከፋፈል ግልጽ ነበር" የሚሉት ሎፔዝ፤ ቀስተኞች እና የከተማን አጥሮችን ለማፍረስ የሚደረጉ የከበባ ልምዶችን በማዳበር መካከል ያለውን መለዋወጥ ጠቅሰዋል።

ሩዚት ግልጽ የሆነ ወታደራዊ አመራርም እንደነበረ ጠቁመዋል። ነገሥታት፣ የጎሳ አለቆች ወይም አዛዦች ጦርን በማደራጀት፣ ዘመቻዎችን በማቀድ እና ጦርነቶችን በማስተባበር ኃላፊነት ነበራቸው።

እንደ ሜሶፖታሚያ ባሉ ሥልጣኔዎች ውስጥ የሥርዓት ተዋረድ፣ ዲሲፕሊን እና የሥራ ክፍፍል ምልክቶች ነበሩ።

የጦር መሳሪያዎች የቴክኖሎጂ ዝግመተ ለውጥ አስፈላጊ ምዕራፍ ነው።

ቅድመ አያቶቻችን የሠሩት የመጀመሪያዎቹ የድንጋይ መሳሪያዎች በጣም መሠረታዊ ስለነበሩ "ለጦርነት ይቀር እና ለአደን ሊያገለግሉ የሚችሉ አልነበሩም" ሲሉ ኪጋን ተናግረዋል።

"በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ አብዮት" ብሎ የሚጠራው ሥራ የተከናወነው በኒዮሊቲክ ዘመን መጀመሪያ ላይ፣ ከ10,000 ዓመታት በፊት ነበር። እንደቀስት፣ ወንጭፍ እና ጩቤ ያሉ አራት "እጅግ በጣም ኃይለኛ አዳዲስ መሳሪያዎች" ብቅ አሉ።

ነገር ግን መሳሪያዎች የበለጠ ውጤታማ እና ገዳይ የሆኑት ከብረት መሠራት ሲጀምሩ ነው። ቀስ በቀስም ወታደሮች ቀስት፣ ጦር እና ድንጋይ ላይ ብቻ ሳይሆን ሰይፍ፣ ጩቤ እና ጋሻዎችንም መጠቀም ጀመሩ።

"ለጦርነቶች ምስጋና ይግባውና የብረት ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል" ሲል ሚሲያቶ ያስታውሳሉ።

በቁፋሮም በቆዳ የተሸፈኑ የብረት የራስ ቆቦች ተገኝተዋል።

"የራስ ቆቦቹ የተሠሩት ከመዳብ ሲሆን የሰው ልጅ መሥራት የተማረው የመጀመሪያው ውድ ያልሆነ ብረት ነው" ሲሉ ጠቁመዋል።

ካለው ጥንካሬ አንጻር ወታደራዊ ጥቁሙ ግን አነስተኛ ነበር።

ነገር ግን መዳብን በማደባለቅ ጠንካራ ነሐስ ማምረት ተለማመዱ።

"በሦስተኛው ሚሊኒየም መጨረሻ ይህ ዘዴ ተስፋፍቶ ነበር" ይላሉ ኪገን።

ለምሳሌ መጥረቢያ መኖሩ የታወቀው ከዚህ ዘመን ጀምሮ ነው።

"ሰይፎች በነሐስ ዘመን [ክርስቶስ ልደት በፊት ከ3300 እስከ 1200] የነበሩ ሲሆን በብረት አጠቃቀም መጨመርም ተስፋፍተዋል" ሲሉ ሎፔዝ ያስረዳሉ።

ለእሳቸው "ታላቁ ወታደራዊ አብዮት" የመጣው "ፈረስን በውጊያ ውስጥ መጠቀም በተጀመረበት" ከዚህ ከነሐስ ዘመን ጀምሮ ነው።

መጀመሪያ ላይ ለመጋለብ ጥቅም ላይ አልዋሉም ነበር። ብዙውን ጊዜ ጥንድ ሆነው የጦር ሠረገላዎችን ይጎትቱ ነበር።

"ብዙ ውድመት ያደርሱ ነበር፤ የዚያ ዘመን ታንኮች ነበሩ" ይላል ሎፔዝ።

ከዚህም በላይ "በጣም ውጤታማ የሆነ የጦርነት መሳሪያ ሽብር ነበር። ለምሳሌ የጠላት ወታደሮችን አንገት የመቁረጥ ልማድ በስፋት ተስፋፍቶ ነበር" ይላሉ ፖዘር። ይህም "የስነልቦና ሽብር አካል ነበር።"

ከላጋሽ እና ኡማ በፊት

ከጽሑፍ መዛግብት በፊት ጦርነት ተብሎ የሚታሰበው ምንድን ነው? ቀደም ባሉት ጊዜያት ጦርነትን የሚገልጸው፣ አልፎ አልፎ ከሚከሰት ወይም በሰው ልጆች መካከል ካለ ቀላል ግጭት የሚለየው ምንድን ነው?

"ጦርነትን የምንገልጽበት መንገድ ብዙ የዘፈቀደ ስሜት አለው" ሲል ሎፔዝ አስተያየታቸው ሰጥተዋል።

"በግልጽ ለመናገር በሁለት ቡድኖች መካከል ሞት የሚያስከትል ገዳይ ግጭት ይሆናል። ነገር ግን ጦርነት የሚባለው በአገራት ወይም በክልላዊ ተቋማት ውስጥ ግጭቶች ሲኖሩ ብቻ ነው።"

ለሩዚት ደግሞ ጽንሰ-ሐሳቡ ከአመራር፣ ከውጊያ ዝግጁነት፣ ከስልታዊ የኃይል አጠቃቀም እና ከአንድ በላይ የሆኑ ዓላማዎችን ያካተተ "እንደ ግዛትን መቆጣጠር፣ የንግድ መስመሮችን መቆጣጠር፣ ማስገበርን ወይም የፖለቲካ ሥልጣንን ማስከበር ያሉትን የሚያካትት ነው።"

የታሪክ ምሑሩ ሚሲያቶ በበኩላቸው አንድ ግጭት እንደ ጦርነት እንዲቆጠር፣ የግዛት እና የፖለቲካ ገጽታዎች ሊኖሩት ይገባል።

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የመጀመሪያው የጦርነት የጽሑፍ መዝገብ ከመጻፉ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ በሰውዎች መካከል ግጭት መኖርን ያረጋግጣሉ። ይህን የሚያረጋግጠው ማስረጃ የምሽጎች መሠራት ነው።

ይህም በአሁኗ የፍልስጤም ግዛት በዮርዳኖስ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ በምትገኘው ኢያሪኮ የሚታይ ነበር።

እንደ ሞሪስ ገለጻ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ8000 አካባቢ ነዋሪዎቹ ግንብ ገንብተዋል። ይህም በዓለም ላይ በአርኪኦሎጂስቶች የተገኘው ጥንታዊው የከተማ ግንብ ነው።

ይህ ግንብ "ለወታደራዊ ሥራ" ነበር ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ በታሪክ ጸሐፊዎች እና በአርኪኦሎጂስቶች መካከል ምንም ዓይነት መግባባት የለም።

ለኪገን በጣም አስደናቂው ጉዳይ መሠረቱ ላይ ሦስት ሜትር ውፍረት ያለው፣ አራት ሜትር ቁመት እና 650 ሜትር አካባቢ ወርድ ያለው ግንብ መሆኑ ነው።

ከድንጋይ እንጂ ከሸክላ የተሠራ አለመሆኑ "ጠንካራ እና የተቀናጀ ሥራ" መሆኑን ያመለክታል ብለዋል። ለተመራማሪው "ከረጅም ጊዜ ከበባ በስተቀር ሁሉንም ነገር የሚቋቋም እውነተኛ ምሽግ ነው።"