ብዙም ያልተነገረለት አሜሪካ በምሥጢር ከቬንዙዌላ አስወጥታ የወሰደችው የበለጸገ የዩራኒየም ክምችት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የቬንዙዌላ መከላከያ ሠራዊት በዋና ከተማዋ ካራካስ ውስጥ ከሚገኘው የሳይንስ ምርምር ተቋም ተነስቶ 160 ኪሎሜትር ተጉዞ በካራቦቦ ግዛት ወደምትገኘው የወደብ ከተማ ፑርቶ ካሌቦ የተጓዘው በምሥጢር ምሽት ላይ ነበር።

ምሥጢራዊው የምሽት ጉዞ ግልጽ የሆነው ከቀናት በኋላ ነው። ወታደሮቹ 13 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበለጸገ ዩራኒየም የጫነ እና ወደ አሜሪካ የሚጓዝ ተሽከርካሪ አጅበው ተጉዘዋል።

በጉዞው የአሜሪካ፣ የቬንዙዌላ እና የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት እንዲሁም ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ተሳትፈዋል።

በግንቦት ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ባወጣው መግለጫ እንቅስቃሴው "በጥንቃቄ የታቀደ የጋራ ተልዕኮ ነው። በጥብቅ የደኅንነት እርምጃዎች ታጅቦ ተከናውኗል" ብሏል።

የተጓጓዘው ኒውክሌር ለአደጋ የሚያጋልጥ ወይም ባልተገባ አካል እጅ ከወደቀ ለደኅነት የሚያሰጋ መሆኑን ጠቁሟል።

ዩራኒየም በከፍተኛ መጠን በልጽጓል ወይም ተብላልቷል የሚባለው ወደ 20 በመቶ ከፍ ሲል ነው።

የተጓጓዘው 13 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ አጠቃላዩ የዩራኒየም ክምችት 400 ኪሎ ግራም ይመዝናል ተብሏል።

የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ክምችቱ የቴህራን እንደነበር ይታመናል። የቬንዙዌላ መንግሥት ከኢራን፣ ከሩሲያ፣ ከኩባ እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለው ትስስር ለአሜሪካ መንግሥት አስጊ ሆኖ መቆየቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች እና ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ተናግረዋል።

የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት ባለሙያ ጃክ ክራውፎርድ እንደሚናገሩት፤ ዩራኒየሙን ማጓጓዝ ያስፈለገው በከፍተኛ መጠን የበለጸገ ዩራኒየም በአገራት ወይም በሌሎች የኒውክሌር መሣሪያ መሥራት በሚፈልጉ ኃይሎች እጅ እንዳይወድቅ ነው።

በከፍተኛ መጠን የበለጸገ ዩራኒየም በአንድ ወቅት ለሰላማዊ ዓላማ እንደሚውል ይታሰብ ነበር።

የተጓጓዘው ዩራኒየም ከ20 በመቶ በላይ የሆነ ዩራኒየም-325 ሲሆን፤ በ90 በመቶ መጠን የተብላላ ዩራኒየም "አነስተኛ የኒውክሌር መሣሪያ ለመገንባት" እንደሚውል ይታመናል።

ቬንዙዌላ እንዴት በከፍተኛ መጠን የበለጸገ ዩራኒየም ኖራት? ለምንስ ለአሜሪካ አስረከበችው? የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በአውሮፓውያኑ 1953 ያደረጉት ንግግር ለሁሉም ነገር መነሻ ሆኗል።

በዝቃዛው ጦርነት ጦርነት ወቅት አሜሪካ እና ሩሲያ የጦር መሣሪያ ለማከማቸት ይሞክሩ ነበር።

አገራት እና የተለያዩ አካሎች የኒውክሌር መሣሪያ ሊታጠቁ ይችላሉ የሚል ስጋት የተንሰራፋበት ወቅት እንደሆነ ይነገራል።

ስለዚህም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም እንዲመሠረት እና አውቶሚክ ኢነርጂን እንደ ሕክምና እና ግብርና ላሉ ሰላማዊ ዓላማዎች ማዋልን እንዲያበረታታ ሐሳብ አቀረቡ።

"መሣሪያውን ከጦር ኃይሎች መንጠቅ ብቻ በቂ አይደለም። ከወታደራዊ አገልግሎት አውጥተው ለሰላማዊ ዓላማ በሚያውሉት እጅ መግባት አለበት" ብለዋል።

ኒውክሌር የማምረት አቅም ያላቸው አገራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስረክበው ደኅንነቱ በተጠበቀ ሥፍራ እንዲቀመጥ ማድረግ ነበር ሐሳቡ። ተመራማሪዎችም ለሰላማዊ ዓላማ የሚውልበትን መንገድ ይፈትሻሉ።

የፕሬዝዳንቱ ንግግር ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም እንዲመሠረት መነሻ ሆነ። አሜሪካም በግሏ 'አቶምስ ፎር ፒስ' የተባለ ተቋም ከፈተች።

በቀጣዮቹ ዓመታት አሜሪካ ሕጓን በማስተካከል የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ኤክስፖርት እንዲደረግ አመቻቸች። ግብዓቱ እና ክህሎቱ የሚሰጣቸው ጥቅም ላይ ሊያውሉት ለሚችሉት አገራት እንደሆነ ተገልጾም ነበር።

በዚህ መሠረት ቬንዙዌላ አርቪ-1 የኒውክሌር ሪአክተር ተሰጣት። ከአሜሪካው ጄነራል ኤሌክትሪክ ተቋም የተሰጣት 3 ሜጋዋት አቅም ያለው ኒውክሌር እንደነበር ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ገልጿል።

የኒውክሌር ነዳጅ ያቀረቡት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ነበሩ።

በአውሮፓውያኑ ኅዳር 22/1960 የተቋቋመው የቬንዙዌላ የሳይንስ ምርምር ማዕከል እስከ 1991 ድረስ ጥናት ሲካሄበት ቆይቷል። ከዚያም በከፊል ሥራውን አቁሟል።

የቬንዙዌላ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሙሉ በሙሉ ተቋሙ የተዘጋው በ1997 ነበር። ጥቅም ላይ እየዋለ የነበረው ነዳጅ በከፊል ከተቋሙ ሲወገድ የተቀረው ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበት ጀመር።

የዩናይትድ ኪንደም መንግሥት እንደሚለው የቬንዙዌላ መንግሥት የተቀረው ዩራኒየም በአውሮፓውያኑ 2017 እንዲወጣ ጠይቋል። ይሄንን ለማስፈጸምም ዕቅድ ወጥቶ ነበር።

የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ባለፈው ታኅሣሥ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ዩራኒየም የማስወጣት ሒደቱ እንዲፋጠን ምክንያት ሆነ።

አሜሪካ ፕሬዝዳንቱን ለመያዝ ጥቃት ስትከፍት የዩራኒየም ሪአክተሩ ሊመታ ተቃርቦ እንደነበር የቬንዙዌላ ባለሥልጣኖች ገልጸዋል።

በአውሮፓውያኑ ግንቦት 7 የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያቫን ጊል ባወጡት መግለጫ እንደተናገሩት ይህ ኦፕሬሽን የፈጠረው ስጋት ዩራኒየሙን የማስወጣት ሒደት እንዲፋጠን አድርጓል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዩራኒየሙን ለማስወገድ "ወራት የሚፈጅ ጊዜ እንደወሰደ" ገልጿል። ነገር ግን ከተያዘለት ጊዜ ገደብ ሁለት ዓመታት ቀድሞ ተጠናቋል ብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም የኒውክሌር ባለሙያዎች ዩራኒየሙን ከቬንዙዌላ አንስተው በአሜሪካ፣ ደቡብ ካሮላይና ወደሚገኘው አይኪን የኒውክሌር ተቋም አዘዋውረዋል።

ለጉዞው የተጠቀሙት ፓስፊክ ኤግሪት መርከብ ያለበትን ቦታ የሚጠቁም የሳተላይት መረጃን ማጋራት ያቆመው ሚያዝያ 11 በደቡብ ካሮላይና፣ ቻርልስተን ሲደርስ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም "በጥንቃቄ የተዋቀረ እና ሁሉንም ሰዓት ከፍተኛ የደኅንነት ጥበቃ ያልተለየው ነው" ብሏል።

ጉዞው እጅግ ውስብስብ እና በጥንቃቄ የታቀደ ሒደትን የተከተለ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ እና በ1970 ዎቹ የተገነቡ የኒውክሌር ማብላያዎች (ሪአክተር) በከፍተኛ መጠን የተብላላ ዩራኒየም ይፈልጋሉ።

አሁን ላይ በአነስተኛ መጠን የበለጸገ ዩራኒየም (እስከ 20 በመቶ) ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛል።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ተቋም እንደሚለው፤ በመላው ዓለም 7,000 ኪሎግራም በከፍተኛ መጠን የተብላላ ዩራኒየም ለተሠራበት አገር ተመልሷል፣ አልያም በማዕከላት ይዞታ ሥር ገብቷል።