ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊጉ ዋንጫ የት ያርፋል? ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን የዋንጫ መዳረሻ የሚወስነው ጨዋታ እሑድ ዕለት በማንቸስተር ሲቲ እና በመሪው አርሰናል መካከል ይደረጋል።
በዚህ ምክንያትም ጨዋታው ከወዲሁ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ለንደን አቅንቶ ከቼልሲ ጋር የሚያከናውኑት ጨዋታ ጨምሮ በ248ኛው የመርሲሳይድ ደርቢ ኤቨርተን እና ሊቨርፑል የሚያደርጉት መርሃ ግብር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን እነዚህን ጨምሮ ሌሎች ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ገምቷል።
ቅዳሜ
ብሬንትፎርድ ከ ፉልሃም
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ፉልሃም ነበር ያሸነፈው።
ብሬንትፎርድ በበኩሉ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቋል።
ቡድኑ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድል ቢኖረውም ይህንንም ጨዋታ በአቻ ውጤት ያጠናቅቃል።
ግምት፡ 1 - 1
ሊድስ ከ ዎልቭስ
ሊድስ ሰኞ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ከ 2 ለ 1 በላይ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ይችል ነበር።
ዶምኒክ ካልቨርት-ሌዊን ሁለት ጎሎችን የማስቆጠር ዕድሎች ነበሩት።
ዎልቭስ ባለቀ ሰዓት ጎል ተቆጥሮበት እስኪሸነፍ ድረስ ከዌስትሃም ጋር መፎካከር ችሏል።
ይህ ጨዋታ ከባድ ቢሆንም ሊድስ ሦስቱን ነጥቦች እንደሚያሳካ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ኒውካስል ዩናይትድ ከ በርንመዝ
ኒውካስል አቋሙ እየወረደ ሲሆን በተከታታይም በሰንደርላንድ እና በክሪስታል ፓላስ ተሸንፏል።
አሰልጣኝ ኤዲ ሃው የቀድሞ ቡድናቸው በርንመዝ ለዘጠኝ ጊዜ ቢገጥሙም አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻሉም።
በርንመዞች በጥሩ አቋም ላይ ከመሆናቸውም በላይ ባለፈው ሳምንት አርሰናልን ማሸነፍ ችለዋል።
ይህንን ጨዋታ ግን ኒውካስል እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ቶተንሃም ከ ብራይተን
የቶተንሃም የውድድር ዓመት ምንም መልካም ነገር የሚነሳበት ሊሆን አልቻለም።
ካለፉት 14 ጨዋታዎች የመጀመሪኣው ድል ለማስመዝገብ ቡድኑ ወደ ሜዳ ይገባል።
ቡድኑ ብራይተንን አሸንፎ ሦስቱን ነጥብ ያሳካሉ ብዬ አላስብም።
ብራይተኖች ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስቱን ያሸነፉበትን ጉዞ ያስቀጥላሉ ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 0 - 1
ቼልሲ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ዩናይትድ ከሊድስ ጋር በነበረው ጨዋታ ምንም መነሳሳት አልነበረውም።
ቼልሲም በበኩሉ ከውጤት ከራቀ ሰነባብቷል።
ቡድኑ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ከማንቸስተር ሲቲው ጨዋታ ውጭ ያደረገበት ምክንያት አላሳመነኝም።
ቡድኑ በሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ ይኖርበታል። ዩናይትድ እንዳበለፈው ጨዋታ ተቀዛቅዞ ከቀረበ አሸናፊነቱ የሰማያዊዎቹ እንደሚሆን አስባለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
እሑድ
አስቶን ቪላ ከ ሰንደርላንድ
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ሰንደርላንድ በ10 ተጫዋቾች አንድ አቻ ለመለያየት ተገዷል።
ባለፈው ሳምንት ከቶተንሃም ጋር በነበረው ጨዋታም ሰንደርላንድ የተደራጀ ቡድን እንዳለው ማሳየት ችሏል።
ይህ ጨዋታ ከባድ ፉክክር የሚደረግበት ቢሆንም ቪላ በሜዳው አሸንፎ በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድሉን እንደሚያሰፋ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 - 0
ኤቨርተን ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ ከፒኤስጂ ጋር ጥሩ የተጫወተበት አጋጣሚ ቢኖርም ውጤታማ አልሆነም።
ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ውጤት ለማግኘት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይኖርበታል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 1 -1
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ በርንሌይ
ይህ ለፎረስት የዓመቱ ትልቅ ጨዋታ ነው።
ሦስት ነጥቦችን ለማሳካት ምርጥ አጋጣሚ ቢሆንም ከፍተኛ ውጥረት የሚኖርበት ጨዋታ ይሆናል።
በርንሌይ ከሊጉ የመውረዱ ነገር የማይቀር በመሆኑ በነጻነት ስለሚጫወት ለፎረስት ፈታኝ እንደሚሆን እጠብቃለሁ።
ግምት፡ 1 - 0
ማንቸስተር ሲቲ ከ አርሰናል
አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊግ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር በነበረው ጨዋታ የተከላካይ ክፍሉ ጠንካራ ቢሆንም ጎል የማስቆጠር ችግሩ ታይቷል።
ቡድኑ ቡድኖችን ኳስ ለማስጣል እና ተደራጅቶ ለመጫወት እንደሚችል ቢያሳይም የፊት መስመሩ ክፍተት አለበት።
በዚህ ምክንያት ሲቲ ጨዋታወን ያሸንፋል ማለት ቢቻልም አርሰናል አቻ መውጣትም በቂው ነው።
ይህ ደግሞ መድፈኞቹ በማትቃት እና በመከላከል ረገድ ሚዛኑን ጠብቀው እንዲጫወቱ ያደርጋቸዋል።
ሲቲ ጨዋታውን በበላይነት እንደሚያጠናቅቅ ባስብም ከፍተኛ ፉክክር ይገጥመዋል።
እንደዤርሚ ዶኩ እና አንቶኒ ሴሜኖ ያሉ ተጨዋቾች ጨዋታን የመቀየር አቅም አላቸው።
ግምት፡ 1 - 0
ሰኞ
ክሪስታል ፓላስ ከ ዌስት ሃም
ዌስት ሃም ይህንን ጨዋታ ሲያከናውን ላለመውረድ የሚፎካከሩትን ቡድኖች ውጤት አውቆ ነው።
ፓላስ ባለቀ ሰዓት ኒውካስልን አሸነፎ ከሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች በማሳካት በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ አሳይቷል።
ዌስት ሃም ከዎልቭስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ጎል እስኪያስቆጥር ድረስ ያለመረጋጋት ነበረው።
ይህም ጨዋታ ከፍተኛ ውጥረት የሚፈጥርባቸው ቢሆንም በአቻ ውጤት ጨዋታውን ያጠናቅቃሉ።
ግምት፡ 1 - 1