ምዕራብ ጎጃም ውስጥ ተመራማሪዎችን በደቦ ጥቃት የገደሉ 32 ሰዎች ተፈረደባቸው

የፍርድ ቤት መዶሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምዕራብ ጎጃም ዞን በምትገኘው ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ውስጥ ለጥናት በሄዱ ተመራማሪዎች ላይ የደቦ ጥቃት በመፈጸም ሕይወት ያጠፉና ጉዳት ያደረሱ ተከሳሾች ተፈረደባቸው።

ጉዳያቸው በባሕር ዳር አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ የቆዩት 32 ተከሳሾች በደቦ ሰው በመግደል፣ በአካል ማጉደል፣ በግድያ ሙከራና ንብረት በማውደም ክስ ነው አርብ ነሐሴ 21/2013 ዓ.ም የእስር ቅጣት የተበየነባቸው።

ከሦስት ዓመት በፊት ጥቅምት 13/2011 ዓ.ም በጎንጂ ቆለላ ወረዳ ውስጥ በተፈጸመው የደቦ ጥቃት የተደገደሉት ሰዎች አንደኛው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ዲግሪ ጥናት ወደ ቦታው ያመራ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሜጫ ወረዳ በሚገኝ ጤና ጣቢያ የሚሰራ የጤና መኮንን ነው።

ከሟቾቹ በተጨማሪ በጥቃቱ ሦስት የጤና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት፣ በአንድ ግለሰብ ላይ የመግደል ሙከራና አንድ ተሽከርካሪ ላይ ደግሞ በእሳት የማቃጠል ጉዳት ደርሷል።

የደቦ ጥቃቱ የተፈጸመው ተመራማሪውና የጤና ባለሙያዎቹ በወረዳው በሚገኘው አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች ላይ ለጥናት የሚያስፈልገውን የምርምር ናሙና ሽንትና ሰገራ በፈቃደኝነት ከተመረጡ ልጆች ላይ እየሰበሰቡ በነበረበት ጊዜ ነበር።

በወቅቱ በአካባቢው ተመራማሪዎቹ "ልጆቻችንን የማይታወቅ መርፌ በመውጋት እየመረዙብን ነው፣ ሊገድሉብን ነው" የሚል ሐሰተኛ ወሪ ለተማሪዎቹ ወላጆች በመድረሱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ግለሰቦች ወደ ትምህርት ቤቱ በማምራት ችግር መፈጠሩን የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የተከሰተው ግርግር ከፀጥታ አስካበሪዎች አቅም በላይ ሆኖ በሐሰተኛ ወሬ ተደናግጠው ከተገኙት ሰዎች መካከል በባለሙያዎቹ ላይ በዱላና በድንጋይ በደቦ በተፈጸመ ጥቃት የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ደርሷል።

በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው እነመላኩ አበበ በሚል የክስ መዝገብ 32 ተከሳሾች በባሕር ዳር ከተማና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቶ ውሳኔ ተሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን በደቦ ጥቃቱ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት 32 ተከሳሾች ውስጥ በወንጀሉ እንደነበራቸው ተሳትፎ ከአንድ ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ የጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፈርዷል።

ከእነዚህ በተጨማሪ አምስት ግለሰቦች በደቦ ጥቃቱ ውስጥ ስለነበራቸው ተሳትፎ ማስረጃ ባለመቅረቡ ቀደም ሲል በነጻ እንደተለቀቁ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።