በድንገተኛው ጎርፍ አደጋ በኔፓል ብቻ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 469 መሆኑ ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኔፓል እና ቲቤት ድንበር ላይ በተከሰተው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ እስካሁን በኔፓል በኩል ብቻ ቢያንስ 469 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደጠፉ ናቸው።

አደጋው ከተከሰተ ከሁለት ቀናት በኋላም የፍለጋ ሥራው የቀጠለ ሲሆን፣ ሌላ ጎርፍ ይከሰታል በሚል ስጋት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በጭንቀት ውስጥ ናቸው።

ሆኖም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋው በደረሰባቸው ስፍራዎች ሁሉ ተሰማርተው ፍለጋቸውን ሲቀጥሉ፣ የጠፉ ሰዎችን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎችን ወዳጅ ዘመዶቻቸው በጭንቀት እየጠበቁ ይገኛሉ።

በትሪሹሊ የውሃ ኃይል ማመንጫ ዋሻ ውስጥ የጠፉ ሰዎችን ለመፈለግ የኔፓል ጦር ሁለት ሄሊኮተሮችን አሰማርቷል።

በትናንትናው ዕለት ሠራተኞችን እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ጨምሮ በዋሻው ውስጥ የነበሩ በርካታ ሰዎችን ማውጣት መቻሉን ጦሩ አስታውቋል። ይሁን እንጂ በስፍራው የቀሩ ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ አልታወቀም።

በቻይናዋ ራስ ገዝ አስተዳደር ቲቤት ደግሞ 3 ሰዎች ሲሞቱ ከ550 በላይ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

ሁለተኛ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት፣ አደጋው ክፉኛ ባጠቃው በኔፓል ግዛት የጠፉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ያሉ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሥራቸውን አቋርተዋል።

በቻይና እና ኔፓል ድንበር ላይ የተፈጠረው መጠኑ እየጨመረ ያለ ሐይቅ ፈንድቶ ሌላ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል በሚል ተሰግቷል።

በቲቤት የተሰማሩ የቻይና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ የሐይቁ ዳርቻዎች ተንዶ ድጋሚ የከፋ ጎርፍ ሊከሰት ይችል እንደሆነ ትናንት ጥናት ሲያደርጉ ውለዋል።

በተፈጠረው ስጋት ምክንያትም በቲቤት የተሰማሩ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ተደርጓል።

በሐይቅ መልክ የተከማቸው ውሃ ረግቶ እንዲቆይ ማድረግ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ቀዳሚው ርምጃ መሆኑን የቻይና ባለሥልጣናት ለአገሪቱ ሚዲያ ተናግረዋል።

የቻይና የውሃ ሀብት ሚኒስቴር የውሃውን መጠን ከለካ በኋላ፥ በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናም በመቀጠሉ ምክንያት በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ውስጥ ሐይቁ ሊፈነዳ የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን አስታውቋል። በዚህም ምክንያት በአደጋው የጠፉትን ሰዎች በመፈለግ ላይ የነበሩ ሠራተኞች ሥራውን እንዲያቆሙ ተነግሯቸዋል።

በቲቤት ከጠፉት ከ550 በላይ ሰዎች ውስጥ 260ው የውጭ ዜጎች ናቸው።

አስከፊው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ተከሰተው ረቡዕ ዕለት በቲቤት በኩል ያለ የበረዶ ግግር መናዱን ተከትሎ ነው።

አደጋው የተከሰተበት የኔፓል-ቲቤት ድንበር በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን የሚያስተናግድ አካባቢ ነው።