በኤሌክትሪካል ምህንድስና 47 ትምህርቶችን 'ኤ ፕላስ' ያመጣችው ሩት አባተ

ሩት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸልማለች

የፎቶው ባለመብት, Ruth Abate

የምስሉ መግለጫ, ሩት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸልማለች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የኤሌክትሪካል ምህንድስና ተመራቂ የሆነችው ሩት አባተ 47 ትምህርቶችን ኤ ፕላስ (A+) አምጥታለች።

የወርቅ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚዋ ሩት በዩኒቨርስቲው ታሪክ '4' በማምጣት "የመጀመሪያዋ ሴት" መሆኗ ስኬቷን "ታሪካዊ" እንዳደረገው ለቢቢሲ ተናግራለች።

የኮሌጁን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸልማለች። በትምህርት ክፍሉ ካሉ የዘንድሮ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ደግሞ ዋንጫ ተበርክቶላታል።

እጅግ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የማዕረግ ተሸላሚ ከመሆኗ በተጨማሪ በኮሌጁ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ሴት ናት።

ሩት በደስታ ሳቅ በታጀበ ድምጽ "ከሽልማቶቹ በሙሉ ደስ ያለኝ ዋንጫው ነው፤ ትልቁ ሽልማት ነው፤ የተሰጠበት መንገድም ልዩ ክብር አለው" ትላለች።

"ዋንጫ መሆኑም የበለጠ አስደሳች ያደርገዋል" ስትልም ስሜቷን ትገልጻለች።

ሩት በኤሌክትሪካል ምህንድስና 60 ኮርሶች ወስዳ 47ቱን 'ኤ ፕላስ' ስታመጣ የቀሩትን 13 ኮርሶች 'ኤ' አምጥታለች።

". . .ቢ እና ሲ አናውቃቸውም" ትላለች።

'ኤ ፕላስ' የማምጣት ያህል ባይሆንም 'ኤ' ስታገኝም "እንደምትቀበለው" የምትናገረው ሩት "ኤ ማይነስ" ማምጣት በውጤት ዝርዝሯ እንደሌለ ሳትጠቅስ አታልፍም።

"ጓደኞቼ ሁሉንም 'ኤ ፕላስ' እንደማመጣ ነበር የሚጠብቁት።"

ክፍል ውስጥ "ሩት ከገባት በቃ እሷ ታስረዳናለች" የምትባለው ተማሪ ናት።

ከድሮም ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። አምስተኛ ክፍል ስትገባ ግን ጎበዝነቷን በደንብ ማስተዋል ጀመረች።

"ሰነፍ ነኝ፣ አልችልም የሚል ነገር ውስጤ የለም።"

ከድሮም ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ የነበረችው ሩት "ሰነፍ ነኝ፣ አልችልም የሚል ነገር ውስጤ የለም" ትላለች

የፎቶው ባለመብት, Ruth Abate

የምስሉ መግለጫ, ከድሮም ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ የነበረችው ሩት "ሰነፍ ነኝ፣ አልችልም የሚል ነገር ውስጤ የለም" ትላለች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ውጤት ካመጡ የ12ኛ ክፍል ተሸላሚዎች መካከል አንዷ ነበረች።

"እንደ ትምህርት ቤት ወደ 15 ሺህ ብር እና ዋንጫ ተሸልመናል። ትልቅ ብር ነው። መድረክ ላይ ወጥቶ መቀበል ክብር ይሰጣል።"

ሽልማቱን ያበረከቱላት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ "ጠንካራ እንድትሆን" እንደነገሯት እና ይህም ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ታስታውሳለች።

ሩት በጣም የምትወደው ትምህርት ሒሳብ ነው። የኤሌክትሪካል ምህንድንስና ትምህርቶችም ያስደስቷታል።

"ሒሳብ ለብዙዎች አስፈሪ ቢመስልም፤ ሲታወቅ እና ተሠርቶ መልስ ሲገኝ ያለው ስሜት ደስ ይለኛል።"

ለብዙዎች ሒሳብ ከባድ ቢመስልም "ለእኔ ቀላል ነው" ስትል ትገልጻለች።

"የሆነ መንገድ ማወቅ ነው። መሸምደድ፣ ቲዮሪ የለውም።"

ሩት ትኩረት ማድረግ እንደምትችልም ትናገራለች። የሆነ ነገር እሠራለሁ ካለች እንደምትሠራው ትገልጻለች።

እንዲያውም "ሻይ ቡና እያለችም" ማጥናች ትችላለች።

ሩት የስኬታማነቷ ምሥጢር ላለፉት አምስት ዓመታት "ያለማቋረጥ ማንበቧ" እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ይህ ማለት ግን አትዝናናም ማለት አይደለም። ማጥናት እና ለስምንት ሰዓት እንቅልፍ ማግኘት እንዳለ ሆኖ ፊልምም ታያለች።

"አልጋዬ ላይ ሆኜ ፊልም ማየት ደስ ይለኛል፤ ያዝናናኛል። በቀን አምስት ስድስት ኤፕሶድ [ክፍል] ማየት ደስ ይለኛል። እስካሁን ካየኋቸው ፊልሞች 'ጌም ኦፍ ትሮንስ' ደስ ይለኛል።"

ሩት ጊዜዋን በአግባቡ ትጠቀምበታለች። ማንበብ ከጀመረች አንዳችም የሚያሰናክላት ነገር አይኖርም።

ለፈተና ተገቢውን ዝግጅት ታደርጋለች። ማንበብ ስትጀምር ትኩረቷን ትሰበስባለች።

ተማሪዎች ጎበዝ እንዲሆኑ ተፈጥሮ ሊያግዝ ቢችልም 90 በመቶው የስኬት ምሥጢር "ጥረት ነው" ብላ ታምናለች።

መምህራን ፈተና እንዳለ ሳይነግሯቸው ሊፈትኗቸው ስለሚችሉ ሁሌም ዝግጁ ሆና እንደምትጠብቅ ትገልጻለች። ውጤቷን ለማስጠበቅ ያለመታከት መሥራቷንም ትናገራለች።

ዩኒቨርስቲ ስትገባ ስኬታማ የመሆን ግብ አንግባ ነው። በቤተሰብ ጫና ወይም 'መደረግ ያለበት' ስለሆነ ሳይሆን ግቧን ለማሳካት ወስና ትምህርቷን መጀመሯን ታስታውሳለች።

አሁን ላይ ብዙዎች 'ትምህርት ተስፋ የለውም' ብለው ሲያቋርጡ፣ አንዳንዶችም ቲክቶከር መሆንን ሲመርጡ ይስተዋላል።

ሩት "ልክም ነው፣ ልክም አይደለም አልልም" ትላለች።

ለእሷ የዩኒቨርስቲ ዲግሪ ግቧ እንደሆነ ሁሉ፤ ቲክቶከር ሆኖ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልግም መንገዱን መከተል እንደሚችል ታምናለች።

"የሕይወት ግብን ማወቅ" ዋነኛው ነጥብ እንደሆነ ትናገራለች።

ሩት ስኬታማ እንድትሆን እናት እና አባቷ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ትናገራለች

የፎቶው ባለመብት, Ruth Abate

የምስሉ መግለጫ, ሩት ስኬታማ እንድትሆን እናት እና አባቷ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ትናገራለች

ኤሌክትሪካል ምህንድስና ለመማር የመረጠችው "ሕይወትን ስለሚያቀል" እንደሆነ ትናገራለች።

የሰዎችን ሕይወት ቀላል ማድረግ ዓላማዋ ነው።

". . .ይሄን ሁሉ 'ኤ' አመጣች ከሚባለው ባለፈ፤ የማኅበረሰቡን ሕይወት ቀላል የሚያደርግ ነገር ብሠራ ደስ ይለኛል።"

ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ሲገቡ የሚያገኙትን ነጻነት በአግባቡ ባለመጠቀም የወደፊት ሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ታምናለች።

ሩት ስኬታማ እንድትሆን እናት እና አባቷ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ትናገራለች።

በቀጣይ ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር አስባለች።

"ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ማስተርሴን ብቀጥል ደስ ይለኛል። የውጭ የትምህርት ዕድልም እየሞከርኩ ነው። ስኬት የዓመታት ጠንካራ ሥራ ውጤት ነው።"