አውሮፓ ያላት የአውሮፕላን ነዳጅ "ምናልባት ለስድስት ሳምንት ብቻ የሚበቃ" መሆኑን ባለሥልጣኑ ተናገሩ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አውሮፓ "ምናልባት ለስድስት ሳምንታት ብቻ የሚበቃ የአውሮፕላን ነዳጅ ቀርቷታል" ሲሉ የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኢኤ) ኃላፊ አስጠንቀቁ።

ድርጅቱ በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት አውሮፓ ከመካከለኛው ምሥራቅ የምታስገባቸውን ምርቶች ቢያንስ ግማሹን መተካት ካልቻለች በሰኔ ወር ያላት ክምችት በአስጊ ሁኔታ እንደሚቀንስ አስጠንቅቀዋል።

ከባህር ሰላጤው የሚመጣው የአውሮፕላን ነዳጅ የሚያልፍበት የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ቴህራን ሙሉ በሙሉ ዘግታው ቆይታለች።

ይህም የነዳጅ ዋጋን ከፍ ከማድረጉ ባሻገር የእጥረት ስጋትን አስከትሏል።

የአይኢኤ ዋና ዳይሬክተር ፋቲህ ቢሮል ለኤፒ እንደተናገሩት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ የሚቆይ ከሆነ በቅርቡ የበረራ ስረዛዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

በኢነርጂ አቅርቦትና ደህንነት ዙሪያ ለ32 አባል አገራት ምክር የሚሰጠው የአይኢኤ ወርሃዊ የነዳጅ ገበያ ሪፖርት እንዳመለከተው የባህረ ሰላጤው አገራት የዓለማችን ግዙፉ የአውሮፕላን ነዳጅ አቀራቢ ናቸው።

እንደ ኮሪያ፣ ሕንድ እና ቻይና ያሉ ሌሎች አገሮች ውስጥ የሚገኙ የነዳጅ ማጣሪያዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ በሚመጡ ድፍድፍ ነዳጅ ምርቶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ናቸው።

በዚህም ምክንያት ቀውሱ "በአቪዬሽን የነዳጅ ገበያዎች ውስጣዊ አሠራር ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል" ሲል ድርጅቱ ገልጿል።

የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ሰዎች እና የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸውን መንቀሳቀሳቸውን ለማረጋገጥ" ከነዳጅ አቅራቢዎችና ከአየር መንገዶች ጋር በጥምረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

"የዩኬ አየር መንገዶች በአሁኑ ጊዜ የአቅርቦት መቆራረጥ እንደማይገጥማው ግልጽ ነው" ብለዋል።

ኤርላየንስ ዩኬ፣ በዩኬ የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ላይ ችግር ባያጋጥምም፣ የነዳጅ መቆራረጥ በሚከሰትበት ጊዜ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የሚያስፈልጉትን "ወሳኝ እርምጃዎችን" በተመለከተ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ተናግሯል።

ቀደም ሲል አውሮፓ 75 በመቶ የሚሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ የምታስገባው ከመካከለኛው ምሥራቅ እንደነበር የዓለም አቀፉ የአውሮፕላን ነዳጅ ኢንዱስትሪ (አይኢኤ) አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገራት ከባህር ሰላጤው የሚመጡ አቅርቦቶችን ከሌላ ቦታ በሚያስገቡት ምርት ለመተካት እየተጣደፉ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት እነዚህን ምርቶች በአሁኑ ወቅት እያገኙ ያሉት ከአሜሪካ እና ከናይጄሪያ ነው።

አይኢኤ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ከአሜሪካ የሚገባው የአውሮፕላን ነዳጅ መጨመሩን አስታውቋል።

እነዚህ ከአሜሪካ እና ናይጄሪያ የሚመጡ የነዳጅ አቅርቦቶች በሙሉ ወደ አውሮፓ ቢገቡም እንኳ ከተስተጓጎለው የመካከለኛው ምሥራቅ አቅርቦት ከግማሽ ትንሽ የሚበልጠውን ብቻ እንደሚተኩ በሪፖርቱ አስጠንቅቋል።

አውሮፓ ከመካከለኛው ምሥራቅ የምታስገባውን ምርት ከ50 በመቶ በላይ መተካት ካልቻለች "በተወሰኑ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ እጥረት ሊፈጠር ይችላል፣ ይህም የበረራ መሰረዝ እና የፍላጎት መስተጓጎል ሊያስከትል ይችላል" ብሏል።

ሦስት አራተኛ የሚሆነውን አቅርቦት መተካት ከተቻለ፣ ተመሳሳይ ሁኔታ አሁንም ሊፈጠር ይችላል ያለው ኤጀንሲው ይህ ግን እስከ ነሐሴ ወር ድረስ እንደማይፈጠር አስታውቋል።

"በዚህም ምክንያት፣ በቀጣይ ወራት በቂ ክምችት እንዲኖር ከተፈለገ የአውሮፓ ገበያዎች ከሌላ ቦታ ተጨማሪ ተተኪ ነዳጅ ለማስገባት ጠንክረው መሥራት የሚያስፈልጋቸው ይመስላል" ብሏል።