ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያዎች እንደ ኢትዮጵያ "አቅም ባላቸው" አገራት መጠበቅ እንዳለባቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, abiy ahmed ali/youtube
"ትናንሽ አገራት" ወሳኝ የባሕር መተላለፊያዎችን "መጠበቅ ስለማይችሉ" እንደ ኢትዮጵያ አይነት "አቅም ያላቸው" አገራት ሊሳተፉ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ "በተቻለ መጠን በሰላም" ሊፈታ የሚገባ፤ ነገር ግን "የግድ መሆን ያለበት" ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቲቪ ጋር ባደረጉት በሁለት ክፍል የተላለፈ ቃለ መጠይቅ ላይ ነው። ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ.ም. የመጨረሻው ክፍል የተላለፈው ይህ ቃለ መጠይቅ በአብዛኛው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ አገር መሆኗ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ምን አይነት ጫና እንዳስከተለ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ኢትዮጵያ ዜጎቿን በበቂ መግባ፣ ራሷን ችሏ፣ በዓለም ተወዳድራ፣ የላቀች ዓለም ለመሆን ካሉብን ማነቆዎች ትልቁ ችግር ወደብ አልባነት ነው" ሲሉ መልሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የባሕር በር አልባነት መፍትሔ ሊያገኝ የሚገባ "የሕልውና ጉዳይ" እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ዐቢይ በፓርላማ ማብራሪያዎቻቸው እና በሌሎች ንግግሮቻቸው በተደጋጋሚ ያነሱ ጉዳይ፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ትኩረትም ሆኗል።
መንግሥታቸው ሲያነሳው የቆየው ይህ ጉዳይ አሁን ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ "ምን ችግር እንዳለው ሁሉም ሰው" እየተመለከተው ነው ብለው እንደሚያስቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያን የሚያክል አገር ከዚያ ርቃ፣ ሸሽታ መኖር የሕልውና ጉዳይ ነው ያስባለው አሁን በግልጽ፣ ማንም ሰው በቀላሉ የሚገነዘበው ይመስለኛል" ብለዋል።
ዐቢይ የባሕር በር አልባ መሆን "ገመናን" ከመሸፈን እንዲሁም ከሎጂስቲክስ ጋር በተያያዘ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ዘርዝረዋል።
የኢንተርኔት መረጃዎች የሚተላለፉባቸው የባሕር ስር መስመሮች በሌላ አገራት በኩል የሚልፉ በሚሆንበት ጊዜ "ዳታ ገመና የለውም፤ ሚስጥር የለም ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል። መጠበቅ ያለባቸው "የአገር ሚስጥሮች" ዋስትናን የማረጋገጥ ስጋት እንደሚጋርጥም ጠቁመዋል።
የሚስጥር አለመጠበቅ ስጋት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እና ወደ ውጭ በሚላኩ ቁሶች ላይም የሚታይ መሆኑን ጠቅሰዋል። "ኢምፖርት የምታደርጋቸው ማንኛውም ቁሳቁሶች ሁሉም ሰው ማወቅ አይጠበቅበትም" ያሉት ዐቢይ፤ "የምትሸጠውን ለማን፣ የት፣ መቼ ሁሉም ነገር መታወቅ የለበትም" በማለት ተናግረዋል።
"የጂኦፖለቲክሱ ውድድር፣ ፍላጎት የሚታወቅ ስለሆነ ማንኛውንም እንቅስቃሴህን ሁሉም ሰው የሚያውቅ ከሆነ ጉዞህ በአጭሩ ሊጨነግፍ ስለሚችል. . ." ሲሉ አብራርተዋል።
ዐቢይ የባሕር በር አለመኖር የሎጂስቲክስ ወጪንም እንደሚጨምር የገለጹ ሲሆን በዚህ የተነሳ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ "ከእኛ ጎረቤቶች አንጻር ከ50 እስከ 100 ፐርሰንት" ከፍ እንደሚል ተናግረዋል። ከወጪው በተጨማሪ ምርቶች የሚጓጓዙበት ቅልጥፍና ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Shipping and Logistics
"በዚህ ምክንያት በአጭር ጊዜ እና ረጅም ጊዜ ከፍለን ካልሰራን በቀር የባሕር በር አልቦነት፣ የወደብ አልቦነት፣ የሎጂስቲክስ ውስንነት የኢትዮጵያ ብልጽግና ላይ ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ የሚቀጥል ችግር ነው። በእኛም ዘመን፣ ከእኛ በኋላም ባለው ዘመን" ብለዋል።
"እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ግራ ቀኝ የሚሉ ዜጎች ስሰማ ይገርመኛል" ያሉት ዐቢይ፤ ተጽዕኖው "እያንዳንዱ ዜጋ" ላይ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያን የሚያክል፣ በዓለም 10ኛ የሕዝብ ቁጥር የያዘ፣ በዘመናት መካከል የወደብ አልቦነት ችግር ያልነበረው አገር" የባሕር በር ያላገኘው፤ "በክፋት፣ ባለመነጋገር፣ በሰጥቶ መቀበል መርኅ ባለማመን፣ አብሮ ለመኖር ባለመዘጋጀት" ምክንያት እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
"ከምጽዋ ጫፍ እስከ ሞቃዲሾ ቀንድ ጫፍ ድረስ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር" የሚደርስ የባህር ዳርቻ በመኖሩ፤ "በቀላሉ በንግድ ሕግ፣ በንግግር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ማግኘት" ይቻል እንደነበር ጠቅሰዋል።
"አንዳችን ለአንዳችን ጥፋት እንድንሆን በሚያመቻች መንገድ ለመሄድ በማሰብ ብቻ ኢትዮጵያን የባሕር በር አልቦ አድርጎ መቀጠል በየትኛውም ዘመን አዋጪ አይደለም። ለእኛ ብቻ አይደለም፤ ለሰፈራችንም አዋጪ አይደለም" ብለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የከፈቱባት ኢራን የዘጋችው የሆርሙዝ ወሸመጥን "ማስከፈት የዓለም አጀንዳ" መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። "የቀይ ባሕር ቢዘጋ ማስከፈት ከእኛ በላይ ለማን አጀንዳ ይሆናል?" ሲሉ ጠይቀዋል።
እንደ ዐቢይ ገለጻ፤ የኢራን ጦርነት ያስከተለው የኤነርጂ አቅርቦት መስተጓጎል ከሌሎቹ አፍሪካ ቀጣናዎች በተለየ "ምሥራቅ አፍሪካን" ጎድቷል።
የሰሜን፣ ምዕራብ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት የአቅርቦት ሰንሰለት በሌሎች የባሕር መስመሮች የሚተላለፍ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "እኛ ግን በቀይ ባሕርም ይሁን፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ፣ በኢራን አካባቢም ያለው ሰርጥ በቀጥታ ጥቃት የሚደርስብን አገር ነን" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty
ችግሩን ያባባሰው "የሩቁ" የሆርሙዝ ወሽመጥ ከመዘጋቱ በተጨማሪ "የቅርቡ ችግር ውስጥ መግባቱ" እንደሆነ በማንሳትም፤ የኢራን አጋር የሆነው አማጺው ሁቲ በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በቀይ ባሕር መካከል በሚገኘው የባብ-ኤል መንደብ ወሽመጥ ላይ ይጥለዋል ተብሎ ስለተፈራው ስጋትም ጠቁመዋል።
"ችግሩን እያየን ለመከላከል እንኳ፣ የእኛን ጥቅም ለመጠበቅ እንኳ መሠማራት የማንችል መሆናችን ነው። ይሄ ጉዳይ በጣም በጣም አሳሳቢ ነው። ጎረቤቶቻችን ማሰብ አለባቸው፤ ዓለም ማሰብ አለበት። አስቸጋሪ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ካልሆነች አታድግም ብቻ ሳይሆን ሰፈሩ አይለወጥም፣ ሰፈሩ ሰላም አያገኝም፣ የዓለም ንግድም ይስተጓጎላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
"እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ምሰሶ (anchor) አገሮች ቁጥጥር ስር መዋል የሚገባቸው አካባቢዎች፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትላልቅ አቅም ያላቸው አገራት ከጉዳዩ ርቀው ከሄዱ ትናንሽ አገራት ያንን ሰርጥ፣ ያንን ወሽመጥ መጠበቅ ስለማይችሉ በእነሱም ጭምር፣ በተቀረው ዓለምም [ላይ] አደጋ ያመጣል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት "ጭቅጭቅ" ሊደረግበት እንደማይገባ የገለጹት ዐቢይ፤ "በተቻለ መጠን፣ በሰላም፣ በንግግር፣ በድርድር" መፈታት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። መቼ ይሆናል የሚለው ጉዳይ "ማሰብ፣ ማስላት፣ መምከር" ሊጠይቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
"ግን የግድ መሆን ያለበት ጎዳይ ነው። ኢትዮጵያ 'ከባሕር በር ተነጥላ እስከ ወዲያኛው ትኖራለች' ብሎ የሚያስብ የቅርብም ይሁን የሩቅ ሰው ካለ እርሱ የዋህ ነው። እንደዚህ የሕልውና ጉዳይን ወደጎን አድርጎ ብልጽግናን ማሰብ አይቻልም" ሲሉ ከዚህ ቀደም የሰጡትን አስተያት ደግመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቱን በይፋ ከገለጸ ወዲህ ከራስ ገዟ ሱማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ መሆን አልቻለም።
መንግሥት፤ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር እንዲኖረው ያለውን ፍላጎት በሚገልጽባቸው ጊዜያት የአሰብ ወደብ በተደጋጋሚ አብሮ ተነስቷል። ኤርትራ በበኩሏ ኢትዮጵያ "በሉዓላዊ የባሕር በር" ስም ጦርነት ልትከፍት ነው የሚል ክስ ታቀርባለች።















