የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 11 አትሌቶች ዜግነታቸውን ወደ ቱርክ እንዳይቀይሩ ከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም አትሌቲክስ 11 ስመጥር አትሌቶች ዜግነታቸውን ወደ ቱርክ ለመቀየር ያቀረቡትን ማመልከቻ ውድቅ አደረገ።
አትሌቲክስን የሚያስተዳድረው አካል የቀረበለትን ጥያቄ መንግሥታት "የሌላ አገር አትሌቶችን በአማላይ ስምምነቶች" ለመመልመል የሚያደርጉት "የተቀናጀ ስልት አካል ነው" ብሏል።
11 ዝነኛ አትሌቶች የተውጣጡት አምስቱ ከኬንያ፣ አራቱ ከጃማይካ፣ አንድ ከናይጄሪያ እና አንድ ከሩሲያ ናቸው።
የኬንያ የቀድሞ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ብሪጅድ ኮስጌ እንዲሁም እአአ በ2024 ለጃማይካ በኦሎምፒክ በዲስከስ ውድድር ወርቅ ያስገኘው ሮጄ ስቶና ይገኙበታል።
ቱርክ በ2024 በፓሪስ በተካሄደው ውድድር ካገኘችው ስምንት ሜዳሊያዎች ውስጥ አንድም ወርቅ የለበትም።
የዓለም አትሌቲክስ አትሌቶቹ ዜግነታቸውን እንዲቀይሩ መፍቀድ "የዓለም አትሌቲክስ የብቁነት እና የዝውውር ደንቦችን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ይጥሳል እና ይጋጫል" ብሏል።
በተጨማሪም ማመልከቻዎቹ "ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ባለቤትነት በተያዘ እና በገንዘብ በሚደገፍ ቡድን" አማካኝነት "ዝውውርን ለማመቻቸት እና እነዚያ አትሌቶች በ2028 የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ጨምሮ ወደፊት በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ቱርክን እንዲወክሉ ለማስቻል" የቀረበ መሆኑን ገልጿል።
አክሎም "በማመልከቻዎቹ ውስጥ ያሉትን የተለመዱ ጠባዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኮሚቴው በጋራ ገምግሞ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ከደንቦቹ ዋና መርሆዎች ጋር የማይጣጣም መሆኑን ወስኗል።
"በውሳኔዎቹ ምክንያት አትሌቶቹ በብሔራዊ ውድድሮች ወይም በሌሎች ተዛማጅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ቱርክን ለመወከል ብቁ አይደሉም።"
ሌሎቹ ዜግነታቸውን ለመቀየር የጠየቁ አትሌቶች ካትሪን ሬሊን አማናንግኦሌ፣ ብሪያን ኪቦር፣ ሮናልድ ክዌሞይ እና ኔልቪን ጄፕኬምቦይ ከኬንያ፣ ጃማይካዊውያኑ ራጂንድራ ካምቤል፣ ጄይደን ሂበርት እና ዌይን ፒንኖክ እና ናይጄሪያዊቷ ፋቮር ኦፊሊ እና ሩሲያዊቷ ሶፊያ ያኩሺና ናቸው።















