ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ለምን እስካሁን 'በጅብ ሃብቷ' አልተጠቀመችም?
በተለምዶ የጅቦች ስም የሚነሳው ከክፉ ነገር ጋር ተያይዞ ነው። ጅቦችን ማጉረስ ባህል ከሆነበት የኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ክፍል ውጭ ስለ ጅቦች ያለው አመለካከት ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል።
በመቀለ ዩኒቨርስቲ እና በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው የሼፊልድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ግደይ ይርጋ ግን የተለየ ዕይታ አላቸው።
ጅቦችን በተመለከተ የሠሩት ጥናት እንሰሳቱ የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይጠቁማል።
ጅቦች የካርበን ልቀትን ይቀንሳሉ፤ አካባቢን በማጽዳት ከበሽታ ይከላከላሉ፤ ገንዘብም ይቆጥባሉ ቢባል ብዙዎች ያምኑ ይሆን?
ጅቦች እንዴት የካርበን ልቀትን ይቀንሳሉ?
የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እንቅልፍ ነስቷል። በአንድ ጽንፍ ከፍተኛ ወበቅ በሌላ ጽንፍ የጎርፍ መጥለቅለቅ ማስከተሉን ቀጥሏል።
የአየር ንብረት ለውጥን ከሚያባብሱ መካከል የካርበን ልቀት ይጠቀሳል። ካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሜቴንን ጨምሮ ሌሎችም የግሪንሀውስ ጋዞች ልቀት ሲደማመር የካርበን ልቀት ይባላል።
በኢትዮጵያ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ ወይም ሌሎች እንሰሳት ከታረዱ በኋላ በየመንገዱ ቅሪታቸው ይጣላል።
ዶ/ር ግደይ እንደሚሉት፤ ይሄ የእንሰሳቱ ቅሪት ሲበሰብስ እንደ ሜቴን እና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያለውን ግሪንሀውስ ጋዝ ይለቃል።
ጅቦች የእንሰሳት ቅሪተ አካል ከመበስበሱ በፊት ስለሚመገቡት የካርበን ልቀትን ይቀንሳሉ ማለት ነው።
"ጅቦች የእንሰሳት ቅሪተ አካል ሳይበሰብስ (decompose ሳያደርግ) በፊት ቶሎ ስለሚበሉት ጋዙ እንዳይለቅ ያደርጋሉ" ይላሉ።
ዶ/ር ግደይ ጥናታቸውን የሠሩት በመቀለ ከተማ ነው። ነገር ግን የጥናቱ ውጤት በሌሎች ከተሞችም ሊተገበር ይችላል።
እንደ ማሳያ መቀለን እንውሰድ። በመቀለ ከተማ ብቻ ጅቦች እና ሌሎችም ጥንብ አንሳዎች (scavengers) በየዓመቱ 1,063 ሜትሪክ ቶን የሚሆን የካርበን ልቀትን ያስወግዳሉ።
ይህም አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ጅቦች "ያልተጠበቀ ሚና እንዲኖራቸው" ማድረጉን አጥኚው ይናገራሉ።
በመቀለ ብቻ የዓመቱ የሚታረዱት እንሰሳት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ። ሁለት ሦስተኛው የእንሰሳቱ ቅሪት በየመንገዱ ይጣላል።
ጅቦች ከቆሻሻ ጋር የገጠሙት 'ግብግብ'
የቆሻሻ አወጋገድ የብዙ ከተሞች ችግር ነው። ዶ/ር ግደይ ጥናታቸውን በሠሩበት መቀለም የቆሻሻ አወጋገድ ሒደት "ደካማ" መሆኑን ይናገራሉ።
"ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት 40% ቆሻሻ ብቻ ነው የሚሰበሰበው" ይላሉ። ስለዚህም ቆሻሻ በየአካባቢው ተከምሮ ማየት የተለመደ ነው።
ጅቦች ቆሻሻን በመመገብ ከተሞችን ንጹህ የማድረግ ሚና ይጫወታሉ። በየዓመቱ 4,455 ሜትሪክ ቶን ቆሻሻ (organic waste) እንደሚያስወግዱ ጥናቱ ያሳያል።
ጅቦችን ተፈጥሯዊ ቆሻሻ ሰብሳቢ ልንላቸው እንችላለን። ጥናቱ እንደሚያሳየው፤ በዓመት ውስጥ መቀለ ቆሻሻ ለመሰብሰብ ወይም ለማስወገድ ታወጣ የነበረውን 89,000 ዶላር መቆጠብ ይቻላል።
ጅቦች መሰብሰብ እና መጓጓዝ ያለበትን ቆሻሻ መጠን ይቀንሳሉ። የከተማ ተፈጥሯዊ አጽጂዎች የሚባሉትም ለዚህ ነው።
ጅቦች በሽታን ያስወግዳሉ?
የእንሰሳት ቅሪት በየቦታው ሲጣል ዝንብ፣ አይጥ እና ሌሎችም በሽታ አስተላላፊ እንሰሳትን ይስባል።
የተከማቸ ቆሻሻ ጎጂ ባክቴርያ አዘል ነው። ይህም ሰዎችንም፣ ዕጽዋትንም፣ አካባቢንም ይጎዳል።
ጅቦች በፍጥነት የእንሰሳትን ቅሪት በመመገብ እና ቆሻሻን በማስወገድ በሽታን እንደሚከላከሉ ዶ/ር ግደይ ያስረዳሉ።
"ብዙ ነዋሪዎች እንደሚሉት ጅቦች በሚመገቡበት ቦታ ቆሻሻ በብዛት አይበሰብስም፤ ዝንቦችም ጥቂት ናቸው" ይላሉ።
ጅቦች ከየጎዳናው እና ከየሕዝብ አደባባዩ ቆሻሻ በማስወገድ የሰዎችን በበሽታ የመያዝ ዕድል ይቀንሳሉ። አካባቢን ንጹህ ማድረጋቸው የሰዎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ያስችላል።
'ጥቅማቸው ያልታየው ጅቦች'
ጅቦች እንደ "አደገኛ እና የማይፈለጉ" እንሰሳት እንደሚወሰዱ አጥኚው ታዝበዋል። "ጥናታችን ግን የጅቦችን የተለየ ገጽታ ያሳያል" ይላሉ።
እነዚህ እንሰሳት በሺህ ቶኖች የሚቆጠር ቆሻሻ ያስወግዳሉ። የካርበን ልቀትን ከመቀነስ በተጨማሪ ንጽህናን ይጠብቃሉ።
"ብዙ ሰዎች ይሄንን እንደሚረዱ ጥናታችን ያሳያል። 72% ያህል ነዋሪዎች ጅቦች ጠቃሚ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ጥናቱ ይጠቁማል" ይላሉ ዶ/ር ግደይ።
ስለዚህም ጅቦችን እንደ ችግር ብቻ ከመመልከት፤ ሰዎች፣ እንሰሳት፣ ዕጽዋት እና ሌሎችም ነፍሳት የሚገኙበትን መስተጋብር (urban ecosystem) አካል አድርጎ በመቀበል "ዋጋቸውን ማየት" እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ለምን እስካሁን 'በጅብ ሃብቷ' አልተጠቀመችም?
አጥኚው ለዚህ ጥያቄ መልስ አላቸው። ከዚህ ቀደም ሚናቸው በደንብ አለመጠናቱ እምብዛም ጥቅም ላይ ላለመዋላቸው አንድ ምክንያት ነው።
የከተማ ዕቅድ (urban planning) እና የቆሻሻ አወጋገድ (waste management) ፖሊሲዎች በዋናነት በሰዎች እና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
እናም የዱር እንሰሳት የሚሰጡት አገልግሎት ብዙም ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል።
ከተሞች ዕቅድ ሲያወጡ "ሰዎች እና የዱር እንሰሳት በሰላማዊ መንገድ አብረው መቀጠል የሚችሉበትን መንገድ ባማከለ ሁኔታ" መሆን እንደሚገባው ምክረ ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ።
ጅቦች እና የአየር ንብረት ለውጥ
በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፤ የዱር እንሰሳት ጠቃሚ ሚና እንዳላቸው ሳይንቲስቶች ከቀድሞውም ያውቃሉ።
ነገር ግን ከተማን በሚያዘወትሩ እንሰሳት (urban scavengers) እና በካርበን ልቀት መካከል ያለው ትስስር በጥልቅ እንዳልተለካ ዶ/ር ግደይ ይናገራሉ።
እንደ ጅቦች ያሉ እንሰሳት (scavenging animals) ቆሻሻ ሳይበሰብስ በመብላት የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀንት እንዴት እንደሚቀንሱ በግልጽ በማሳየት "የመጀመሪያ ከሆኑ ጥናቶች የእኛ አንዱ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።
የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እንዴት የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት እንደሚውል የሚያሳይ ነው።
በእርግጥ ታዳሽ ኃይል መጠቀም፣ የኢንዱስትሪዎች ልቀትን መቀነስ እና ኃይል መቆጠብን የመሰሉ ሁነኛ ስልቶችን ጅቦች እንደማይተኩ ያሰምሩበታል።
እነዚህ እርምጃዎች የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ጉልህ ድርሻ ይዘው ይቀጥላሉ።
"ጥናታችን የሚያሳየው ተፈጥሯዊ መንገድም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ሚና እንዳለው ነው" ይላሉ።
ብዝኃ ሕይወትን ማስጠበቅ እና ባለበት ማስቀጠል፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥረውን ጫና ማኅበረሰቡ መወጣት እንዲችል ያግዛል። ሳይንቲስቶች ደግሞ ተፈጥሮን መሠረት ላደረገ መፍትሔ ዕውቅና ይሰጣሉ።
የዶ/ር ግደይ ጥናት፤ ጅቦች እንዴት ባልተጠበቀ መንግድ የመፍትሔው አካል እንደሚሆኑ ማሳያ ነው።
ጅቦች የሚሰጡት አገልግሎት "ወጪ ቆጣቢም" ጭምር ነው።
ጅቦችን ማጥናት
ዶ/ር ግደይ በመቀለ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳሉ ነበር ስለ ጅቦች የማወቅ ፍላጎት ያደረባቸው።
"በዩኒቨርስቲው ዙሪያ ምሽት ላይ ብዙውን ጊዜ ጅቦች እመለከት ነበር። በብዙ አገሮች ውስጥ ከተሞች አቅራቢያ እንዲህ ያሉ ግዙፍ እንሰሳት (large predators) ስለማይኖሩ ስለ እነሱ የማወቅ ጉጉት ተፈጠረብኝ" ሲሉ ያስታውሳሉ።
እንደ መቀለ እና ሐረር ባሉ ከተሞች ጅቦች ከሰዎች ጎን መኖርን ተላምደዋል።
ይሄንን "ልዩ ግንኙነት" መመልከታቸው፤ አብሮ የመኖር ሒደቱ ምን እንደሚመስል ለማወቅ እንዲጓጉ ምክንያት ሆኗል።
"ይሄ ልዩ ግንኙነት፤ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ያላወቁት ከጅቦች የሚገኝ ጥቅም ሊኖር ይችላል ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል" ይላሉ።
እነዚህ እንሰሳት ከተማ ውስጥ እየኖሩ ብቻ ሳይሆን "ከተማውንም እየረዱ" እንደሆነም አስተውለዋል።
ይሄንን መገንዘባቸው ጅቦችን የበለጠ ለማጥናት እና ሰዎችም የዱር እንሰሳትን ሚና እንዲረዱ ለማድረግ እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ።