እስራኤላውያንን በአግራሞት 'እጅ በአፍ ያስጫነው' የትራምፕ የሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዜና ትናንት ምሽት በእስራኤል ሰሜናዊ አካባቢ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ዘንድ በደረሰበት ወቅት ከሊባኖስ የሚተኮሱ ሮኬቶችን ተከትሎ ሦስት ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደወል ተሰምቷል።
በሰሜናዊቷ የናሃሪያ ከተማ ሰማይ ላይ የእስራኤል የአየር መከላከያዎች እነሱን ለመመከት የከፈቱት ተኩስ ፍንዳታ አስከትሏል።
የአምቡላንስ ሠራተኞች እንደተናገሩት የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከመሆኑ ጥቂት ሰዓታት በፊት ቢያንስ ሦስት ሰዎች በፍንጥርጣሪ ቆስለዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ ከባድ ጉዳት አስተናግደዋል።
እዚህ እና በመላ አገሪቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን በተኩስ አቁሙ እንደተስማሙ ጥያቄ ፈጥሯል።
በናሃሪያ የምትገኘው ተማሪዋ ጋል "መንግሥት እንደዋሸን ይሰማኛል" ብላለች። "አሁን በተለየ መንገድ እንደሚያበቃ ቃል ገብተውልናል፤ ነገር ግን እንደገና ምንም ነገር ወደማይፈታ የተኩስ አቁም ስምምነት የደረስን ይመስላል።"
"ለሊባኖስ መንግሥት ዕድል ሰጥተነዋል፤ ስምምነቱንም ለመጠበቅ አልቻሉም፤ ሄዝቦላህን ትጥቅ አላስፈቱም" ያለው ደግሞ ባለፈው ዓመት ቤቱ በሮኬት ተመትቶ የነበረ የ32 ዓመቱ የጭነት መኪና አሽከርካሪ ማኦር ነው።
"እኛ ካላደረግነው ማንም አያደርገውም። ማቆማቸው [ድብደባውን] ያሳዝናል። በዚህ ጊዜ ጉልህ ስኬቶች የነበሩ ይመስል ነበር።"
እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ አምስት ክፍለ ጦር ወታደር አላት። የጦር ኃይሏ ዋና ቃል አቀባይ ትናንት ግስጋሴያቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረው ነበር።
ይህ የተኩስ አቁም መግለጫ እስራኤልን አስገርሟታል፤ ይህ መገረም በተራው ማኅበረሰብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት የደህንነት ካቢኔ ውስጥም ጭምር የተፈጠረ ነው።
ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የእስራኤል የዜና አውታር ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመሰማቱ ጥቂት ደቂቃ ቀደም ብሎ የጸጥታ ካቢኔ ስብሰባ እየተሳተፉ እንደነበር ዘግቧል።
ከዚያ ስብሰባ ሾልከው የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሚኒስትሮቹ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ድምጽ እንዲሰጡ አልተደረገም።
ለብዙዎች ይህ ኔታንያሁ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ያቀረቡትን ጥያቄ መቀበል፣ ስምምነቶቹ ወይም ወቅቱ እስራኤል የምትፈልገው ባይሆንም እንኳ፣ ለአሜሪካ ጥያቄ ተገዢ መሆናቸውን የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"የተኩስ አቁም ስምምነት መምጣት ያለበት የእስራኤልን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከጠንካራ አቋም ነው" ሲሉ የቀድሞው የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ዋና አዛዥ እና የያሻር ፓርቲ መሪ ጋዲ አይሰንኮት ተናግረዋል።
"በጋዛ፣ በኢራን እና አሁን በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚጫንብን አካሄድ ተፈጥሯል። ኔታንያሁ ወታደራዊ ስኬቶችን ወደ ዲፕሎማሲያዊ ድል እንዴት መቀየር እንዳለበት አያውቅም።"
ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነቱን "ከሊባኖስ ጋር ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ" አድርገው ቢገልጹትም በመሬት ላይ ጥቂት ስምምነቶችን ብቻ ማድረጋቸውን ግልጽ አድርገዋል።
ሄዝቦላህ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን መጠየቁን ይፋ አድርጓል።
ቀዳሚው የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ እንዲወጣ ሲሆን ሌላው ደግሞ "አንተኩስም፤ አትተኩሱብን" የሚል መርህ ነው።
"በፊተኛውም ሆነ በኋለኛው አልተስማማሁም" ብለዋል። "እነዚህ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ አይደለም። በሊባኖስ ውስጥ ጠንካራ የጸጥታ ቀጠና ውስጥ ነው ያለነው[…] እዚያው ነን፣ እና አንወጣም።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከአሜሪካ ጋር ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ በሚገኘው የሄዝቦላህ ቡድን ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንድታቆም ስትጠይቅ ቆይታለች።
መጀመሪያ ላይ እስራኤል በሊባኖስ በሄዝቦላህ ላይ የምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ "የተናጠል ግጭት" እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ፣ ትራምፕ በዚህ ሳምንት "በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል ትንሽ የመተንፈሻ ቦታ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው" ብለው ነበር።
በዚህ መካከል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ድርድር ያለውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን የተኩስ አቁም ጊዜው በሚቀጥለው ሳምንት ሊጠናቀቅ ቀናትን እየቆጠረ ነው።
ኔታንያሁም ሆኑ የእስራኤል ወታደራዊ መሪዎች ትራምፕ ከቴህራን ጋር የተስማሙት የተኩስ አቁም ስምምነት በሊባኖስ ተፈጻሚ የሚሆን እንዳልሆነ አፅንዖት በመስጠት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የእስራኤል ቻናል 12 የዜና ኔትወርክ ባለፈው ሳምንት በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ወደ 80 በመቶ የሚጠጉ ምላሽ ሰጪዎች በሄዝቦላህ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ደግፈዋል።
እንዲሁም ሦስት የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡትትን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተቃውመዋል።
የማቴህ አሸር የክልል ምክር ቤት ኃላፊ ሞሼ ዴቪዶቪች ለእስራኤል መገናኛ ብዙኃን "በዋሽንግተን ስምምነት ሊፈረም ይችላል፣ ነገር ግን ዋጋው በደም እና በሚፈረሱ ቤቶች ይከፈላል" ሲሉ ተናግረዋል።
"የሰሜን ነዋሪዎች በዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ትርኢት ላይ ትርፍ አይደሉም" ሲሉ አክለዋል።
እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተስማማችው የተኩስ አቁም ስምምነት "በማንኛውም ጊዜ ራስን ለመከላከል የሚፈጸሙ የታቀዱ፣ ወይም ቀጣይ ጥቃቶችን ለመፈጸም እርምጃ የመውሰድ መብቷን እንደምትጠብቅ" በግልጽ ያሳያል።
ይህ ደግሞ እአአ በኅዳር 2024 ተደርሶ በነበረው የመጨረሻው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት እስራኤል እንደ ስጋት በምትቆጥራቸው ዒላማዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሟን በመቀጠል አሳይታለች።
ጥቂቶች እስራኤላውያን ይህንን የተኩስ አቁም ስምምነት ከሄዝቦላህ ጋር ከተፈጠረው ግጭት ለመውጣት እንደ መንገድ አድርገው ይመለከቱታል።
ነገር ግን ብዙዎች መሪያቸው ከዋሽንግተን ፍላጎቶች ጋር እንዲጓዙ ጫና ውስጥ መግባታቸውን እና የቁልፍ አጋራቸው የአሜሪካ የጦርነት ግቦች ሁልጊዜ ከእነርሱ ፍላጎት ጋር አንድ ዓይነት አለመሆናቸውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ አድርገው ይመለከቱታል።















