የዴሞክራቲክ ኮንጎ ኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን ከታዩት እጅግ የከፋው ለመሆን መቃረቡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተነሳው ኢቦላ ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን የከፋ ወረርሽኝ ለመሆን መቃረቡን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ተናገሩ።
ወረርሽኙ አሁን ላይ እየተስፋፋበት ያለው መጠን ከዚህ ቀደም ከነበሩት በበለጠ የከፋ ለመሆን መቃረቡን ገልጸዋል።
የዘንድሮው ወረርሽኝ "እየተስፋፋበት ያለው መጠን" ከዚህ በፊት በአውሮፓውያኑ ከ2014 እስከ 2016 የነበረውን ስርጭት "እንደሚልፍ" ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ አስታወቀዋል።
ከ2014 እስከ 2026 ባሉት ዓመታት በኢቦላ ምክንያት 11,000 ሞተዋል።
በያዝነው ዓመት ግንቦት 15 በይፋ የታወጀው የኢቦላ ወረርሽኝ ቢያንስ 2,000 ሰዎችን ለሕልፈት ዳርጓል። ቢያንስ 4,300 ሰዎችም በቫይረሱ ተይዘዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በሦስት ወራት ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀልበስ ተስፋ አድርጓል። ይህ ግን ማለት የቫይረሱን ስርጭት መቀነስ እንጂ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ መግታት እንዳልሆነ አስጠንቅቋል።
ግንቦት ላይ ወረርሽኙ በይፋ ቢታወጅም ስርጭቱ የተጀመረው ሦስት ወራት ቀድሞ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ጃባኒ ከወረርሽኙ ማዕከል በቅርብ ርቀት በሚገኘው ቡኒያ ከተማ በሰጡት መግለጫ "ቫይረሱን እያሳደድን ነው፤ ቫይረሱ ግን ቀድሞናል" ብለዋል።
ቫይረሱ ጥር ላይ መሰራጨት እንደጀመረ እና በስህተት ወባ ወይም ታይፎይድ ነው ተብሎ እንደታሰበ የሚያሳይ ጥናትን አጣቅሰዋል።
አሁን ላይ እየተሰራጨ የሚገኘው የኢቦላ ቫይረስ 'ቡንዲቡግዩ' የተባለው ዝርያ ሲሆን ከዚህ በፊት በ2007 እና በ2012 ተቀስቅሷል።
እስካሁን ድረስ ለዚህ የቫይረሱ ዝርያ የሚሆን ክትባት ወይም የሚታወቅ ማገገሚያ መድኃኒት የለም።
በዲሞክራቲን ኮንጎ ወረርሽኙ በተነሳበት አካባቢ ያለው ግጭት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አስተጓጉሏል።
ዶ/ር መሐመድ እንደሚናገሩት የጤና ባለሙያዎች ከአካባቢው መሸፈን የቻሉት 30% ብቻ ነው።
በኢቦላ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ከሁለት እስከ 12 ቀናት ባለው ጊዜ ምልክት ያሳያሉ።
ከጉንፋን እና ወባ ጋር የሚመሳሰል ምልክት ያለው ገዳይ ቫይረስ ነው። ድንገተኛ የሆነ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና ድካም ከምልክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ቫይረሱ እየጠነከረ ሲሄድ ማስመለስ፣ ማስቀመጥ እና የሰውነት ክፍሎች ሥራ ማቆም ይከተላል።
እንደ ደም ባሉ ከሰውነት የሚወጡ ፈሳሾች አማካኝነት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።
የዩናይትድ ኪንግደሙ መድኃኒት ተቆጣጣሪ ኤምኤችአርኤ፤ ቡንዲቡግዩ ለተባለው የኢቦላ ዝርያ የተዘጋጀ ክትባት በሰዎች ላይ ሙከራ እንዲደረግበት ፈቅዷል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች የተመረተው ክትባቱ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተዘጋጀው አስትራዜኒካ ክትባት ጋር በሚመሳሰል ቴክኖሎጂ ነው የተሠራው።
የዓለም ጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ለሚደረግ የክትባት ሙከራም ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።















