ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'የማያመልጡት ወጥመድ'፡ እናት በመሆናቸው የሚጸጸቱት ሴቶች
ካርመን የአስር ዓመት ልጇ ቲዮን በጣም ትወደዋለች። ወደኋላ ተመልሰሽ አንድ ነገር መቀየር ትችያለሽ ብትባል ግን እናት አልሆንም ነበር ትላለች።
"እናትነት ጤንነቴን፣ ጊዜዬን፣ ገንዘቤን፣ ጉልበቴን እና ሰውነቴን ነጥቆታል" ትላለች። "ዋጋው በጣም ውድ ነው፤ የሚከፈለውም ለዘላለም ነው።"
በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው አስተማሪዋ ካርመን እናት በመሆናቸው ከሚጸጸቱ ሴቶች መካከል ነች።
ይህ ጸጸት አልፎ አልፎ ነው የሚነገረው። ይህንን ስሜታቸውን ያጋሩን ሴቶች ቤተሰቦቻቸው ስለማያውቁ ሊኖር የሚችለውን ከባድ መዘዝ በመፍራት ስማቸው እንዲገለጽ አይፈልጉም።
ካርመን ከጥቂት ዓመታት በፊት በተደረገ የወላጆች መድረክ ላይ ጸጸቷን በቃላት ገልጻለች። አንዳንድ ሰዎች ርህራሄ ቢያስይዋትም ሌሎች ደግሞ "አስፈሪ" እና "ጭራቅ" እንደሆነች አድርገው ስለዋታል።
ካርመን "እናትነት ባንፈልገው እንኳ የሚከተለን እና የምናከናውነው ማለቂያ የሌለው ሥራ ነው፣ ምክንያቱም ልጆቻችን በእኛ ላይ ጥገኛ ናቸው… የማናመልጠው ወጥመድ ይመስላል" ትላለች።
እናት መሆን ምን ያህል "አስከፊ" እንደሆነም ያለማመንታት ትናገራለች። ስለልጇ ስትጠየቅ ግን ድምጸቷ ጭምር ብሩህ ይሆናል።
"ቲዮ ከጸጸቴ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ድንቅ፣ የሚያምር ልጅ ነው። በጣም እወደዋለሁ" ትላለች። "ያለጥርጥር ሕይወቴን ለእሱ እሰጣለሁ። ደግ፣ ቀላል እና ጎበዝ ተማሪ ነው።"
"ብዙውን ጊዜ ሴቶች ስለእናትነታቸው ጸጸታቸውን ለመናገር የሚደፍሩ ከሆነ ይህ የሚመጣው ከፍቅር እጦት ሳይሆን ከመገለል፣ ከድካም ወይም ከጠፋ ማንነት ስሜት ነው" ይላኡ የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ አና ማቱር።
ለካርመን "ጥሩ ዜጋ፣ መልካም እና ደስተኛ ሰው" ማሳደግ ትልቅ ኃላፊነት ነው። ይህም ኃላፊነቷን ከባድ ያደርገዋል።
ቲዮ እንደ ትልቅ ሰው እንዲቆጥራት በጭራሽ እንደማትፈልግ ካርመን ለራሷ ቃል ገብታለች። ከድሃ ቤተሰቦች የተገኘችው ካርመን ቤተሰቧም ጥሩ አልነበረም። "ጉልበት ዋና ቋንቋ የነበረበት" ቤት ሲሆን ፍቅር የማግኘት ስሜት ተሰምቷት አታውቅም።
መጀመሪያ ላይ እናት መሆን "የሚያስደስት" ነበር ትላለች። ልጇ ጥሩ እንቅልፍ ይተኛ ነበር። በወሊድ ፈቃድ ላይ እያለችም ሕፃን ልጇን በመንከባከብ ያሳለፈቻቸውን ቀናት ትወዳቸው ነበር።
ልጇ ከባድ የዕድገት ውስንነቶች ማሳየት ሲጀምር እና "እያንዳንዱ ቀላል ነገር ወደ ስጋት ሲቀየር" ነገሮች ተቀያሩ ትላላች ካርመን።
"በጣም የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። ሕይወቱም ወደ ማያበራ ግብግብ ይቀየራል በሚል እጨነቅ ነበር።"
በኋላ ላይም ቲዮ ተመርምሮ ካርመን ትፈራው የነበረው ችግር እንደሌለበት ታወቀ። አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ነገር ግን ጭንቀቱ እና የማያቋርጠው ፍርሃት በሽታ እንዳስከተለባት ትናገራለች።
የእናትነት ጸጸትን ከፍቅር ማጣት እና ጥሩ ካልሆነ አስተዳደግ ጋር ማገናኘትተገቢነት ላይ ጥርጣሩ እንዳላቸው ከእናትነት በኋላ የሚፈጠር ጸጸትን የሚመለከት መጽሐፍ የጻፉት የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዋ ኦርና ዶናት ተናግረዋል።
ዶናት ለ23 እናቶች ቃለ መጠይቅ አድርገዋል። ለሁሉም የእናትነት ጸጸታቸው እና ለልጆቻቸው ባላቸው ስሜት መካከል ያለውን ልዩነት አፅንዖት ሰጥተውታል።
ብዙዎቹ በእናትነት እንደተታለሉ ተሰምቷቸዋል። ምክንያታቸው ደግሞ እውነታው እና ማኅበረሰቡ ለእነሱ ከሰጣቸው ሃሳባዊ እናትነት ጋር ስለማይጣጣም ነው።
"ልጆች በመውለዴ እና እናት በመሆኔ ተጸጽቻለሁ፤ ነገር ግን ልጆቼን እወዳቸዋለሁ... መኖራቸውን ብፈልገውም ግን እናት መሆንን አልፈልግም" ስትል በጥናቱ ውስጥ የተሳተፈች አንዲት የሁለት ታዳጊዎች እናት ተናግራለች።
ያለው መረጃ አነስተኛ ቢሆንም ይህ ያልተለመደ ስሜት እንዳልሆነ ያሳያል። በ2023 በፖላንድ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ5 እስከ 14 በመቶ የሚሆኑ ወላጆች ልጅ በመውለድ ውሳኔኔያቸው ይጸጸታሉ። በድጋሚ ዕድሉን ቢያገኙ ልጅ አለመውለደንም ይመርጣሉ።
ወላጆች ስለጸጸቱ በግልጽ ላይናገሩ ቢችሉም ግን በበይነ መረብ ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች እያገኙ ነው።
ካርመን ከመላው ዓለም 96 ሺህ አባላት ያሉት ልጅ በመውለቸዳው የተጸጸቱ ወላጆች ያሉበት የፌስቡክ ቡድንን ስትቀላቀል ብቻዋን እንዳልሆነች ተገነዘበች።
"እናትነት በጣፋጭ ጊዜያት የተሞላ ነው። ላገኝ እችል የነበረውን ነፃነት ግን አያካክሱም" ስትል ከአምስት ዓመት ልጇ ጋር በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት የቡድኑ አባል የሆነች እናት ለቢቢሲ ተናግራለች።
"በልጄ ዙሪያ ስሆን ጭምብሌን በደንብ እለብሳለሁ" ትላለች። ነገር ግን ወደ አልጋዋ ስትሄድ እና እኔ እና ባለቤቴ አብረን አጭር ግን ጥሩ ጊዜ ሲኖረን ጭምብሌ ይወልቅ እና ብቻዬን መሆንን እመርጣለሁ።"
ልጅ መውለድ ማለት የገንዘብ አቅምን ይፈትናል። መጓዝ፣ ሥራ መጀመር እና የኢንቨስትመንት ተቋም መገንባትን የመሳሰሉ ሁሉንም ግቦቿን እና ምኞቶቿን ትገፋለች።
"በዚህ በተበላሸ ዓለም ውስጥ ጨዋ ልጅ ለማሳደግ ከመሞከር ውጪ ያሉ ለማንኛውም ነገር ያለኝን ተነሳሽነት አጥቻለሁ" ትላለች።
ሌላኛዋ የቡድኑ አባል እና ነዋሪነቷ በዩናይትድ ኪንግደም ሆነች እና ሰዎች ደስተኛ ያልሆነች እናት ከወሊድ በኋላ በድብርት እየተሰቃየች እንደሆነ ማሰባቸው "አሳፋሪ" እንደሆነ ታምናለች።
"ሰዎች እንደዚያ ብለው መሰየማቸው የበለጠ ሊቀላቸው ይችላል። ልጆቼ አሁን አዋቂዎች ቢሆኑም እስካሁን ድረስ ስላላገኘሁትን ሕይወት አሁንም አዝናለሁ።"
"አሁን ደግሞ የልጅ ልጆችን ስለ መንከባከብ እጨነቃለሁ፤ እንክብካቤው ማቆሚያ የለውም።"
ልጆች ስለወለዱ የሚጸጸቱ ወላጆች አባ ልየሆኑበት የፌስቡክ ቡድን የተፈጠረው በአውሮፓውኑ 2007 ሲሆን፣ ይዘቱ ከወላጆች በአብዛኛው ከሴቶች የሚገኝ ነው። ታሪኮቻቸውን በውስጥ መስመር በመላክ ማንነታቸው ሳይገለጽ እንዲለጠፍ ይደረጋል።
የቡድኑ ተቆጣጣሪ የሆነችው አሜሪካዊቷ የላብራቶሪ ሳይንቲስት ጂያኒና "ዓላማው ወላጆችን ማሸማቀቅ ወይም የተለየ የአኗኗር ዘይቤ ማስተዋወቅ አልነበረም" ትላለች።
"ብዙውን ጊዜ ትልቅ ቦታ የሌለውን የባህል ክስተት መመዝገብ ነው" ትላለች።
"ማኅበረሰቡ ትልቅ እና ንቁ ነው። ብዙ ሰዎች ሊኖራቸው የማይገባቸውን ስሜቶች በፀጥታ እየታገሉ ነው።"
የ44 ዓመቷ ጂያኒና ልጆች ስለመውለድ ለመወሰን ተቸግራ ነበር። በመድረኩ ላይ የምታነባቸው ታሪኮች ላለመውለድ ለመወሰኗ ተጽዕኖ አሳድሯል ትላለች።
ወጣቶች ልጅ የመውለድ ጥያቄን በተመለከተ ከታላላቆቻቸው በጣም በተለየ መንገድ መመልከት ጀምረዋል ሲሉ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት እና ሰዎች ወላጅ መሆን አለመሆናቸውን እንዲወስኑ በመርዳት ላይ የሚሠሩት አማካሪዋ ማርጋሬት ኦኮነር ተናግረዋል።
"የምርጫ ጉዳይ መሆኑን የበለጠ ግንዛቤ አለ። ማድረግ ያለብዎት ነገር አይደለም" ይላሉ።
"በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ እና መውለድ የሚፈልጉ ነገር ግን ስለ ተግዳሮቶቹ የሚጨነቁ እና ይህንንም ለመቋቋም ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች አሉኝ።"
ሁሉም ሰው ተሞክሮው የተለያየ ስለሆነ አንዲት ሴት በእናትነት ውሳኔዋ እንደምትጸጸት የሚያሳዩ ምልክቶችን መጥቀስ ከባድ ነው ሲሉ ኦኮነር ያስጠነቅቃሉ።
"ስለዚህ ትልቅ ውሳኔ ከባልደረባዎ ወይም ከወላጆችዎ ከሚመጣ ውጫዊ ግፊት ይልቅ በተቻለዎት መጠን እርግጠኛ መሆን እና በራስዎ ምክንያቶች መወሰን አለብዎት" ይላሉ።
ሁሉም ሰው የሚደግፈውን ሃሳብ በቀላሉ ከመቀበል እንድንቆጠብ አስጠንቅቀዋል።
ኦኮነር ወላጆች ምን ያህል ትልቅ እና ከባድ ሚና እንዳላቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት ጸጸት ውስጥ መውደቃቸው ሙሉ በሙሉ የተለመደ ነው ይላሉ።
የዚያን ጸጸት መንስኤ ለማወቅ እና "ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ" ለመነጋገር ባለሙያን እንዲያማክሩ ይናገራሉ።
የእናትነት ጸጸት ሁልጊዜ "ሙሉ በሙሉ" ሊቀለበስ አይችልም ይላሉ ማቱር።
"ለአንዳንድ ሴቶች እነዚያ [የጸጸት] ስሜቶች በድጋፍ፣ በእረፍት፣ በጊዜ እና በሁኔታዎች መሻሻል በእጅጉ ይለዋወጣሉ።"
"ለሌሎች ግን ስሜቶቹ ሊቆዩ ይችላሉ። በመሆኑም ያለ ሀፍረት ለመነጋገር የሚያስፈልግ ቦታ መምረጥ አስፈላጊ ነው።"
የኦርና ዶናት ጥናት የሚያሳየውም ለአንዳንዶች የእናትነት መጸጸት ፈጽሞ የማይጠፋ ስሜት መሆኑን አረጋግጧል።
"ያነጋገርኳቸው ሴቶች ከጸጸታቸው ጎን ለጎን የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ይሞክራሉ" ይላሉ።
"ከጥቂት ዓመታት በፊት እናት በመሆኗ የምትጸጸት ሴት የላከችው ደብዳቤ ደረሰኝ። የረዳት ነገር ጸጸቱ አንድ ቀን እንደሚጠፋ ተስፋ አለማድረግ ነው... እንደማይጠፋ በተረዳች ቁጥርም ከመታገል እና ከመልፋት ይልቅ መቀበልን መርጣለች።"
ካርመን ስሜቱ ዘላቂ ነው ብላ ታስባለች፤ "መስዋዕትቱ የዘላለም ነው"።
ላለፉት ለጥቂት ዓመታት ባለሙያ ማናገር ስለጀመረች ራሷን እና ስለ እናትነት ምን እንደሚሰማት እንድትቀበል እንደረዳት ትናገራለች።
"ከአሁን በኋላ መራራ ስሜት አይሰማኝም" ትላለች።
አሁን ወደ ጂም ለመሄድ እና ጓደኞችን ለማየት ጊዜ ትመድባለች። ፍጹም ለመሆን ላለመታገል ለእራሷን ፈቃድ ለመስጠትም እየሞከረች ነው።
"በመጨረሻም 'አይ፣ ይቅርታ፣ ደክሞኛል እና በጊዜ ልተኛ ነው። ለእራት የምትፈልገውን ብላ፤ አባትህ እዚህ አለ'" ማለት ጀመረች።
ይህን ስታደርግ ዓለም እንደማይፈነዳ አወቀች።
"ቲዮ እኔ ሰው እንደሆንኩ፣ ፍጹም እንዳልሆንኩኝ ማየት ጀመረ። ይህም ችግር አልፈጠረበትም።"
ካርመን ከልጇ ጋር ስትሆን ስለሚፈጥረባት ደስታ ተጠይቃለች።
ቲኦ ከመተኛቷ በፊት ወደ አልጋው ይሄዱ እና ስለውሏቸው ይነጋገራሉ። ልጇ ወደ ብርድ ልብሱ ይገባ እናቱን አቅፎ ይተኛል።
"ከቲዮ ጋር የማወራበት በዓለም ውስጥ በጣም የምወደውን ሰው የማይበት አጋጣሚ ነው" ስትል ትመልሳለች።
"ከአሁን በኋላ ግን ጭራቅ እንደሆንኩኝ አይሰማኝም።"