በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ይደረሳል በሚል ተስፋ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ይፈረማል የሚል ተስፋ በስፋት በመታየቱ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ። የእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ላይም ጭማሪ ታይቷል።
ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሰላም ስምምነቱ ነጥቦች "በአብዛኛው ድርድር ተደርጎባቸዋል" በማለት ዝርዝሩን ይፋ ሳያደርጉ ቀርተዋል።
ሁለቱ አገራት በበርካታ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው ሲገለጽ ቢቆይም ትራምፕ ተደራዳሪዎች ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፈራረም እንዳይጣደፉ አሳስበዋል።
ሰኞ ጠዋት በእስያ ገበያ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ 5.5 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን በአሜሪካ ደግሞ የ5.8 በመቶ ቀንሶ 90.99 ዶላር ተሸጧል።
ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ማስከፈትን የሚያካትት ነው ያሉ ሲሆን ይህም ለወራት መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በነጻነት እንዲጓዙ ያስችላል ተብሎ ነበር።
ጠባቡ የባሕር መተላለፊያ የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበት ሲሆን ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኋላ ተዘግቷል።
ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ኳታር ጋር “በሰላም ስምምነቱ የመግባቢያ ሰነድ” ዙሪያ “ጥሩ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።