ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል ከሚገኙ 138 የምርጫ ክልሎች በስምንቱ ምርጫ እንደማይደረግ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
በመላ አገሪቱ ሰኞ ግንቦት 24 በሚደረገው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአማራ ክልል ከሚገኙ 138 የምርጫ ክልሎች መካከል በስምንቱ ምርጫ እንደማይደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ በተጨማሪም የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ በትግራይ ክልል ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር በአንድ ላይ ምርጫ የማይካሄድ መሆኑን ገልጿል።
ቦርዱ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም. የቅድመ ምርጫ ሥራዎች እና የድምፅ መስጫ ቀንን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በአጠቃላይ በ46 ምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይደርግ አስታውቋል።
የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ በመግለጫ ላይ በአማራ ክልል በስምንት፣ በትግራይ ክልል ደግሞ በ38 የምርጫ ክልሎች ምርጫ አይካሄድም ብለዋል።
በአማራ ክልል ድምጽ የማይሰጥባቸው ስምንቱ የምርጫ ክልሎች በደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ በአምባሰል እንዲሁም በደጋ ዳሞት የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።
የቦርድ ሰብሳቢዋ ሰኞ ዕለት ድምጽ በማይሰጥባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ወደፊት እንዲመርጡ እንደሚደረግ ቢናገሩም ጊዜውን ግን ሳያሳውቁ ቀርተዋል።
አክለውም ስድስት ፓርቲዎች ከሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ከውድድር ውጪ መሆናቸውን እና 42 ፓርቲዎች የመራጮችን ድምጽ ለማግኘት እንደሚፎካከሩ ተናግረዋል።
ከውድድሩ ውጪ የሆኑት ፓርቲዎች ሦስቱ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ስምረት፣ ቃንጪ ሀቂ እና ትንሳዔ ሰብዓ እንደርታ መሆናቸውን ሲገልጹ ቀሪዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ 10,400 በላይ ዕጩዎች መመዝገባቸውን አስታውቀው ከዘጠኝ ፓርቲዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመመዝገብ የሚያስፈልጋቸውን መስፈርት ባለማሟላታቸው 80 ዕጩዎች ውድቅ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ (ኢሶዴፓ) "309 ዕጩዎች ከምርጫ ውድድር ውጪ ሆነዋል" እያለ ነው፤ ታዲያ ውድቅ የተደረጉ ዕጩዎች ቁጥር እንዴት 80 ብቻ ሆነ የሚል ጥያቄ ለቦርዱ ሰብሳቢ ቀርቦላቸዋል።
በሰጡት ምላሽ፤ 80 ዕጩዎች ውድቅ የተደረጉት ያላሟሉትን መስፈርት እንዲያሟሉ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ መሠረት ባለማሟላታቸው መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) 309 ዕጩዎች ግን ተመዝግበው ምስክር ወረቀት ካገኙ በኋላ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል። ይህ ሰፊ ልዩነት አለው ሲሉ 80 እና 309 ዕጩዎች ከውድድሩ ውጪ የሆኑበት ምክንያት እንደማይገናኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን አገራዊ ምርጫ ከሚታዘቡ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ባሻገር ከውጪ የሚመጡት የአፍሪካ ኅብረት እና ምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ታዛቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ ተጨማሪ በጀት መጠየቁ ተዘግቦ የነበረ ሲሆን፣ ሰብሳቢዋ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ የተወሰነ እንደተፈቀደላቸው አስታውቀዋል።
ቦርዱ በተጨማሪም በመራጮች ምዝገባ ችግር በተስተዋለባቸዉ የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባው እንዲሰረዝ ማድረጉን አስታውቋል።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በመግለጫቸዉ "ምዝገባዉ እየተካሄደ እያለ በሚደርሱ ጥቆማዎች ቦርዱ የራሱ የሆነ ክትትልን ሲያደርግ ቆይቷል" ብለዋል።
ቦርዱ ችግር አለባቸዉ የተባሉ ምርጫ ጣቢያዎችን አስመልክቶ በቪዲዮ እና በወረቀት በደረሰዉ በማስረጃ የተደገፈ ጥቆማ መሠረት ምዝገባዉ መሠረዙን አስታውቋል።
በመሆኑም ምዝገባ ከተሰረዘባቸዉ አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ግምጃ ቤት ምርጫ ጣቢያ፣ በሶማሌ ክልል ሰገን ምርጫ ጣቢያ፣ በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙበት ተነግሯል።
በመጪው ሰኞ በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ መራጮች ለክልል ምር ቤቶች እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሚሆኑ እንደራሴዎቻቸውን ይመርጣሉ።