ዩኬ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምትወስደውን እርምጃ እንደማትቀላቀል አስታወቀች

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ በኢራን ላይ በምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ እንደማትሳተፍ አስታወቀች።

የዩኬ የባሕር ፈንጂ አምካኝ እና ፀረ ድሮን ኃይል በቀጣናው መንቀሳቀሱን ቢቀጥልም የብሪታኒያ የጦር መርከቦች እና ወታደሮች ግን የኢራንን ወደቦችን ለመዝጋት እንደማይሰማሩ ተገልጿል።

የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ "የባሕር እንቅስቃሴን በነፃነት ማድረግን እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን መደገፋችንን እንቀጥላለን። ይህም የዓለም ኢኮኖሚ እና በአገራችን የኑሮ ዋጋ ለማረጋጋት በአስቸኳይ የሚያስፈልግ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ የኢራን ወደቦችን ለመዝጋት የወሰነችው በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የተደረገው ድርድር በመክሸፉ ነው።

አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ዋና ከተማ እስላማባድ ድርድር ካደረጉ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ ማንኛውንም እና ሁሉንም መርከቦች እንደምታገድ አስታውቀዋል።

ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ጦሩ ዕግዱን "ያለ ልዩነት" በአረቢያን እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ ጨምሮ ወደ ኢራን ወደብ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ እንደሚያስፈፅም አረጋግጧል።

ሴንትኮም አክሎም የአሜሪካ ኃይል ከኢራን ወደቦች ውጭ የሚገቡ እና የሚወጡ የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት እንደማይሆን ገልጿል። ተጨማሪ መረጃዎች እግዱ ከመጀመሩ በፊት ለንግድ መርከቦች በይፋ እንደሚያሳውቅም ጠቁሟል።

ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ በወደብ የመዝጋት እርምጃቸው ሌሎች አገራት ተሳታፊ ይሆናሉ ያሉ ሱሆን፤ የትኞቹ አገራት እንደሆኑ ግን አልጠቀሱም።

ፕሬዝዳንቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ሰርጡን "ለማፅዳት" እርዳታ ማቅረቡን ተናግረዋል።

ትራምፕ አሜሪካ የባሕር ፈንጂዎችን የሚፈልግ ኃይል እንደምታሰማራ እና የኔቶ አባል አገር የሆነችው ዩናይትድ ኪንግደምም ይህኑ እንደምታደርግ ገልፀዋል።

"ዩኬ እና ሁለት የሚሆኑ ሌሎች አገራት ፈንጂ አምካኝ እንደሚልኩ ተረድቻለሁ" ብለዋል።

20 በመቶ ገደማ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት ጥቃት ከፈፀሙባት በኋላ ዘግታዋለች።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በዚህ ጦርነት አገራቸው ወታደራዊ ተሳትፎ እንደማይኖራት ደጋግመው ተናግረዋል።

በአንፃሩ ዩኬ በኢራን እርምጃ ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በማሻቀቡ ወሽመጡ እንዲከፈት ወትውታለች።

አገሪቱ ከፈረንሳይ እና ከሌሎች አጋራት ጋር በመሆን መርከቦች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረህ ሰፊ ጥምረት ለመፍጠት እየሰራች መሆኑንም አስታውቃለች።

ኤሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን እስላማባድ ባደረጉት ድርድር ዩናይትድ ኪንግደም ባትሳተፍም ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ንግግሩ ካለውጤት ከተበተነ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነቱ ከዚህ በበለጠ እንዳይስፋፋ አስጠንቅቀዋል።