ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛት በተደረገው ቅድመ ምርጫ ያሸነፈችው ሜላት ኪሮስ ማን ናት?
ዲሞክራቲክ ሶሻሊስቷ ሜላት ኪሮስ ዲሞክራቲክ ፓርቲን ለመወከል በኮሎራዶ ግዛት በተደረገ የአካባቢ ቅድመ ምርጫ አሸንፋለች።
ትናንት ማክሰኞ በተካሄደው ምርጫ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት ዲያና ደጌትን ማሸነፍ ችላለች።
የሜላት ማሸነፍ ፓርቲው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካስመዘገባቸው ድሎች አንዱ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በስፋት ዘግበዋል።
ሜላት የዲሞክራቲክ ፓርቲው ይፋዊ ዕጩ የሆነች ሲሆን፣ በቀጣይ ከሪፐብሊካን ዕጩ ጋር ትወዳደራለች። ካሸነፈችም የተወካዮች ምክር ቤት ትገባለች።
ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርክ በተካሄደ ምርጫ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ሁለት ዴሞክራቲክ እንደራሴዎችን በሌሎች ዕጩዎች ተተክተዋል።
በስምንት ቀናት ውስጥ ከምክር ቤት አባል እንደራሴ ጋር ተፎካክራ ምርጫ ያሸነፈች ሦስተኛዋ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ መሆኗን ሲኤንኤን ዘግቧል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሜላት ኪሮስ በቀጣይ ዓመት ኅዳር ላይ በሚደረግ ምርጫ የምትወዳደር ይሆናል።
የ29 ዓመቷ ሜላት በአውሮፓውያኑ 2022 ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ኖተር ዳም በሕግ ተመርቃለች።
እስራኤል በሐማስ የተፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ላይ የወሰደችውን እርምጃ የተቃወሙ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች "ፀረ ሴማዊ" ናቸው መባላቸውን በመተቸት የበይረ መረብ ጽሑፍ ማቅረቧን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
ጽሑፉን ከበይነ መረብ ለማውረድ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ትሠራበት ከነበረው የሕግ መሥሪያ ቤት መባረሯም ተገልጿል።
ለኮንግረስ እንደምትወዳደር ስትገልጽ ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ድጋፋቸውን እንደገለጹላት የዘ ጋርዲያን ዘገባ ያትታል።
ሜላት በምርጫው ስትወዳደር ዲሞክራቲክ ሶሻሊስትስ ኦፍ አሜሪካ እና ጀስቲስ ዲሞክራትስ ድጋፍ ከሰጧት ተራማጅ (progressive) ቡድኖች መካከል ተጠቅሰዋል።
ጀስቲስ ዲሞክራትስ ባወጣው መግለጫ ሜላት "የዴንቨር ነዋሪዎች ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምን እንደሚመስል ለመወሰን እና በማን መወከል እንደሚፈልጉ ለመምረጥ በማነሳሳቷ" አድናቆቱን መግለጹ ተዘግቧል።
በሪፐብሊካኖች በአብላጫ ወደተያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመግባት ሜላት የምትወዳደርበት ቀጣይ ምርጫ፤ ዲሞክራቶች በምክር ቤቱ የሚኖራቸውን የመቀመጫ ብዛት የሚወስን እንደሆነ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሜላት በምርጫው ዕለት ለደጋፊዎቿ ባደረገችው ንግግር "በሁሉም የኃላፊነት ደረጃ ከጥግ እስከ ጥግ እያሸነፍን ነው። ፓርቲያችንን እና አገራችንን እያስመለስን ነው" ማለቷን የሲኤንኤን ዘገባ ይገልጻል።
ሜላት የ68 ዓመቷ ዲያና ደጌትን ማሸነፏን ተከትሎ ዲሞክራቲክ ፓርቲን የሚደግፉ ድምጽ ሰጪዎች ወደ ወጣት ፖለቲከኞች እያዘነበሉ መምጣታቸውን እንደሚጠቁም አስተያየቶች ተስተጋብተዋል።
በተለይም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በዕድሜ የገፉ ፖለቲከኞች በብዛት ያሉበትን ፓርቲ በወጣት እጩዎች የመተካት አካሄድ እንደሚስተዋል ተገልጿል።
ሜላት አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ላይ እንዲሁም በትራምፕ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲዎች ላይም ጥያቄዎች ማንሳቷ ተገልጿል።
ሲኤንኤን እንደዘገበው ሜላት ያሸነፈቻቸውን የሕዝብ እንደራሴ "የከሸፈው አስተዳደር" አድርጋ ትመለከታለች።
"ዲሞክራቶች በአሥርታት ባልታየ መጠን ድጋፋችን ቀንሷል። ምክንያቱ ደግሞ ለሠራተኛው ማኅበረሰብ ምንም አለማድረጋችን" ነው ስትል በምርጫ ክርክር ወቅት ተናግራለች።
የሜላትን ማሸነፍ ተከትሎ ዲሞክራቲክ ሶሻሊስቶስ ደስታቸውን መግለጽ ቀጥለዋል።
ሲኤንኤን እንደዘገበው፤ የምርጫው ውጤት ከተገለጸ በኋላ ባደረገችው ንግግር ማሸነፏ "እንደማንጠብቅ ግልጽ መልዕክት የሚያሳይ ነው" ብላለች።
"ትግሉን ዶናልድ ትራምፕ እና ባለ ጸጎች ጋር መውሰድ" በንግግሯ ነጠቀሰቻቸው ነጥቦች መካከል ነው።
የአሜሪካ የጉምሩክ ቁጥጥር ባለሥልጣን (አይስ) ማክሰም እንዲሁም "ያለፈውን የፖለቲካ ምዕራፍ መዝጋትንም" ጠቅሳለች።
"በፍልስጤም እየተፈጸመ ያለውን የዘር ጭፍጨፋ ለማስቆም" ያላትን ቁርጠኝነትም ገልጻለች።
አሸናፊነቷን "ከዚህ ቅጽበትም በላይ ነው" ስትል የገለጸችው ሜላት "ይሄ ንቅናቄ ነው፤ እናም ገና እየጀመርነው ነው" ብላለች።
አዲስ አበባ ተወልዳ በሕጻንነቷ ወደ አሜሪካ የሄደችው ሜላት አሁን ለዕጩነት ያገኘችው ድል ለምክር ቤት አባልነት የማሸነፍ ዕድሏ ሰፊ እንደሆነ አመለክቷል።
ከወራት በኋላ በሚደረገው ምርጫ አሸንፋ ወደ አሜሪካ ምክር ቤት የምትገባ ከሆነ በ29 ዓመቷ በዕድሜ ትንሿ እንደራሴ ለመሆን ትችላለች። የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የአሜሪካ ምክር ቤት አባልም ትሆናለች።