በአሳማ ሥጋ ምክንያት የሚፈጠረው ብዙም የማይታወቀው ከባድ የሚጥል ሕመም

ሎውሪ ዴንማን
የምስሉ መግለጫ, ሎውሪ ዴንማን በዩናይትድ ኪንግደም በየዓመቱ የአንጎል ኢንፌክሽን ከሚገኝባቸው ጥቂት ሰዎች አንዷ ናት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ሎውሪ ዴንማን አንዳች ክፉ ነገር እንደገጠማት ያወቀችው አንድ ሜትር የሚረዝም የኮሶ ትል ከሰውነቷ መውጣቱት ስትመለከት ነበር።

መጸዳጃ ቤት ሳለች የተመለከተችው የኮሶ ትል "እጅግ አስቀያሚ" እንደነበር ትናገራለች።

"እጅግ ያስቀይማል። እንደ ፕላስተርም ይመስላል" ትላለች የ42 ዓመቷ ሎውሪ።

በዩናይትድ ኪንገደም ዌልስ የምትኖረው ሎውሪ ያየችው ምልክት አንጎሏ በጥገኛ ሕዋሳት የመወረሩ (neurocysticercosis) ማሳያ ነበር።

በአንጎሏ ውስጥ 38 ጥገኛ ሕዋሳት (parasites) መገኘታቸው ከፍተኛ ራስ ምታት፣ ራስን አስቶ የሚጥል በሽታ እና ከልክ ያለፈ መንቀጥቀጥ ወይም ቅዠት አስከትሏል።

ሎውሪ ዴንማን በዩናይትድ ኪንግደም በየዓመቱ የአንጎል ኢንፌክሽን ከሚገኝባቸው ጥቂት ሰዎች አንዷ ናት።

ይህ የአንጎል ኢንፌክሽን የሚከሰተው የአሳማ ሥጋ በመመገብ ወደ ሰውነት የሚገባው የኮሶ ትል ዓይነት (pork tapeworm) ዕጭ ደረጃ ላይ ሳለ (larvae) ነው።

ሎውሪ ለማገገም ዓመታት ወስዶባታል። ያለፈችበት ውጣ ውረድ ለሌሎች አስተማሪ እንዲሆን ትፈልጋለች።

ስለ ሕመሙ ግንዛቤ መፍጠር እንደምትሻ ትናገራለች።

ሎውሪ ከበሽታው ለማገገም ዓመታት ወስዶባታል

የፎቶው ባለመብት, Lowri Denman

የምስሉ መግለጫ, ሎውሪ ከበሽታው ለማገገም ዓመታት ወስዶባታል

ሎውሪ በአውሮፓውያኑ 2007 ለሦስት ወራት ሽርሽር ወደ ሕንድ ሄዳ ነበር። ኢንፌክሽኑ የገጠማት ሕንድ ሳለች እንደሆነ የተላላፊ በሽታዎች እና ማይክሮ ባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ብሬንዳን ሄይሊ ይናገራሉ።

በሕንድ ቆይታዋ የምግብ መመረዝ እንዳያጋጥማት በሚል ሥጋ መመገብ አቁማ ነበር።

ዶ/ር ብሬንዳን እንደሚሉት ሎውሪ የኮሶ ትል እንቁላል ያለበት የአሳማ ሥጋ ተመግባለች።

ሎውሪ ጥገኛ ሕዋሱን የተመለከተችው ከሕንድ ጉዞዋ ከሦስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2010 ነበር።

በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ በሚገኝ መጸዳጃ ቤት ሳለች ነበር ጥገኛውን ትል የተመለከተችው።

የሰገራ ምርመራ ስታደርግ ምንም ስላልተገኘ መደበኛ ሕይወቷን ቀጠለች።

ይህ በሆነ በዓመቱ ከፍተኛ የራስ ምታት ያሰቃያት ጀመር። በ2011 ለመጀመሪያ ጊዜ ራሷን ስታ ወደቀች።

"መናገር አቅቶኝ ነበር። ከዚያም እራሴን አምቡላንስ ውስጥ አገኘሁት። ምንድን ነው የተፈጠረው? ለምን ይህ ሆነ? ብዬ እራሴን እጠይቅ ጀመር።"

ካት ስካን እና ኤምአርአይ ከተነሳች በኋላ ውጤቷን ለመቀበል ወደ ሆስፒታል አቀናች።

"ዶክተሩ አንጎሌ ውስጥ 38 ጥገኛ ሕዋሳት መገኘታቸውን ነገረኝ። ዜናውን ስንሰማ እኔ እና እናቴ በጣም ደነገጥን። ምንድን ነው? ብለን ጠየቅን" ትላለች።

ኢንፌክሽን ካለባቸው ድመቶች ሰገራ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚከሰት (toxoplasmosis) እንደሆነ አስበው ነበር።

የሎውሪ እናት ከአንድ ዓመት በፊት ልጃቸው ራሷን መሳቷን በማስታወስ ከኮሶ ትል ጋር የሚያያዝ ችግር እንደሆነ ጠየቁ።

ተጨማሪ ምርመራ ከተደረገ በኋላ አንጎል በጥገኛ ሕዋሳት ሲወወር የሚፈጠር ሕመም (neurocysticercosis) እንደተገኘባት ተገለጸላት።

"በወቅቱ በጤናዬ ላይ ምን እንደተከሰተ ስላላወቅኩ ብዙ ጥያቄ ነበረኝ" ትላለች ሎውሪ።

በአንጎሏ ውስጥ የተገኘው የኮሶ ትል ዝርያ (Taenia solium) በመላው ዓለም ያለ ሲሆን፣ በላቲን አሜሪካ፣ ደቡብ እስያ፣ ደቡብ ምሥራቅ እስያ እና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በስፋት ይገኛል።

የንጽሕና ጉድለት ጥገኛ ነፍሳቱ እንዲስፋፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይም ከአሳማ ጋር ንክኪ ባላቸው አካባቢዎች በብዛት እንደሚስተዋል የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ተቋም (ሲዲሲ) ይገልጻል።

ሎውሪ ዴንማን

የፎቶው ባለመብት, Lowri Denma

የምስሉ መግለጫ, ሎውሪ ዴንማን

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም ወደ 8.3 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው የሚያዙ ሲሆን፣ ምልክት የሚያሳዩ እና የማያሳዩም ይገኙበታል።

በሽታው በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ራስን ስቶ ለመውደቅ በማጋለጥ ይታወቃል።

የአሳማ ሥጋ በመመገብ ወደ ሰውነት የኮሶ ትል ሲገባም በቀጥታ አንጎል ውስጥ ጥገኛ ነፍሳት አያስከትልም።

በማይክሮስኮፕ የሚታዩ የኮሶ ትል እንቁላሎች ሰገራ ውስጥ ይገኛሉ። ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጅን በአግባቡ አለመታጠብ እንቁላሉ ወደ ምግብ እና መጠጥ ተሻግሮ ወደ ሰውነት እንዲገባ ያደርጋል።

እንቁላሉ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ዕጭ ደረጃ ይሻገራል። ጡንቻ፣ ልብ እና ዐይንን ጨምሮ ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይስፋፋል። ይህም በሽታውን ያስከትላል።

ጥገኛ ነፍሳት ወደ አንጎል ሲሻገሩ በሽታው የከፋ ደረጃ ደርሷል ማለት ነው።

ሎውሪ ሆስፒታል ለሁለት ሳምንታት ተኝታለች። ፀረ ጥገኛ ነፍሳት መድኃኒት እና አበረታች መድኃኒት ወስዳለች።

ለዓመታት ጤነኛ ሆና አንድ ቀን ሥራ ላይ ሳለች ራሷን ስታ ወደቀች።

ከዚያም ሰውነቷ ላይ ድካም እና መኮርኮር ተሰማት። ሥራ አቁማ ከአባቷ ጋር መኖር ጀመረች።

ዶ/ር ብሬንዳን እንደሚሉት ሎውሪ የኮሶ ትል እንቁላል ያለበት የዓሳማ ሥጋ ተመግባለች
የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ብሬንዳን እንደሚሉት ሎውሪ የኮሶ ትል እንቁላል ያለበት የዓሳማ ሥጋ ተመግባለች

የተሰጣት አበረታች መድኃኒት የሰውነት ክብደቷ እንዲጨምር አድርጓል።

"የመንቀጥቀጥ እና የመቃዠት ስሜቱ መጣ። ከፍተኛ ጭንቀት ነበረኝ። ስድስት ሳምንት ሆስፒታል ተኛሁ። ቤተሰቦቼ እንዴት ነገሮች ከቁጥጥር ወጡ ብለው ተጨነቁ።"

ጤናማ ሆና ወደ ሥራ ለመመለስ ዓመታት ወስዶባታል። በአውሮፓውያኑ 2022 ሥራ ጀምራለች።

ዶ/ር ብሬንዳን እንደሚሉት፤ የሎውሪ የጤና ቀውስ በረዥም ጊዜ አንዴ የሚገጥም ስለሆነ በአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ባለሙያዎች መማማሪያ አድርገውታል።

"እንዲዚህ ያለ ነገር የማይገጥማቸው የተላላፊ በሽታ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው። የተለየ ክስተት ነው" ይላሉ።

ከዓመታት ትግል በኋላ ጥገኛ ተህዋሳቱ ከሎውሪ አንጎል ተወግደዋል።

ከአንጎሏ ተህዋሲያኑን ለማስወገድ ቀዶ ሕክምና አላደረገችም።

ዶክተሩ እንደሚሉት የተህዋሱን እንቁላሎች ለመግደል መድኃኒት ሰጥተዋታል።

"በሕክምና እንቁላሎቹ በአጠቃላይ ሞተዋል" ይላሉ።

ከ2017 ጀምሮ ራሷን ስታ ባትወድቅም የዕድሜ ልክ መድኃኒት ትወስዳለች።

ያለፈችበት ስቃይ ለሌሎች መማሪያ ሆኖ አወንታዊ ውጤት እንዲኖረው ትመኛለች።

"አሁን ሕይወቴን በጥሩ ሁኔታ መቀጠል ነው የምፈልገው። ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲፈጠር እሻለሁ። በሕይወት በመኖሬ ደስተኛ ነኝ። ጤነኛ ነኝ፤ ሰውነቴ ጥሩ አቋም ላይ ነው። ይሄንንም በቀላሉ አልመለከተውም።"