በዩኬ እና አውሮፓ ሚሊዮኖች በሕይወት ዘመን አንዴ የሚከሰት የፀሐይ ግርዶሽ ተመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትናንት ረቡዕ በ30 ዓመታት ውስጥ ከነበሩት በተለየ ሁኔታ አስደናቂ የሆነ የፀሐይ ግርዶሽ በዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ አገራት ታይቷል።
በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ይህ በትውልድ አንድ ጊዜ የሚከሰት የፀሐይ ግርዶሽ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም አመሻሽ ላይ ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ መታየት ከጀመረ በኋላ በሒደት 90% የፀሐይ ክፍል በጨረቃ ተሸፍኗል።
የግሪንላንድ፣ አይስላንድ እና ስፔን አንዳንድ አካባቢዎች በሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ምክንያት በጨለማ ተውጠዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ አገራት ነዋሪዎች በብዛት ተሰብስበው ክስተቱን በደማቅ ሁኔታ ተከታትለዋል።
ሥነ ከዋክብት ወዳጆች ዓለማችን ምን ያህል "ድንቅ" እንደሆነች የሚያሳይ ክስተት ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ጠቅላላው የፀሐይ ግርዶሽ መነሻው በሰሜናዊ ሩሲያ የሚገኘው ሳይቤሪያ ነው። ይህም ከቴሌስኮፕ የራቀ ቢሆንም ቀስ ቀስ ግርዶሹ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ተሻግሯል።
የፀሐይ ግርዶሹ አይስላንድ ከደረሰ በኋላ ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ ተጉዞ በዩናይትድ ኪንግደም ታይቷል።
በሰሜን ስኮትላንድ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ ታይቷል። በማዕከላዊ እና ደቡባዊ እንግሊዝ እና ዌልስ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጨረቃ ቀስ በቀስ ፀሐይን ሸፍናለች።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ብዙዎች የፀሐይ ግርዶሽ መመልከቻ መነጽር እየሸመቱ ስለነበር ገበያው ላይ እጥረት አጋጥሟል።
መነጽሩን ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች በካርቶን እና ሌሎችም ቁሳቁሶች መነጽር ሠርተው የፀሐይ ግርዶሹን ተመለክተዋል።
በዩኬ ቀጣዩ የጨረቃ ግርዶሽ በ2081 የሚከሰት ይሆናል። በዚህ ወቅት 99% ግርዶሽ ይፈጠራል። ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚከሰተው ደግሞ በ2090 ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፀሐይ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ በፀሐይ እና በመሬት መካከል ስትገባ ነው። ጨረቃ የፀሐይን ጨረር ስትጋርድ የሚፈጠረው ጥላ እና ጨለማ መሬት ላይ ይታያል።
ጨረቃ ፀሐይን የምትጋርደው ቀስ በቀስ ነው። ትናንት በዩኬ በታየው የፀሐይ ግርዶሽ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና መሬት በአንድ ቀጥተኛ መስመር ላይ አልነበሩም።
ስለዚህም ጨረቃ ፀሐይን የጋረደችው 90% ብቻ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Cesar Manso/AFP/Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም በአውሮፓውያኑ 1999 የፀሐይ ግርዶሽ 95% ነበር።
በስፔን ትናንት የታየው የፀሐይ ግርዶሽ ልዩ ነበር። ፀሐይ፣ ጨረቃ እና መሬት በአንድ ቀጥተኛ መስመር ላይ በመገናኘታቸው ሙሉ ግርዶሽ ተፈጥሯል።
ክስተቱን ለማየት ረዥም ርቀት ተጉዛ ስፔን የተገኘችው ቺሊያዊ ሳይንቲስት ያዝሚን ካርሪቾ "የፀሐይ ግርዶሹ ሙሉ ሲሆን ሁሉም ሰው ደስታውን እየገለጸ ነበር። ስሜቱን ቃላት አይገልጹትም" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Ina Fassbender/AFP/Getty Images
የፀሐይ ግርዶሽ በአንድ የዓለም ክፍል በ18 ወራት ውስጥ ይከሰታል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ግን እስከ 400 ዓመታት ሳይታይ ሊቆይ ይችላል።
በስፔን በሙሉ ግርዶሽ ምክንያት ፀሐይ ከጨረቃ ጀርባ ሆነ ነጸብራቋን ስትለቅቅ ታይቷል።
ይህ ብርሃን ፀሐይ የምትለቅቀው እና በሺህ ማይሎች ሕዋ ላይ የሚፈነጥቀው ጋዝ (corona) ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
በሒደት ጨረቃ ዘወር ስትል የፀሐይ ሙሉ ብርሃን ይታያል። አጠቃላይ ግርዶሹ 2 ደቂቃ ቆይቷል።
ፀሐይ ከመሬት 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ትርቃለች። ከጨረቃ 400 እጥፍ ርቃም ትገኛለች።
ከአውሮፓውያኑ 2026 እስከ 2028 ያሉት ዓመታት የፀሐይ ግርዶሽ "ወርቃማ ዘመናት" ይባላሉ።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ሦስት ሙሉ የፀሐይ ግርዶሾች እንደሚከሰቱ ይጠበቃል።















