ኢዜማ "የሐረሪ ብሔረሰብ አባልነት መስፈርት" በመደረጉ በክልሉ የቀረቡ ዕጩዎች ከምርጫ መሰረዛቸውን ገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በሐረር ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ያቀረበው ተወዳዳሪ "የሐረሪ ብሔረሰብ አባልነትን መስፈርት" ተደርጎ በመቀመጡ ከዕጩነት እንዲሰረዝ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መወሰኑን አስታወቀ።

"የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲ ዕጩዎችም" በተመሳሳይም ምክንያት ከምርጫው መታገዳቸውን የገለጸው ኢዜማ፤ ክስተቱ ዜጎች "አንደኛ እና ሁለተኛ ዜጋ ተደርገው እንደሚታዩ" የሚያሳይ ነው ሲል ኮንኗል።

ኢዜማ ይህንን ወቀሳ ያሰማው ዛሬ አርብ ግንቦት 07/2018 ዓ.ም. በወቅታዊ የምርጫ ጉዳዮች በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ነው።

በዚህ ወር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ 1,249 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጠው ኢዜማ፤ "የምርጫ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎች" ያላቸውን ጉዳዮችን በመግለጫው ዘርዝሯል።

ፓርቲው መግለጫውን ያወጣው "በምርጫው ላይ እያደረግን ባለው ተሳትፎ ከአቅማችን በላይ የሆኑትን ጉዳዮች ለማኅበረሰቡ ማሳወቅ አስፈላጊ በመሆኑ" እንደሆነ ገልጿል።

በፓርቲው መግለጫ ላይ በቀዳሚነት የተቀመጠው በሐረሪ ክልል "በብሔር ማንነት ምክንያት" ተነጥቋል ያለውን "ዜጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት" ጉዳይ ነው።

ፓርቲው "ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩነት ያቀረብነው ተወካያችን እና የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕጩዎች" በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት "ከምርጫው ውጪ እንዲደረጉ ተወስኗል" ብሏል።

ኢዜማ እንደገለጸው፤ ይህ ውሳኔ የተላለፈው የክልሉ ሕገ መንግሥት "ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ የሚወዳደሩ አባላት በምርጫው ለመወዳደር የሐረሪ ብሔረሰብ አባልነትን መስፈርት አድርጎ" በማስቀመጡ ነው።

ምርጫ ቦርድም "በዚህ ዕጩ ፋንታ የመብቱ ባለቤት ከሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ይልቅ ከግለሰቡ ብዙ ማንነት አንዱ የሆነውን የዘውጌ ማንነቱን የሚያሟላ ዕጩ እንድንተካ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ትዕዛዝ ሰጥቶናል" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

ይህ ክስተት "ዜጎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ አንደኛ እና ሁለተኛ ዜጋ ተደርገው እንደሚታዩ በግልጽ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው" ያለው ኢዜማ፤ አሠራሩ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ተቃራኒ መሆኑን አንስቷል።

ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ሕግ ወይም ውሳኔ ተፈጻሚ እንደማይሆን በሚገልጸው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሠረት "ውሳኔውን ለማስቀልበስ እስከ መጨረሻው ሒደት" እንዲሚጓዝ አስታውቋል።

በተጨማሪም ፓርቲው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዕጩዎቹ እና አስተባባሪዎቹ ላይ እስር እና እንግልት መድረሱን በመግለጫው አስፍሯል።

ዕጩዎቹ በምርጫ ቦርድ ግፊት መለቀቃቸውን የጠቀሰው ፓርቲው፤ ሌሎች አባላቶቹ ግን አሁንም እስር ላይ መሆናቸነን ገልጿል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም በፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ላይ ዛቻ እንዲሁም ማስፈራራቶች እየተፈጸሙ መሆኑንም አንስቷል።

"መንግሥት በየሚዲያው በሚያደርገው ዲስኩር የሚገልጸውን ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ በተግባር እንዲያረጋግጥ እና በየደረጃው የሚገኙ ካድሬዎቹን ሀይ እንዲል እናሳስባለን" ሲልም አስጠንቅቋል።

ምርጫ ቦርድም "የማያዳግም እና ቆንጣጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ" እና "በሕገ ወጥ ተግባር የሚሳተፉ የመንግሥት ሹመኞች ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ" ጠይቋል።