ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራናውያን ትራምፕ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸው የቴህራንን ፖሊሲ ይቀይር ይሆን?
የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የሽኝት እና የቀብር ሥነ ስርዓት ከተለመደው ዘለግ ብሎ ለአንድ ሳምንት ያህል ተካሄዷል።
የቀብር ሥነ ስርዓቱ ግን ሐዘንን ከመግለጽ ባለፈ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቁ መልዕክቶች በስፋት ተደምጠውበታል።
የኢራን ፖለቲካ እና ሃይማኖት መሪዎች ለኻሜኒ ሞት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ብሔራዊ ግዴታ መሆኑን ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃንም ይህንን በሰፊው ዘግበውታል።
ይህ የፖለቲከኞቹ የበቀል እርምጃ ጥሪ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር በዲፕሎማሲያዊ ንግግር ውስጥ ያለችው ኢራን ከኻሜኒ በኋላ በየትኛው አቅጣጫ ልትጓዝ ትችላለች የሚል ጥያቄ አጭሯል።
'በቀል' ለምን ማዕከላዊ ነጥብ ሆነ?
የኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ከአባታቸው የቀብር ሥነ ስርዓት በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ከእርቅ ወይም ከመልሶ ግንባታ ይልቅ በቀልን አንስተዋል።
ለሳምንት የዘለቀው የሐዘን ሥነ ስርዓት ካበቃ በኋላ ሐምሌ 4/2018 ዓ.ም. በተላለፈው መልዕክታቸው ላይ የሞቱ መሪዎችን መንገድ እንደሚከተሉ ይፋ አድርገዋል።
አስከትለውም "በእነዚህ ሁለት ጦርነቶች በወንጀለኛ እና የተዋረዱ ገዳዮች ሰማዕት የሆኑ ሰዎች ንጹህ ደምን እንበቀላለን" ብለዋል።
"የሕዝባችን ፍላጎት" በማለት የገለጹት በቀል "መፈጸም እንዳለበት" ገልጸዋል።
ለኢራናውያኑ ሞት ተጠያቂ ናቸው ያሏቸውንም አካላት "ሰላማዊ የሞት ጽዋን አትጎነጩም" ሲሉ ዝተዋል።
ይህ ከአዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ የተሰማው መግለጫ በአባታቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ከመግለጽም ያለፈ ነው።
መልዕክቱ በሽኝት ሥነ ስርዓቱ እና በቀብሩ ወቅት የታየው ስሜት ነጸብራቅ ነው።
በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ማሻድ ከተማ የተካሄደው የኻሜኒ የቀብር ሥነ ስርዓት በፖለቲካ ቅስቀሳ የታጀበ ነበር።
የአገሪቱ ብሄራዊ መገናኛ ብዙኃን በቀልን የሚጠይቁ ሐዘንተኞች መፈክር ሲያሰሙ በተደጋጋሚ አሳይቷል።
ሐዘንተኞቹ ለኻሜኒ ሞት ትራምፕን እና ቤንያሚን ኔታንያሁን ተጠያቂ የሚያደርጉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል።
ሌሎች መፈክሮች ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ድርድርን ውድቅ የሚያደርጉ የነበሩ ሲሆን ከዲፕሎማሲ ይልቅ ፍትህ እንዲሰፍን የሚጠይቁ መልዕክቶችን አስተጋብተዋል።
ይህም የቴህራን ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ይወስናል ተብሎ ተሰግቷል።
በቀብሩ ላይ የተገኙ ከፍተኛ ፖለቲከኞች፣ የፓርላማ አባላት እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ወግ አጥባቂዎች ሁሉም በአንድ ድምጽ በቀል እንዲፈጸም የሚጠይቁ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
የበቀል እርምጃ ሃሳብ እንዴት ተዛመተ?
የኢራን የፖለቲካ ስርዓት ከዋና ዋና ብሔራዊ ቀውሶች በኋላ ለረጅም ጊዜ ተምሳሌታዊ ቋንቋን በመጠቀም ይታወቃል። ነገር ግን ከኻሜኒ ሞት በኋላ የበቀል ጥሪውን የሚያጠናክሩት ድምጾች የበለጠ ግርምትን የሚያጭሩ ናቸው።
የቀድሞው የኒውክሌር ተደራዳሪ እና ወግ አጥባቂ ፖለቲከኛ ሰኢድ ጃሊሊ "ሰማዕት የሆኑትን መሪ" ደም መበቀል "የአገራችን መብት እና የባለሥልጣናት ግዴታ" መሆኑን በመግለጽ ተናግረዋል።
የአገሪቱን ታላቅ ብሔራዊ ሀብት መጠበቅ የበቀል እርምጃን ይጠይቃል ሲሉ ተከራክረዋል።
ሌላኛው ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል አሚር ሆሴይን ሳቤቲ በበኩላቸው ሕግ አውጪዎች ትራምፕን እና ሌሎች የአሜሪካንና የእስራኤል መሪዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ለፓርላማ የቀረቡትን ሕጎች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲመለከቱ አሳስበዋል።
የፓርላማው የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሊ ኬዝሪያን በበኩላቸው ፓርላማው ባሳተመው ጽሑፍ ላይ በታላላቅ የሃይማኖት አባቶች የወጡ ውሳኔዎች ቀድሞውኑ "የበቀል እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አቅም" እንደነበሩ እና ይህንንም "ምንም ኃይል" ሊከላከል እንደማይችል ተናግረዋል።
ይኸው መልዕክት በተለያዩ ከተሞች በተደረጉ የአርብ ጸሎቶች ላይ ተስተጋብቷል። በማሽሃድ ወግ አጥባቂ የሃይማኖት አባት የሆኑት አህመድ አላሞልሆዳ "ሰማዕት የሆኑትን መሪ" ደም መበቀል ሁልጊዜ "የሕዝብ ፍላጎት" ሆኖ መቆየት እንዳለበት ለምዕመናን ተናግረዋል።
በቡሼህር የሚገኙት ሌላኛው የእምነት አባት ዩሴፍ ጀማሊ፣ ዜጎች የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ እየጠየቁ እንደሆነ በመግለጽ ጥሪው እስኪፈጸም ድረስ ጥያቄያቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
በአርዳቢል ሌላኛው የአርብ ጸሎት መሪ ሀሰን አሜሊ፣ ምንም እንኳን በቀል የማይቀር ቢሆንም፣ "አንድ ሺህ የትራፕም" ሞት እንኳ የሟቹን መሪ ደም ዋጋ ሊተካከል እንደማይችል ገልጸዋል።
አክራሪ ጋዜጦች እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን መልዕክቱን የበለጠ አጉልተውታል።
የጋዜጦቹ ርዕሰ አንቀጾች የበቀል እርምጃን የአገሪቱ ሕዝብ ዋና ፍላጎት አድርገው ሲገልጹት፣ ሚዲያዎቹ ደግሞ ቀይ ባንዲራ ይዘው የበቀል ጥሪ የሚያሰሙ ሐዘንተኞች ምስል በተደጋጋሚ አሳይተዋል። አንዳንድ ወግ አጥባቂ የዜና አውታሮች የትራምፕን ምሰል ከ "ይፈለጋል" ማስታወቂያ ጋር በማድረግ አሳይተዋል።
ትራምፕ ለምን ትዕምርት ሆኑ?
የኢራን ባለሥልጣናት ዩናይትድ ስቴትስንም ሆነ እስራኤልን ማውገዛቸውን ቢቀጥሉም፣ የኻሜኒ ሞትን በተመለከተ አብዛኛው የሕዝብ ቁጣ በትራምፕ ዙሪያ ያተኮረ ነው።
በኢራን ይፋዊ መግለጫዎች ውስጥ፣ ትራምፕ እንደ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ብቻ ሳይሆን በቅርብ ጊዜ በተካሄደው ግጭት የመክፈቻ ምዕራፍ ላይ ኻሜኒ የተገደሉበትን ጥቃት ይሁንታ የሰጡ ግለሰብ እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል።
የትራምፕን አቋም በኢራን አክራሪ ወገኖች ዓይን የበለጠ የሚያወሳስበው ደግሞ ይህ ታሪክ ነው።
በእነርሱ ምልከታ፤ እአአ በ2020 በባግዳድ በተፈጸመው የአየር ጥቃት የኢራንን ኃያል አዛዥ ቃሴም ሶሌይማኒ እንዲገደሉ ትዕዛዝ የሰጡት ትራምፕ ላይ መወሰድ የነበረበት የበቀል እርምጃ ዘግይቷል።
ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ ያተኮረ የበቀል ዛቻ የጂኦፖሊቲካዊ ግጭትን ወደ ሞራል ትግል ለመቀየር ይረዳል።
ይህም መንግሥት ሰፊ ቅሬታዎችን የሚያስተጋባበት ግልጽ የሆነ ግለሰብ እንዲኖር አድርጓል።
በዚህ መልኩ የኢራን ባለሥልጣናት የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከአንድ አስተዳደር ወይም ከአንድ አገር በላይ እንደሚዘልቅ በማሳየት የሚቃወሙት ነገር የፖለቲካ ችግሮቻቸው ሁሉ ትዕምርት አድርገው ስለዋቸዋል።
ዛቻው የአገሪቱ ፖሊሲን ያመለክታል?
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት፣ ሐዘንተኞች ለበርካታ ዓመታት የሺዓ ሙስሊሞች በካርባላ ጦርነት የኢማም ሁሴንን ግድያ ለመበቀል የሚያሰሙትን ድምፅ የሚያስተጋቡ ቀይ ባንዲራዎችን ይዘው ነበር።
መፈክሩም ተመሳሳይ የሆነ 'የተቀደሰ ምኞት' ቀጣይነትን ለማጉላት የተጻፈ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ ከ1979 አብዮት ወዲህ እስላማዊ ሪፐብሊክ በችግር ጊዜ መስዋዕትነትን፣ ተቃውሞን እና አለ የሚባልን ኢፍትሃዊነት ለመግለጽ ይህንን በተደጋጋሚ ተጠቅሟል።
የኢራን መሪዎች ብዙውን ጊዜ በግጭት ወቅት ስትራቴጂካዊ ተለዋዋጭነትን በመጠበቅ ረገድ የማያወላውል ንግግር ያደርጋሉ። ሆኖም ግን የአሁኑ ዘመቻ በጥንካሬው ከዚህ ቀደሞቹ ይልቅ ጎልቶ ተስተውሏል።
በተከታታይ ከተናጠል መግለጫዎች ይልቅ የተቀናጀ የሚመስለው የበቀል ጥሪ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች፣ ከፓርላማ አባላትና ከሃይማኖት አባቶች ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ቁልፍ የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ካላቸው ከፍተኛ መሪዎችም ጭምር የተሰማ ነው።
ባለሥልጣናት እንዴት እና መቼ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ሆን ብለው ግልጽ ባያደርጉም፣ የሞጅታባ ኻሜኒ ሃይማኖታዊ አቋም ለወደፊቱ ለሚደረገው የበቀል ዘመቻ ከፍተኛ ክብደት እና ሃይማኖታዊ ቅቡልነት ይሰጣል።
ለዲፕሎማሲው ምን ማለት ነው?
ይህ ንግግር ለጊዜው የመንግሥት ፖሊሲ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ወደፊት በሚኖር ዲፕሎማሲ ዙሪያ የሚኖረውን የፖለቲካ ሁኔታ መልክ ያስይዛል።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የተሰሙት የበቀል ጥሪዎች ድርድርን ውድቅ ከሚያደርጉ መፈክሮች ጋር በጋራ ነበር የቀረቡት።
የወግ አጥባቂው ዕለታዊ ጋዜጣ ካይሃን አዘጋጅ የኢራን ባለሥልጣናት ትራምፕን "መገደል አለበት" ብለው ማወጅ እንዳለባቸው ተናግሯል።
አክሎም ከዋሽንግተን ጋር የሚደረግ ማንኛውም ድርድር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለኢራን ለፍርድ ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጉን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተከራክሯል። ምንም እንኳን ይህ ንግግር በፖሊሲ ረገድ ወረቀት ላይ የሰፈረ ባይሆንም ጥያቄው አሁንም በኢራን የፖለቲካ ተቋማት ውስጥ ያለውን ስሜት ያንፀባርቃል።
እንዲህ ዓይነቱ መልእክት ከአሜሪካ ጋር ለመተባበር የአገር ውስጥ የፖለቲካ ፍላጎት ዝቅ ያደርገዋል። ይህም የወደፊት ስምምነቶችን ለወግ አጥባቂ ወገኖች ለማሳመን አስቸጋሪ ያደርጋል።
ሲኤንኤን የስለላ ምንጮችን በመጥቀስ እስራኤል ቴህራን ትራምፕ ዒላማ ለማድረግ ማሰቧን በመጥቀስ ማስጠንቀቋን ዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኒውዮርክ ፖስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጉዳዩን ከአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃቶች ጋር በማያያዝ ለሚሰጠው ምላሽ መመሪያ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ሐምሌ 4 2018 ዓ.ም. በሶሻል ትሩዝ ገጻቸው ላይ "1,000 ሚሳዔሎች ለዚህ ዓላማ ተቀባብለው ተቀምጠዋል" በማለት ጽፈዋል።
የኢራን ዘመቻ በአብዛኛው ተምሳሌታዊ ሆኖ ይቀጥላል ወይም የወደፊት የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚለውን ማወቅ አይቻልም።
ሆኖም ግን የአዲሱን ጠቅላይ መሪ መግለጫ ከሃይማኖታዊ መልክቶች እና ከከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከመንግሥት ሚዲያዎች ከተሰሙ መልዕክቶች ጋር በማጣመር እስላማዊ ሪፐብሊክ በቀልን ከኻሜኒ በኋላ ባለው ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ አካል አድርጎታል።
ይህም አስቀድሞ የተገደበውን የወደፊት የአሜሪካ-ኢራን ግንኙነት የበለጠ በማጥበብ አደጋ ላይ የሚጥል ነው።