ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢየሱስን መስለው የሚታዩበትን ምሥል መለጠፋቸው ትችት በማስነሳቱ ከገጻቸው አጠፉት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸውን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርጎ የሚያሳይ ምሥል በቱሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ማጋራታቸው ተቃውሞ ካስነሳባቸው በኋላ ከገጻቸው አጠፉት።

በሠው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሰራው ምሥል ዶናልድ ትራምፕ በሆስፒታል አልጋ ላይ የተኛን ታማሚ ሠው ሲያክሙ ያሳያል።

በዚህ ምስል የተነሳ ከታማኝ እና ቀንደኛ ደጋፊዎቻቸው ጀምሮ ከሁለቱም የአገሬው የፖለቲካ ጎራ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

ትራምፕ የማኅበራዊ የትስስር ገፅ ልጥፉን ያጋሩት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ላይ ትችት ያቀረቡትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ሊዮ 14ተኛን የሚተች ረዘም ያለ መልዕክት ካሰራጩ በኋላ ነው።

ትራምፕ ምሥሉን ማጋራቸውን አምነው፤ እቅዳቸው ግን ራሳቸውን እንደ ሐኪም ማሳየት እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አሁን በተሰረዘው ምሥል ላይ ፕሬዝዳንቱ ነጭ ጋወን ለብሰው በሚያንፀባርቅ እጃቸው የታመመው ሠው ግንባርን ሲነኩ የሚታዩ ሲሆን፤ ይህም እየሱስ ክርስቶስ ፈውስ ሲሰጥ የሚያሳዩ ኃይማኖታዊ ስዕሎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተቺዎች ተናግረዋል።

ከምሥሎ ጀርባ ደግሞ የሚውለበለብ ትልቅ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ፣ 'ስታቹ ኦፍ ሊብሪቲ' ተብሎ የሚጠራው ሀውልት፣ ተዋጊ ጄቶች እና ንስር እንዲሁም ነርስ፣ የምትፀልይ ሴት እና ወታደራዊ መለዮ የለበሰ ወታደርም ይታያሉ።

ምሥሉ ከተሰረዘ ከሰዓታት በኋላ ትራምፕ ምሥሉ ራሳቸውን ከቀይ መስቀል ሰራተኛ ጎን የቆመ ዶክተር አድርጎ ያሳያል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

"እንደ ዶክተር ሠዎችን የሚያሽል አድርጎ የሚያሳይ ነበር" ያሉት ትራምፕ፤ "እናም ሠዎችን አሽላለው፤ ሠዎችን በጣም አሽላለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ ምስሉን የሰረዙት ሠዎች ግራ እንዳይጋቡ በለመፈለጋቸው እንደሆነ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

ምሥሉ እንደተለጠፈ የትራምፕ እና የአስተዳደራቸው ደጋፊዎች ናቸው የሚባሉ ታዋቂ ሠዎችን ጨምሮ በርካቶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

አብዛኛው ትችት የተሰማው ኃይማኖታዊ መሠረት ካላቸው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ነው።

አወዛጋቢው የትራምፕ ምሥል የተለጠፈው ፖፕ ሊዮ 14ተኛን "ወንጀል ላይ ደካማ" እና "ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መጥፎ" በማለት ከተቹ በኋላ ነው።

ፖፕ ሊዮ አሜሪካዊ የመጀመሪያው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፤ በኢራን የተከፈተውን ጦርነት በተደጋጋሚ ተችተዋል።

ፖፕ ሊዮ የትራምፕን አስተዳደር ወይም የወንጌሉን መልዕክት ጮክ ብለው መናገር ላይ "ምንም ፍርሃት" እንደሌላቸው ሰኞ ዕለት ተናግረው ነበር።

ትራምፕ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ላቀረቡት ትችት ይቅርታ አልጠየቁም።

"ፖፕ ሊዮ ስህተት ነገሮች ተናግረዋል" ያሉት ትራምፕ፤ "በኢራን ላይ እያደረኩት ያለውን በጣም ይቃወማሉ። እኛ ኒውክሌር የታጠቀች ኢራን አንፈልግም። በመጨረሻው ውጤት ፖፕ ሊዮ ደስተኛ አይሆኑም" ብለዋል።

ትራምፕ በሠው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ ምስል በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ለጥፈው ትችት ሲደርስባቸው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።