ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የደረሰባትን ከፍተኛ ኪሳራ ለማካካስ ተማሪዎችን እየመለመለች እንደሆነ ተገለፀ
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የደረሰባትን ኪሳራ ለማካካስ ተማሪዎችን ለውትድርና እየመለመለች ነው።
የዩኒቨርሲቲ፣ የቴክኒክ ኮሌጅ እና የሙያ ተማሪዎች ጦሩን እንዲቀላቀሉ የሚያበረታታው የአገሪቱ ዘመቻ የተጀመረው በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ነው።
ዘመቻው በዋናነት ትኩረት ያደረገው በትምህርታቸው ደካማ የሆኑ እንዲሁም ከትምህርታቸው እረፍት ለመውሰድ እያሰቡ ባሉ ተማሪዎች ላይ ነው።
ምልመላው ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ሙሉ ወረራ የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎችን ለመተካት ያለመ ነው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር አንድሬ ቤሎውሶቭ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ጦሩ በዋናነት ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
በሳምንታት ውስጥም ወጣት ተመልማዮች "አዲስ ቴክኖሎጂን እና ፍጥነቱን" ይበልጥ እንደሚቀበሉ በማሰብ ምልመላው በመላው ሩሲያ የትምህርት ተቋማት ተጀምሯል።
የቢቢሲ ሩሲያ አገልግሎት ያገኘው መረጃ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ቢያንስ በ95 ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች ምልመላዎች እንደተደረጉ አመልክቷል።
ሚያዝያ ወር ላይ የተማሪዎች ጆርናል ለድሮን ኃይሎች ኮታ የተሰጣቸው የዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆችን ቁጥርን ወደ 270 አድርሶታል።
ምልመላውም በጥንቃቄ የተደረገ ነው።
ተማሪዎች ለሥልጠና እና በድሮን ክፍል ብቻ ለማገልገል ለአንድ ዓመት እንዲፈርሙ ተነግሯቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ትምህርታቸው ከመመለሳቸው በፊት ከፍተኛ ክፍያ እንደሚያገኙ እና ወሳኝ ቴክኒካዊ ክህሎት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል።
በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች አጠቃላይ ክፍያን፣ ወደ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት በቀላሉ መግባትን ወይም የተሻለ መኖሪያን ጨምሮ ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸዋል።
በመዲናዋ ሞስኮ ለተማሪዎች የተበተነ በራሪ ወረቀትም በጎ ፈቃደኞች በመጀመሪያው ዓመት ወደ 57 ሺህ ዶላር እንደሚሰጣቸው ይገልጻል።
ሆኖም የሕግ ባለሙያዎች እና የመብት ተሟጋቾች እነዚህ ቃል ኪዳኖች ተፈፃሚ ላይሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
በዚህ ሁኔታ ተመልምለው ወደ ጦር ግንባር የተላኩ በርካታ ተማሪዎችም መሞታቸው ተገልጿል።
ከሞቱት ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ቫለሪ አቬሪን አሳዳጊ ኦክሳና አፋናዬቫ "ልጇ ለሦስት ወራት የድሮን ሥልጠና እንደተሰጠው እና ከዚያ በኋላ ወደ ግንባር እንደወረወሩት" ተናግራለች።
የ23 ዓመቱ አቬሪን መጀመሪያ ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመልመለው በዩክሬን ከተገደሉ ተማሪዎች አንዱ ነው።
"በሠራዊቱ ውስጥ እንኳን አገልግሎ አያውቅም" ስትልም አፋናዬቫ ቅሬታዋን ገልጻለች።
ባለሥልጣናት አቬሪን ዘመናዊ፣ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ያለው እና በአንጻራዊነት ደኅንነቱ የተጠበቀ የጦር ኃይሎች ቅርንጫፍ ውስጥ ለመግባት በፈቃደኝነት የተመለመለበትን ዕቅድ አቅርበዋል።
የ18 ዓመቱ ቭላዲስላቭ ጎርቡኖቭም በሰሜናዊ የዩክሬን ድንበር የተገደለው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ኮንትራት ከተፈራረመ ከአራት ወራት በኋላ ነበር።
ጎርቡኖቭ በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ውስጥ የባቡር መንገድ ግንባታ እና ጥገና ትምህርቱን እየተከታተለ ነበር።
ወጣቱ ከምልመላ በኋላ ወደ ድሮን ኦፕሬተሮች ክፍል ከመግባቱ በፊት ወደ ግንባር ተልኳል።
በማዕድን የትምህርት ዘርፍ ትምህርቱ ሲከተታል የነበረው ማራክሂም አብዱሊንም፣ በትምህርቱ ስላልተሳካለት ከ18ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ካከበረ ሁለት ሳምንት በኋላ ጥር ወር ላይ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ በማሰብ ለድሮን ኦፕሬተርነት ተመዝግቧል።
"እዚያ ከሄደ በኋላ ግን ምንም ደኅንነቱ የተጠበቀ አልነበረም፤ የጦር ግንባር ላይ ነበሩ" ብላለች እናቱ ኤሌና።
"በፍጥነት ሄዶ በፍጥነት ነው የተመለሰው" ስትልም ከሄደ ከሦስት ወራት በኋላ መሞቱን ገልጻለች።
ሩሲያ በጦርነቱ አብዱሊን፣ ጎርቡኖቭ እና አቬሪን የተባሉትን ሦስት የቀድሞ ተማሪዎችን ጨምሮ 230 ሺህ 407 ወታደሮች እና መኮንኖችን ማጣቷን ቢቢሲ በመቃብር ሥፍራዎች፣ የጦር መታሰቢያዎች ፣ በመንግሥት መረጃዎች እና የማስታወሻ ጽሑፎች ትንተናው አረጋግጧል።
ትክክለኛው የሞቱ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር ቢቢሲ ካረጋገጠውም እንደሚበልጥ ይታመናል። ወታደራዊ ባለሙያዎች የቢቢሲ ትንተና የሚያመለክተው ከአጠቃላዩ ከ45 እስከ 55 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው ብለዋል።
በዚህ ስሌት መሠረት የሟቾች ቁጥር ከ417 ሺህ እስከ 509 ሺህ 500 ይደርሳል።
የዩናይትድ ኪንግደም ግዙፉ የደኅንነት ተቋም - ጂሲኤችኪው - እንዳለው ግንቦት ላይ የሟቾች ቁጥር 500 ሺህ ገደማ ደርሶ ነበር።
ዩክሬንም በተመሳሳይ በጦርነቱ በርካታ ወታደሮቿ ተገድለውባታል።
ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ የካቲት ወር ላይ 55 ሺህ ወታደሮች እንደሞቱ እና በርካቶች እንደጠፉ ገልጸዋል።
አንድ የዩክሬን ድረ ገጽ በአጠቃላይ የሞቱ ወታደሮች 213 ሺህ እንደሚደርስ ያመለከተ ሲሆን የደች የጦር ደኅንነት የሟቾች፣ ጉዳት የደረሰባቸው እና የጠፉ ወታደሮች ቁጥር ወደ 500 ሺህ እንደሚደርስ ገልጿል።