አባትነት የወንዶችን አእምሮ በምን መልኩ ይቀይራል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

ወንዶች ልጆቻቸው ከመወለዳቸው በፊት እንኳ በባሕሪያቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እና በልጆቻቸው ደኅንነት ላይ ውጤት ያላቸው ከባድ የሆርሞን ለውጦች ያጋጥሟቸዋል።

ልጄ ከመወለዱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ፣ እኔና አጋሬ በወሊድ ዝግጅት አውደ ጥናት፣ ጡት በማጥባት ሥልጠና እና በሆስፒታል በሚመራው የቅድመ ወሊድ ትምህርት ላይ ተሳትፈናል፤ እንዲሁም በርካታ የእርግዝና እና የሕፃናት መጻሕፍትን አንብበናል፣ ብዙ ድረ-ገጾችንም ተመልክተናል።

በዚያን ጊዜ ከያዝኳቸው ማስታወሻዎች መካከል የሴቶች አካል ለወሊድና ለእናትነት የሚዘጋጅባቸው ብዙ መንገዶች ይገኙበታል።

ሆርሞኖች ይጨምራሉ እንዲሁም ይቀንሳሉ፣ የሰውነት ክፍሎች ቦታቸውን ይለውጣሉ፣ አእምሮም ቅርጹን ይቀይራል።

ሆኖም የእኔም አንጎል እና አካል ለአባትነት እየተዘጋጁ መሆኑን የነገረኝ ግን አልነበረም።

ልጄ አንድ ዓመት አልፎት ነው ይህን ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ "ፋዘር ታይም" (Father Time) በተሰኘው የአጥቢ እንስሳት ተመራማሪዋ ሣራ ብላፈር ሃርዲ መጽሐፍ ላይ ያገኘሁት፤ እሳቸውም እንደሚሉት ወንዶች ልክ እንደ ትጉህ እናቶች ሁሉ ተንከባካቢ እና ጠባቂ ለመሆን የሚያስፈልጋቸው ተፈጥሯዊ (ባዮሎጂካዊ) ዝግጅት አላቸው።

ይህ ጉጉቴን ቀሰቀሰው። እኔ አባት በንቃት ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ጽኑ እምነት ያለኝ ሰው ብሆንም ይህ የእኛ ትውልድ ወንዶች የባሕል ምርጫ መስሎኝ ነበር።

ከሃርዲ እና ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ቃለ-መጠይቅ ካደረግሁ እና ጥናቶችን ከመረመርኩ በኋላ ወደ አንድ ቀላል መደምደሚያ ደረስኩ፦ እናትነት ሴቶችን እንደሚለውጥ ሁሉ አባትነትም ወንዶችን ይለውጣል።

አንድ አባት በልጁ እንክብካቤ ውስጥ በበለጠ መጠን በተሳተፈ ቁጥር፣ ይህ ሽግግር ይበልጥ ጥልቅ ይሆናል።

በሆርሞን እና በነርቭ ሥርዓታችን ውስጥ የሚታዩት እነዚህ ለውጦች እንደሚያሳዩት ተንከባካቢ አባት መሆን ዘመናዊ እንግዳ ባሕሪ ሳይሆን፣ በጥልቅ ሥር የሰደደ ተፈጥሯዊ (ባዮሎጂካዊ) መገለጫ ነው።

የቴስቶስትሮን መጠን መቀነስ

አባቶች በልጆች ምክንያት አካላዊ ለውጥ እንደሚያመጡ የሚጠቁሙ የመጀመሪያዎቹ ጥናቶች የተገኙት ሌሎች እንስሳትን በመመልከት ነበር።

እነዚህ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙ ወንድ አጥቢ እንስሳት ከሰው ዘር ውጪም የሆኑትን ጨምሮ ንቁ የወላጅነት ክብካቤ በሚያደርጉበት ጊዜ እንደ ቴስቶስትሮን፣ ቫሶፕሬሲን እና ፕሮላክቲን ባሉ ሆርሞኖች ላይ ግልጽ የሆነ ለውጥ (መጨመር እና መቀነስ) ያሳያሉ። እነዚህ ሆርሞኖች በተለምዶ ከእናትነት ጋር ተያይዘው የሚታወቁ ናቸው።

አሜሪካዊው የሰው ዘር ጥናት ተመራማሪው ሊ ጌትለር በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ መጀመሪያ የቅድመ ምረቃ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ስለነዚህ ግኝቶች ሲሰሙ በጣም ተሳቡ።

አሁን በኢንዲያና በሚገኘው የኖተር ዳም ዩኒቨርሲቲ የሆርሞን፣ የጤና እና የሰው ልጅ ባሕሪ ቤተ-ሙከራ ዳይሬክተር የሆኑት ጌትለር እንዲህ ይላሉ።

"መምህሬን 'በሰዎች አባቶች ላይ እነዚህን ጥያቄዎች የሚያጠና ሰው አለ?' ብዬ ጠየቅኩት፤ በወቅቱ የነበረው መልስ ግን 'በጭራሽ የለም' የሚል ነበር።"

በወንዶች ላይ የሚታዩ የሆርሞን ለውጦችን የሚያሳይ የመጀመሪያው ጥናት በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2000 ዓ.ም. በሁለቱ ካናዳውያን ምሁራን ካትሪን ኤድዋርድስ እና አን ስቶሪ ታትሞ ነበር።

ጌትለር ወደዚህ ዘርፍ ጥናት በገባበት ወቅት፣ አባቶች ልጆች ከሌላቸው ወንዶች ያነሰ የቴስቶስትሮን መጠን እንዳላቸው የተረጋገጠ እውነታ ሆኖ ነበር።

ጌትለር ሲያስረዱ "እዚህ ጋር 'ዶሮዋ ወይስ እንቁላሉ ነው የቀደመው' የሚል ዓይነት ግራ የሚያጋባ ጥያቄ አለ" ይላሉ። "ዝቅተኛ የቴስቶስትሮን መጠን ያላቸው ወንዶች አባት የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው? ወይስ አባት መሆን በወንዶች ላይ ለሚከሰቱት ተከታታይ ባዮሎጂካዊ ለውጦች ምክንያት ይሆናል?"

ለዚህ እና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት፣ ጌትለር በፊሊፒንስ ለበርካታ አሥርት ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ከሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች ጋር ተባብረው መሥራት ጀመሩ።

በአውሮፓውያኑ 2005 ይህ ቡድን የትዳር አጋር ከሌላቸው እና አማካይ ዕድሜያቸው 21 ዓመት ከሆነ 624 ወንዶች የምራቅ ናሙና በመውሰድ የቴስቶስትሮን መጠናቸውን መረመረ፤ ከዚያም ከአራት ዓመታት በኋላ ድጋሚ ምርመራ አደረገ።

ጥናቱ ለሁለት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያለመ ነበር። በዚያ የጊዜ ልዩነት ውስጥ አባት የሆኑ ወንዶች ዝቅተኛ የቴስቶስትሮን መጠን ይኖራቸዋል? እንዲሁም በሕፃናት እንክብካቤ ላይ ብዙ ሰዓት በሚያሳልፉ አባቶች ላይ መጠኑ ይበልጥ ይቀንሳል?

የጥናቱ ውጤት ሲታወቅ የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ "አዎ" የሚል ሆነ። ልጆች ያሏቸው ወንዶች ልጆች ከሌላቸው ወንዶች ጋር ሲነጻጸሩ በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅተኛ የሆነ የቴስቶስትሮን መጠን አሳይተዋል።

በተጨማሪም ሕፃናትን በመንከባከብ ረጅም ጊዜ ያሳለፉ ወንዶች ላይ የቴስቶስትሮን መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ተገኝቷል። ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር በአንድ አልጋ ላይ የሚተኙትም ዝቅተኛ መጠን ነበራቸው።

"ወንዶች ለአባትነት የመዘጋጀት አቅም እንዳላቸው በሳይንሳዊ ጽሑፎች ውስጥ የቀረበው የመጀመሪያው ግልጽ መልዕክት ይመስለኛል" ብለውኛል ጌትለር። በሌላ አነጋገር የእነርሱ ባዮሎጂ ለክብካቤ እያዘጋጃቸው መሆኑን የሚያሳይ እንደማለት ነው።

የእነርሱ ግኝት የተለየ አይደለም። ሌሎች የምርምር ቡድኖችም በፍቅር አጋራቸው እርግዝና ወቅት የሚታይ የቴስቶስትሮን መጠን መቀነስ፣ ከወሊድ በኋላ ከሚኖር ከፍተኛ ትጋት፣ ቁርጠኝነት እና እርካታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ደርሰውበታል።

በተጨማሪም የዚህ ሆርሞን መጠን ወንዶች ለሕፃናት ልቅሶ ከሚሰጡት ምላሽ ጋር የተያያዘ ነው፤ ይህም ይበልጥ ንቁ እና ምላሽ ሰጪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በአውሮፓውኑ 2018 በጌትለር ላብራቶሪ ውስጥ የሚሠራ አንድ ቡድን ዝቅተኛ የቴስቶስትሮን መጠን ያላቸው አባቶች ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን በመንከባከብ ረገድ ይበልጥ ንቁ የመሆን ዝንባሌ እንዳላቸው ደምድሟል።

ነገር ግን ይህ የሚከሰተው መቼ ነው? ይህ ለውጥ የሚመጣው ከወሊድ በፊት ነው ወይስ በኋላ? የሚለው ጥያቄ በአሜሪካ ኤሞሪ ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጅ ማኅበራዊ የነርቭ ሳይንስ ላብራቶሪ ዳይሬክተር በሆኑት የጄምስ ኬ ሪሊንግ አእምሮ ውስጥ ይመላለስ ነበር።

ሪሊንግ "የእኔ ግምት ለውጡ የሚመጣው ከወሊድ በኋላ አባቶች ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር የተወሰነ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ይሆናል የሚል ነበር" ብለውኛል።

ያገኙት ውጤት ግን አስገራሚ ነበር። እርግዝና በተፈጠረ በአራት ወራት ውስጥ ብቻ የወደፊት አባቶችን ሲመረምሩ፣ ሁለት ሆርሞኖች (ቴስቶስትሮን እና ቫሶፕሬሲን) ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ብለው ተገኝተዋል።

በ2024 "ፋዘር ኔቸር" የተሰኘ የአባትነትን ሳይንስን የሚመረምር መጽሐፍ ያሳተሙት ሪሊንግ "የሚያስገርመው ነገር፣ የቴስቶስትሮን መጠናቸው ዝቅተኛ በሆነ መጠን ከወሊድ በኋላ ከእናትየው እና ከሕፃኑ ጋር ያላቸው ተሳትፎ ይበልጥ ይጨምራል" ይላሉ።

ሪሊንግ ይህ ለውጥ ለምን እንደሚከሰት ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አደረባቸው። የወደፊት አባቶች ከነፍሰ ጡር አጋሮቻቸው የሚያገኙት የሽታ ምልክት ይኖር ይሆን? ወይስ ልጅ እንደሚወልዱ ካወቁ በኋላ የሚመጣ ሥነ-ልቦናዊ ለውጥ ነው?

በዚህ በአንጻራዊ ሁኔታ በጅማሬ ላይ ባለው የጥናት ዘርፍ ውስጥ እንደሚታዩ ብዙ አስገራሚ ግኝቶች ሁሉ፣ ለዚህም እስካሁን መልሱን አናውቅም። እርግጠኛ የሚያደርገው ግን ለውጡ ከቴስቶስትሮን በላይ መሆኑን ነው።

የፍቅር ሆርሞን ማዕበል

ለምሳሌ "የፍቅር ሆርሞን" ተብሎ የሚጠራውን ኦክሲቶሲንን እንውሰድ። ይህ ሆርሞን ከቅድመ ወሊድ ትምህርቶቼ የማስታውሰው የትዳር አጋሬ የኦክሲቶሲን መጠን እንዲጨምር እና ምጥ እንዲቀልላት በወሊድ ወቅት ነገሮች ቀለል በማድረግ ዘና ማለት ይበረታታ ነበር።

ልጄ ከተወለደም በኋላ በወሊድ ወቅት የሚፈጠረው ከፍተኛ የኦክሲቶሲን መጠን እና በጡት ማጥባት ወቅት የሚኖረው ተደጋጋሚ መነቃቃት እሱ እና እናቱ እንዲቀራረቡ እንደሚረዳ ተነግሮን ነበር። ነገር ግን ልጄ በተወለደ በመጀመሪያዎቹ ሰዓታት በራቁት ደረቴ ላይ ተኝቶ ሳለ በእኔም ውስጥ የኦክሲቶሲን መጠን እየጨመረ መሆኑን አላውቅም ነበር።

በዓለም ዙሪያ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የሆናቸው ልጆች ባሏቸው እና ዕድሜያቸው ከስድስት ወር በታች ከሆኑ ሕፃናት ጋር ግንኙነት በሚያደርጉ አባቶች ውስጥ ከፍተኛ የኦክሲቶሲን መጠን አግኝተዋል ይህም ከልጆቻችን ጋር ከምናሳልፈው ጊዜ መጠን ጋር የሚመጣጠን ይመስላል።

ለምሳሌ፣ ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጨዋታዎችን እና ንክኪዎችን ያደረጉ አባቶች የኦክሲቶሲን መጠን መጨመር አሳይተዋል፤ ተመሳሳይ ለውጥ ደግሞ አባቶች አዲስ የተወለዱ ልጆቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያቅፉ እንኳ በግልጽ ታይቷል።

ኦክሲቶሲን የአባትነት ሰሜታችንን በእጅጉ ያነቃቃዋል። ሪሊንግ እንደሚያስረዱት የወንዶችን አፍንጫ ላይ ሆርሞኑን በመረጨትና የሚፈጠረውን ለውጥ በመመልከት ይህንን ማረጋገጥ ይቻላል።

"በጣም የምወደው አንድ ጥናት አለ" ይላሉ። "አባቶች ከጨቅላ ልጆቻቸው ጋር በሚገናኙበት ወቅት በአፍንጫቸው በኩል ኦክሲቶሲን እንዲተነፍሱ ይደረጋል፤ ይህም አባቶቹ ራሳቸውን ይበልጥ በፍጥነት እንዲያወዛውዙ እንደሚያደርጋቸው ደርሰውበታል። በጣም የተደሰተ አባት በሚመስል ሁኔታ ራሳቸውን ወደ ግራ እና ቀኝ እንዲሁም ወደ ላይ እና ታች በፍጥነት ያንቀሳቅሳሉ።"

እንዲህ ያሉት ውጤቶች ከኦክሲቶሲን ጋር ተያይዞ ራሱን የሚያጠናክር አዎንታዊ የዑደት ሂደት እንዳለ ይጠቁማሉ። የሆርሞኑ መጠን ሲጨምር፣ አባቱ ከልጁ ጋር የመቀራረብ ዕድልን ያሰፋል፤ ይህም ደግሞ የሆርሞኑ መጠን ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል።

ሳይንቲስቶች ወደዚህ ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀት በገቡ ቁጥር በሌሎች ሆርሞኖች ላይም ተጨማሪ ለውጦችን እያገኙ ነው።

በ2025 በታተመ ጥናት ላይ ሪሊንግ እና ቡድኑ እንደደረሱበት፣ ቫሶፕሬሲን የተሰኘው እና በእንስሳት ዘንድ አብዛኛውን ጊዜ ከግዛት ጥበቃ እና በወንዶች መካከል ከሚደረግ ፍልሚያ ጋር የሚያያዘው ሆርሞን፣ አዲስ አባቶች በሚሆኑ ወንዶች ውስጥ ልጆቻቸው ከመወለዳቸው በፊት ቀንሶ ይገኛል።

ሌላው አስገራሚ ሆርሞን ፕሮላክቲን ነው። በሰዎች ዘንድ ይህ ኬሚካል በወተት ምርት እና በእናትነት ክብካቤ ውስጥ ባለው ድርሻ ይታወቃል፤ ነገር ግን የሥነ-ሕይወት ተመራማሪዎች ሆርሞኑን እንደ ወፎች፣ ዓሳዎች እና በሌሎች እንስሳት ውስጥ ከአባትነት እንክብካቤ ጋር አያይዘውታል።

በ2023 በአሜሪካዊቷ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ዳርቢ ሳክስቤ የሚመራ ቡድን፣ የወደፊት አባቶችን የፕሮላክቲን መጠን በመመርመር ገና ላልተወለደ ልጃቸው ጠንካራ ቁርኝት የሚሰማቸው አባቶች ከፍተኛ የሆርሞን መጠን እንዳላቸው ደምድሟል፤ እንዲሁም ከወሊድ በፊት ያለው የፕሮላክቲን መጠን እነዚህ አባቶች በልጆቻቸው ክብካቤ ላይ ምን ያህል ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስቀድሞ የሚጠቁም መሆኑን አረጋግጧል።

ቀደም ሲል በኦክሲቶሲን መጠን ላይ እንዳየነው፣ ሁለቱም የሆርሞን ለውጦች ለሕፃናት ልጆቻቸው ትልቅ እንክብካቤ በሚያደርጉ አባቶች ላይ ይበልጥ ጎልተው ይታያሉ።

ዳርቢ ሲናገሩ "የሆርሞን ለውጥ የሚያጋጥማቸው አዲስ እናቶች ብቻ አይደሉም፤ ወንዶችም ተመሳሳይ ዓይነት የመላመድ ሂደቶች እና ተመሳሳይ ውጤቶች እያሳዩ መሆናቸው እየታየ ነው" ብለዋል።

ሁለተኛው የጉርምስና ዕድሜ

ሳክስቤ የእነዚህ የሆርሞን ለውጦች ውጤቶች በአባቶች አንጎል ላይ አሻራቸውን ያሳርፉ እንደሆነ ሲመረምሩ ቆይተዋል።

"አባቶች ያለ ባዮሎጂካዊ እርግዝና የወላጅነት ሽግግርን ስለሚያጋጥማቸው፣ በእውነቱ በጣም የሚስቡ እና በተለየ ሁኔታ መታየት ያለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

ወላጅ እናቶች ልጆቻቸውን በሚሸከሙበት ወቅት የሆርሞን መጨመር ያጋጥማቸዋል፤ ከዚያም በወሊድ ወቅት ሌላ ተጨማሪ መነቃቃት ያገኛሉ። ነገር ግን የትዳር አጋሮቻቸው የሚያጋጥሟቸው ለውጦች ረቂቅ ናቸው።

"ስለዚህ የእነርሱ ሁኔታ የእርግዝናን ውጤቶች ከወላጅነት ተሞክሮ ውጤቶች ለይተን እንድንመለከት ያስችሉናል" ሲሉ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት "የአባት አንጎል" የተሰኘ መጽሐፍ የሚያሳትሙት ሳክስቤ አስረድተዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የእሳቸው ቡድን በስፔን ከሚገኙ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመተባበር ልጆቻቸው ከመወለዳቸው በፊት እና በኋላ የመጀመሪያ ጊዜ አባቶችን አንጎል በምሥል ማንሻ መሳሪያዎች መርምረዋል። በዚህም በነርቭ ሥርዓት ላይ ለውጦች እየተካሄዱ መሆናቸውን ደርሰውበታል። አንጎላቸው ከአዳዲስ ተሞክሮዎችና መረጃዎች ጋር ራሱን እያላመደ ነበር።

ሳክስቤ ይህንን ወደ አባትነት የሚደረግ ሽግግር ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ያነጻጽሩታል፤ ይህም አንጎላችን ከአዳዲስ ተግዳሮቶች፣ ቀስቃሽ ሁኔታዎች እና ሐሳቦች ጋር ራሱን ማላመድ ያለበት ሌላው ወሳኝ የዕድገት ምዕራፍ ነው።

ባደረጉት ተከታታይ ጥናትም ገና ላልተወለደ ልጃቸው ከፍተኛ ቁርኝት የሚሰማቸው ወይም ረጅም የወላጅነት ፈቃድ ለመውሰድ ያቀዱ ወንዶች በአንጎላቸው ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚታይ ደርሰውበታል።

በ2026 ሪሊንግ በአዲስ አባቶች ላይ ተመሳሳይ የአእምሮ ለውጥ ማስረጃዎችን በማቅረብ ይህንን የነርቭ ሥርዓት ሽግግር አረጋግጠዋል።

በአባትነት አንጎላችን እና አካላችን ላይ እንደሚከሰቱት በርካታ ለውጦች ሁሉ፣ እዚህም ካልተጠቀሙበት የሚያመልጥ ዓይነት ክስተት አለ፤ ይበልጥ በተሳተፉ ቁጥር፣ ለውጡም ያንኑ ያህል ጥልቅ ይሆናል። "ፋዘር ታይም" የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉት የአጥቢ እንስሳት ተመራማሪዋ ሣራ ህርዲ "ልክ አንድ ነገር እንደሚቀሰቀስ ያህል ነው" ይላሉ።

እሳቸው እንደሚያምኑት፣ ሁሉም የሰው ልጅ አንጎል ወላጅ የመሆን የተዳፈነ አቅም አለው፤ ይህንንም "አሎፓሬንታል ሰብስትሬት" ብለው ይጠሩታል።

በ"ፋዘር ታይም" መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከራከሩት፣ የሰው ልጅ ወደ ውስብስብ ማኅበረሰብ እያደገ ሲመጣ እንዲበለጽግ ያደረገው የጋራ ክብካቤ ነው። ለሕፃን ልጅ ዋናውን ክብካቤ መስጠት የሚችሉ ወንዶች መኖራቸው ጠቃሚ በመሆኑ ይህን የማድረግ አቅምን አዳብሮ መዝለቅ ይጠይቃል።

ማኅበራዊ ለውጦች

ያነጋገርኳቸው ባለሙያዎች በሙሉ እና በዚህ ዘርፍ ያሉ አብዛኛዎቹ ጽሑፎች፣ እነዚህ በአባቶች ተፈጥሮ (ባዮሎጂ) ላይ የሚታዩ ለውጦች ቤተሰብን በሚመለከቱ የመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይስማማሉ።

ሳክስቤ "አባቶች እነዚህን ቁርኝቶች እንዲፈጥሩ ዕድል ማመቻቸት አጣዳፊ ማኅበራዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው" ይላሉ። ለምሳሌ የተሻሻሉ የወላጅነት ፈቃድ ፖሊሲዎች በአባቶችና በልጆች መካከል ያለውን ትስስር ሊያሳድጉ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

ሌላው ቁልፍ ለውጥ ወንዶች ገና ከመጀመሪያው እንዲሳተፉ ማድረግ ነው በማለት ጌትለርም ይናገራሉ፤ ይህም በቅደመ ወሊድ ወቅት ምርመራዎችን መከታተልን፣ ወደ ቀጠሮዎች መሄድን እና ከትዳር አጋራቸው ጋር በንቃት መገናኘትን ይጨምራል።

"ቤተሰቦች ሕፃናትን ለመቀበል በሚዘጋጁበት የእርግዝና ወቅት፣ ይህ ሥነ-ሕይወታዊ ሂደት ሊነቃቃ እንደሚችል እናውቃለን" ብለዋል።

ንቁ እና ተሳታፊ የሆኑ አባቶች ለቤተሰብ ጥቅም አላቸው። እንደ ፓኪስታን፣ ኬንያ እና አሜሪካ ባሉ አገራት ውስጥ ንቁ የሆኑ የትዳር አጋሮች ያሉዋቸው እናቶች የተሻለ የአእምሮ ጤና እንዳላቸው ተገልጿል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ልጆቹም ተጠቃሚ ናቸው። በ2026 መጀመሪያ ላይ የታተመ እና ለሰባት ዓመታት 292 ቤተሰቦችን የተከታተለ አንድ ትልቅ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የበለጠ ትኩረት የሚሰጡ አባቶች ያሏቸው ልጆች የተሻለ የልብ ጤና አላቸው። የሚያስገርመው ግን የእናቶች ባሕሪ ያን ያክል ውጤት አልነበረውም።

"የአባትነት ተፈጥሯዊ ስሪት ገና ከጅማሬው ጠንካራ እና ጤናማ ቤተሰቦችን ለመገንባት እንዴት መሠረት እንደሚሆን ማሰብ ይገባል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል ጌትለር።