ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ሶሪያን አወጣች
አሜሪካ ከ47 ዓመታት በኋላ ሽብርን የሚደግፉ ብላ ከዘረዘረቻቸው አገራት ውስጥ ሶሪያን ማውጣቷን አስታወቀች።
በሶሪያ የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዳይኖር "የመጨረሻው ዋና መሰናክል" የነበረው በሽብር ደጋፊነት ፍረጃ መነሳቱ አገሪቱ ከዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ጋር ዳግም እንድትዋሃድ የሚያስችል ነው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ ይህ እርምጃ የተወሰደው የሶሪያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የሽብር ተግባራት ራሱን ለማራቅ ለወሰደው አወንታዊ እርምጃ እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር፣ ከዚህ ቀደም የአል ቃኤዳ ቅርንጫፍ መሪ የነበሩትን አዲሱን የሶሪያ ፕሬዝዳንት አህመድ አል-ሻራን ተቀብሏል።
አሜሪካ፣ የቀድሞ ታጣቂ የነበረውን የአሁኑን የሶሪያ ፕሬዝዳንት ለመያዝ ለሚረዳት ሰው የሽልማት ገንዘብ ጭምር አዘጋጅታ ነበር።
"ሀያት ታህሪር አል-ሻም" የተባለው እሳቸው የሚመሩት እስላማዊ ቡድንም ከአሜሪካ የዓለም አቀፍ አሸባሪ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ተሰርዟል።
ቀደም ሲል "አል-ኑስራ ፍሮንት" በመባል የሚታወቀው ሀያት ታህሪር አል-ሻም፣ አል-ሻራ ከጅሃዲስት አውታር ጋር የነበረውን ግንኙነት እአአ በ2016 እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ በአል ቃኤይዳ ስር የነበረ የሶርያ ቅርንጫፍ ነበር።
"ሀያት ታህሪር አል-ሻም" በ2024 መጨረሻ ላይ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድን የገለበጠውን የአማጺያን ጥቃት መርቷል። በአሁኑ ሰዓትም ቡድኑ በሶሪያ የሽግግር አስተዳደር ላይ የበላይነት አለው።
አሜሪካ ሶሪያን ከሩሲያ ወይም ከቻይና ተፅዕኖ በማራቅ ወደ ራሷ ምህዋር ለማምጣት ተስፋ አድርጋ እየሰራች ነው።
ይሁን እንጂ ሶሪያ አሁንም ደኅንነቷ የተጠናከረ አለመሆኑ እንዲሁም የተረጋጋ መንግሥት አለመመስረቷ ፈታኝ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም በጎረቤቶቿ እስራኤል እና ቱርክ ውጥረት መካከል ትገኛለች።
ሐምሌ ላይ ታቅዶ ትናተት ሰኞ ተግባራዊ የሆነው ሶሪያን ከሽብር ደጋፊ አገራት ዝርዝር ውስጥ የመሰረዝ ውሳኔ፥ የሶሪያን ሕዝብ "ወደ ብልጽግና መንገድ ያስገባል" ሲሉ ሩቢዮ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት፣ "የዛሬው እርምጃ በሶሪያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚያስችል ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል" ብለዋል።
የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ ሃሳን አል-ሻይባኒ "ታሪካዊ እርምጃ" ሲሉ የአሜሪካን ውሳኔ ማድነቃቸውን የሶሪያ የዜና ወኪል ሳና ዘግቧል።
ሚኒስትሩ "የመገለል ተፅዕኖን ለማስወገድ እና በግልጽነት፣ በጋራ ፍላጎት እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሁኔታን ለመፍጠር መስራታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ "ሀያት ታህሪር አል-ሻም"ን ከውጭ አሸባሪ ድርጅት ዝርዝር ስትሰርዝ፥ መሪውን ሻራንም በልዩ ሁኔታ ከተፈረጁ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ዝርዝር አስወጥታለች።
አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ ከ1979 ጀምሮ ሶሪያ ላይ የጣለችውን ሽብርተኝነትን የምትደግፍ አገር የሚል ፍረጃ በማንሳቷ፣ በአሁኑ ሰዓት በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙት ብቸኛ አገራት ኩባ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን ሆነዋል።
በዝርዝሩ ውስጥ ባሉ አገራት ላይ የገንዘብ ማዕቀቦች፣ የአሜሪካ የውጭ እርዳታ እና የመከላከያ ምርቶች ሽያጭ ገደቦች የተጣሉ ሲሆን ማዕቀቡ ከተጣለባቸው አገራት ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ ግለሰቦች እና ሌሎች አገሮችም ሊቀጡ ይችላሉ።