"በምፅዋ ወደብ" በኩል ለህወሓት የቀረበ "ለአንድ መጠነኛ አገር" የሚሆን መሣሪያ መያዙን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, ebc/youtube
ከመስከረም አጋማሽ አንስቶ በተደረገው ውጊያ የትግራይ ኃይሎች "በምፅዋ ወደብ የተላለፈላቸውን የአንድ መጠነኛ አገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሣሪያ" መማረኩን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች የደቡባዊ ኤርትራ ከተማ ወደሆነችው "መንደፈራ ገብተዋል" ሲሉም ተደምጠዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ይህንን ያሉት፤ ዛሬ እሑድ ጥቅምት 15/2019 ዓ. ም. በአዲስ አበባ እየተከበረ ባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 119ኛ ዓመት ክብረ በዓል ባደረጉት ንግግር ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ያደረጉት ንግግር በአብዛኛው ያተኮረው መስከረም 13 ቀን ስለተቀሰቀሰው እንዲሁም የፌደራል መንግሥት እና አጋር ኃይሎቹ የትግራይ ዋና ከተሞችን ስለተቆጣጠሩበት ውጊያ ነው።
ይህ ውጊያ የተቀሰቀሰው ህወሓት፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን (ኦነሠ) ጨምሮ ሰባት የትጥቅ እና ፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት መመሥረታቸውን ካወጁ ከቀናት በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለኅልውና የተባለው ይህ ጥምረት "የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት እንደሚንቀሳቀስ አስታውቆ ነበር።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዛሬው ንግግራቸው፣ " 'መከላከያ ሠራዊትን እናፈርሳለን፣ የሽግግር መንግሥት እናመጣለን' የሚሉ ደፋር ባንዳዎች ተፈልፍለዋል" ብለዋል። ታጣቂዎቹን "የአገሪቱን ምሰሶ አፍርሰው፣ አገር ለማፍረስ የከጀሉ" በማለት የገለጿቸው ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፣ "በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላት እየተነዱና እየተጫኑ ቋንቋቸው የተደባለቀ፣ ገንጣይና ሽብርተኛ፣ የባዕድ ተልዕኮ ተሸካሚ ፍጡራን ናቸው" በማለት ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በፊት የተጀመረው ውጊያ ውስጥ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኤርትራ እጃቸው እንዳለበት በመግለፅ ፌደራል መንግሥቱ ያቀረበውን ክስ በድጋሚ ሰንዝረዋል። "ከግብፅ እስከ ካርቱም እና አሥመራ የተቀናጀው" ሲሉ የገለጹት ጥምረት፤ "ህወሓትን በመላክ በሰሜን ወሎ፣ በዋግ እና በአፋር ግንባሮች ጦርነት መክፈቱን" ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ "ራሱ በከፈተው ጦርነት እንዳልነበር ሆኗል" ብለዋል። በዚህ ውጊያ በኤርትራ በኩል ገብቷል ያሉት ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ መያዙንም አክለዋል።
"በምፅዋ ወደብ የተላለፈላቸው የአንድ መጠነኛ አገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሣሪያ ሠራዊታችን ተቆጣጥሯል" ሲሉ ተናግረዋል። "ሠራዊታችን በእግዚአብሔር ፍትሕ እየተመራ ሰባት የፅምዶ ቡድኖችን፣ የትብብር ኃይሎችን፣ ሦስት የጀርባ የውጭ ኃይሎችን አሸንፏል" ብለዋል።
"ለመከላከያ የተመኙትን መፈራረስ ተጎንጭተው የትግራይን ንብረት ጭነው መንደፈራ ገብተዋል" ሲሉ የህወሓት አመራሮች ወደ ኤርትራ ተሻግረዋል የሚል ክስ አቅርበዋል።
የትግራይ ኃይሎች "ስልታዊ ማፈግፈግ" አድርገናል ማለታቸውን ጠቅሰውም፣ "በውትድርና ጥበብ ማፈግፈግ ሁሉንም አቅም ጥሎ በአስር ቀን ከሰሜን ወሎ፣ አፋር መንደፈራ ገብቶ መገኘት ማለት አይደለም" ሲሉም ክሳቸውን አጠናክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, ebc
አክለውም "[ህወሓት] አሁን ወደ ባልደረባው ሻዕቢያ ሄዷል። ህወሓት ከተቻለው አምስተኛ እንቅፋት እንዳይመታው ከማድረግ የሚመልሰው አእምሮ የለውም። ነገር ግን አምስተኛ ዕድል እንዲኖረው አናደርግም" ብለዋል።
የህወሓት አመራሮች ወደ ኤርትራ ተሻግረዋል የሚለውን ክስ ህወሓት እና የኤርትራ መንግሥት ከሰሞኑ ውድቅ አድርገውት ነበር። የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አማኑኤል አሰፋ "አመራሩ ትግራይ ውስጥ እየሠራ ነው" ሲሉ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀልም በተመሳሳይ "ውሸት" ሲሉ ክሱን ውድቅ ማድረጋቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል። የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ይደግፋል በሚል የቀረበበትን ክስም ተቃውሟል።
ኢትዮጵያ "ራስን በመከላከል ስም" በሉዓላዊት የተባበሩት መንግሥታት አባል አገር ላይ የምትፈጽመውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው ስትል ኤርትራ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ አስታውቃለች።
ግብፅ እና ሱዳንም በተመሳሳይ ውንጀላውን ውድቅ አድርገዋል።
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዛሬው ንግግራቸው የአባይ ወንዝ እና የቀይ ባሕር ጉዳይን አንስተዋል። አባይን "የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋ" በማለት የገለጹት ሲሆን ቀይ ባሕርን ደግሞ "እኛ ኢትዮጵያውያን እንድንገለገልበት ፈጣሪ ያበጃጀው ባሕር" ሲሉ ጠርተውታል።
"ሁለቱም ውሃዎች ለቀጣናው የሚበቁ ናቸው" ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ "ነገር ግን ብቻውን ሊጠቀልል የሚፈልግ ገብጋባ እየታገልን ነው" ብለዋል። "የኢትዮጵያ መንግሥት እና መከላከያ ሠራዊት ከሁለቱ ውሃዎች የሚገኘውን የኢትዮጵያን ጥቅም ከማስከበር ውጪ አማራጭ የላቸውም" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከ2016 ዓ. ም. አንስቶ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ለማግኘት ያለውን ፍላጎት ሲገልጽ ቆይቷል። ከመንግሥት ዋነኛ አጀንዳዎች ቀዳሚ ሆኖ እየወጣ ካለው የባሕር በር ጉዳይ ላይ የአሰብ ወደብ መነሳቱን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት አዲስ አበባ በኃይል የውሃ አካሉን ልትይዝ እንደሆነ የሚገልጽ ክስ አቅርቧል።
ሰሞነኛው ውጊያ መነሳቱን እና የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛቶች መግባታቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።































