ለአጋማሽ ዘመን ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ባራክ ኦባማ የትራምፕን አስተዳደር ወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለዴሞክራቶች ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ባራክ ኦባማ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርን ተችተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከኢራን ጦርነት እና ከኑሮ ውድነት ጋር በተያየዘ ትራምፕን ነቅፈዋል።
በኦሀዮ ባደረጉት ንግግር "የዚህን አስተዳደር ቂላቂልነት በትንሹም ቢሆን ለመቀነስ የመጨረሻው አማራጫችን ይሄ ምርጫ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ በጆርጂያ ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ አስተዳደራቸው በስደተኞች ላይ የወሰደውን እርምጃ እና ታሪፎች መጣሉን በማንሳት "የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን ላይ እንገኛለን" ብለዋል።
የአጋማሽ ዘመን ምርጫው በቀሪው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን ኮንግረስን በአብላጫ የሚይዘውን ፓርቲ ይወስናል።
ትራምፕ ዕቅዶቻቸውን ማስፈጸም የሚችሉበት አቅም የሚወሰነው አብላጫ መቀመጫ በሚያገኘው ፓርቲ አማካኝነት ይሆናል።
መራጮች ድምጽ መስጠት የጀመሩ ሲሆን ትራምፕ እና ባለቤታቸው ሜላኒያ በፍሎሪዳ ድምጽ ሰጥተዋል።
ኦባማ በኦሀዮ እና ሚችጋን ቅስቀሳ ባደረጉበት ወቅት፤ ትራምፕ ዋይት ሀውስን ለማስዋብ ባደረጉት ጥረት ተሳልቀዋል።
"ወርቁ ምን ይሠራል? ዋይት ሀውስን የሳዳም ሁሴን የቺዝ ኬክ ቤት አስመሰለው" ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ወርፈዋል።
ኦባማ አክለውም "ሁለት ዓመት ሙሉ የነበረው ቀውስ፣ ጭካኔ፣ ሙስና እና የብቃት ማነስ በመዘናዊ ታሪክ ያልታየ ነው። በቃ ማለት የምትችሉበት ዕድል አላችሁ" ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 ከነበረው የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት፣ የዋጋ ንረት እና ኮሮናቫይረስ ከፈጠረው ቀውስ ጋር በተያያዘ ለዴሞክራቶች ድምጽ ያልሰጡ ሰዎች መኖራቸውን እንደሚገዘነቡ ኦባማ ገልጸዋል።
ሆኖም ግን አሁን ላለው የምጣኔ ሃብት ቀውስ ተጠያቂው ትራምፕ ብቻ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
"ያኔ ከእሱ በፊት [ከትራምፕ ሥልጣን መያዝ አስቀድሞ] ሁሉም ነገር ውድ የሆነ መስሏችሁ ከነበረ፣ አሁን ሁሉም ነገር የእውነት ውድ ሆኗል" ብለዋል የቀድሞው ፕሬዝዳንት።
ትራምፕ የነዳጅ ዋጋ "በጊዜያዊነት" መጨመሩን አምነው፣ አገሪቱ "በየጊዜው እየጠነከረች በመሄዷ" ዋጋው እንደሚቀንስ ገልጸዋል።
በኢራን እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መናሩ ትራምፕ ላይ ጫና አሳድሯል።
ትራምፕ "በታሪፍ አማካኝነት ከፍተኛ ገንዘብ እያገኘን ነው" ያሉ ሲሆን፤ ሪፐብሊካኖች አብላጫ ድምጽ አግኝተው ካሸነፉ ለእያንዳንዱ አዋቂ አሜሪካዊ 5,000 እንደሚሰጡ በድጋሚ ቃል ገብተዋል።
ዴሞክራቶች "ሃብታችሁን ይበዘብዙታል፤ ድንበራችሁን ያፈርሱታል" በማለትም መራጮችን አስጠንቅቀዋል።
"ሽብር የተንሰራፋባቸው" ካሏቸው እንደ ሊቢያ፣ የመን፣ ሄይቲ እና ሶማሊያ ያሉ አገራት ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
ትራምፕ ከሕዝብ እንደራሴዎች ጋር መነጋገራቸውን ጠቅሰውም "ለምንድን ነው ሁሌም ከአስቀያሚ አገራት ስደተኞች የምንቀበለው? ብዬ ጠይቄያለሁ። ለምን ከኖርዌይ፣ ስዊድን ወይም ዴንማርክ ሰዎችን አንወስድም?" ብለዋል።
ባራክ ኦባማ በበኩላቸው በኢራን ጦርነት ትራምፕን ተችተዋል። በጦርነቱ ምክንያት ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ "ውሳኔ ሰጪ የመሆን ጉልበት" እንዳገኘች ጠቅሰዋል።
ትራምፕ ስለ ኢራን ጦርነት ሲጠየቁ፤ አዲስ ጥቃት የሚሰነዘርበት አልያም ስምምነት ላይ የሚደረስበት ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በሩሲያ በተያዘችው ኦልሽኪ ከተማ በሩሲያ እና ዩክሬን መሀል የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማድረጋቸውን ዋይት ሀውስ አስታውቋል።































