የኢቦላ መከሰት ለሕክምና እርዳታ ሰጪዎች በርካታ ተግዳሮቶችን መደቀኑ ኤምኤስኤፍ ገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢቦላ ወረርሽኝ ዳግም መከሰት ለሕክምና እርዳታ ድርጅቶች ከፍተኛ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ መሆኑን አንድ ከፍተኛ የሰብዓዊ ድርጅት ኃላፊ ተናገሩ።

ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየሄዱ የሚገኙት የሜዴሲን ሳን ፍሮንቲየርስ (ኤምኤስኤፍ) የፕሮግራም ኃላፊ፣ ኬት ዋይት ገንዘብ እና ቁሳቁሶችን ወደ አገሪቱ ማስገባት አለመቻላቸው እጅግ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሦስት የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች የሟቾችን አስከሬን ሲያነሱ በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ መሞታቸው ተገልጿል።

ቫይረሱ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለሞት እንደዳረገ እና ከ850 በላይ የሚሆኑ ደግሞ በበሽታው መያዛቸው ይጠረጠራል።

እሁድ ዕለት ወደ ኮንጎ የተጓዙት ዋይት "ሁሉም የመከላከያ እርምጃዎች በቦታው መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ያጠናክራል" ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ቫይረሱ መጀመርያ ከታሰበው በላይ በፍጥነት እየተዛመተ መሆን አስታውቆ አሳሳቢ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ነው ሲል አውጇል።

ለወረርሽኙ እስካሁን ድረስ ክትባት የሌለ ሲሆን በሙከራ ላይ ያሉ ግን መኖራቸው ተሰምቷል።

በሽታውን ለማከም የሚያስችል ምንም መድሃኒት አለመኖሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል።

በአፍሪካ ከዚህ በፊት በተከሰቱ የኢቦላ ወረርሽኞች ላይ የሠሩት ዋይት "እነዚህን ወረርሽኞች በተደጋጋሚ ብናያቸውም አሁንም ሁሉን አቀፍ የሕክምና መከላከያ እርምጃዎች የሉንም... [ሕክምና፣ ክትባቶች፣ በፍጥነት ሊተገበሩ የሚችሉ የምርመራ መንገዶች] በአሁኑ ጊዜ ስላለው የዓለም ሁኔታ አንድ ነገር ይነግረናል።"

የአየር ክልል መዘጋት የጤና ባለሙያዎችን እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ቫይረሱ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች ማጓጓዝ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንደሚያሳስባቸውም ጠቅሰዋል።

"አሁን ማግኘት የሚያስፈልገን መጠን በጣም ግዙፍ ነው" ያሉት ዋይት፤ "ቫይረሱ በተሰራጨባቸው በሁሉም አካባቢዎች በበሽታው የተያዙትን የመለየት እና የማከም አቅምን ማሻሻል አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች ምንም ዓይነት ድጋፍ በማያገኙበት የሕክምና ማዕከላት ውስጥ ተቀምጠው እንዲቆዩ አንፈልግም" ብለዋል።

"ከሕመሙ እንዳገገሙ ወዲያውኑ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱም እንፈልጋለን፤ ስለዚህ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ ይችላሉ፤ እኛ ግን እስካሁን ያንን ማድረግ አልቻልንም።"

ኢቦላ ምንድን ነው? ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው?

ኢቦላ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ የሆነ ተላላፊ በሽታ ነው። መጀመሪያ ላይ የሚታዩት ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ከፍተኛ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ጉሮሮ መከርከር ናቸው።

ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ሲሠራጭ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ይከሰታል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰውነታቸው ውስጥ እና ከሰውነታቸው ውጪ ደም ይፈስሳቸዋል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምልክት የሚያሳዩት ከሁለት ቀናት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ኢቦላ እንደ ወባ እና ታይፎይድ ካሉ ሕመሞች ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች አሉት።

ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው የሚረጋገጠው በቤተ ሙከራ በሚደረግ ምርመራ ብቻ ነው።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለይቶ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1976 ሲሆን፤ በወቅቱ ወረርሽኙ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን ተስፋፍቶ ነበር።

በሽታው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የሚወጣ የሰውነት ፈሳሽ ጋር የሚኖር ንክኪ ነው። ይህም ደም፣ ምራቅ፣ የወንድ የዘር ፈሳሽ፣ ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ፣ ሽንት፣ ሰገራ እና ላብን ይጨምራል።

ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ የነካቸው ቁሳቁሶችም በሽታውን ያስተላልፋሉ። ዐይን፣ አፍንጫ፣ አፍ እና አንዳች ስንጥቅ ያለው የቆዳ ክፍል በመንካት ቫይረሱ ይተላለፋል።

የሌሊት ወፍ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጃርት እና ድኩላ በሽታውን የሚያስተላልፉ እንሰሳት ናቸው። ለምግብነት የሚታደኑ የዱር እንሰሳት ሥጋ ላይ ቫይረሱ ሊኖር ይችላል።

በኢቦላ ሳቢያ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን መንካትም ለበሽታው ያጋልጣል።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በከፍተኛ መጠን የኢቦላ ወረርሽኝ የተነሳው ከአውሮፓውያኑ 2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ሲሆን 2,300 ገደማ ሰዎች ሞተዋል።

በ2022 በኡጋንዳ በተከሰተው የሱዳን ኢቦላ ዝርያ ወረርሽኝ ምክንያት 164 ሰዎች ለኅልፈት ተዳርገዋል።

በ2014 በጊኒ፣ በላይቤሪያ እና በሴራ ሊዮን የተነሳው የኢቦላ ወረርሽኝ ከምንጊዜውም በላይ የከፋ ሲሆን ከ11,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።