ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእናታቸው ስም የሚጠሩ ወንዶች ለምን መነጋገሪያ ሆኑ?
በኬንያ በርካታ ሕፃናት በተለምዶ የሚጠሩት በወላጅ አባታቸው የመጀመሪያ ስም ነው። ሆኖም ከመጠሪያ ስማቸው ቀጥሎ የእናታቸውን ስም የሚያስከትሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
ይህ በስፋት የታየው በአገሪቷ ትልቁ በሆነው ኪኩዩ ጎሳ ውስጥ ነው። ጉዳዩ የመነጋገሪያ ርዕስ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች በሴት ስም የሚጠሩ ወንዶች መሳቂ እና መሳላቂያ ሆነዋል።
በእናታቸው ስም የሚጠሩ ልጃገረዶች እና ሴቶች ግን ተመሳሳይ ትችት አልገጠማቸውም።
ምክንያቱም በአብዛኛው በሚያገቡበት ጊዜ የባላቸውን የመጀመሪያ ስም መጠሪያቸው አድርገው ስለሚወስዱ ነው።
በአገሪቱ በሴቶች ስም የሚጠሩ ወንዶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አንዳንዶች በሴቶች ላይ ያለውን አመለካከት እና በአባዊ (ፓትሪያርካል) ሥርዓት ውስጥ ያለባቸውን ተፅዕኖ ይቀይራል ብለዋል።
ሌሎች ደግሞ በእናታቸው ስም የሚጠሩ ወይም የእናታቸውን ስም ለመጠቀም እያሰቡ ያሉ ወንዶችን ተችተዋል።
ከዚህ ቀደም የአባታቸውን ስም በእናታቸው ስም በመተካት የሚጠሩ ወንዶች እምብዛም አልነበሩም።
አሁን ግን እንደ የፓርላማ አባሉ ጆን ንጂጉና ዋንጂኩ ያሉ በርካታ ታዋቂ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ በእናታቸው ስም ይጠራሉ።
በላጤ እናት (ሲንግል ማም) ያደጉት የፓርላማ አባሉ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡት እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ሲሆን፣ ሲወለዱ ጀምሮ ነው 'ካ ዋንጂኩ' ወይም የዋንጂኩ ልጅ በሚል ቅፅል ስም መጠራት የጀመሩት።
እንደ ዋንጂኩ ያሉ ሲወለዱ ጀምሮ የእናታቸው ስም ለመጠሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ አንዳንዶች ግን ለእናታቸው ያላቸውን ክብር ለመግለፅ ስማቸውን መጠቀም መርጠዋል።
ኪጊያ ዋ ኤስተር በሚል ስም የሚታወቀው ሙዚቀኛ ፒተር ኪጊያ "የእናታችሁን ስም ስትወስዱ እናታችሁን ትወዳላችሁ፤ ታከብራላችሁ ማለት ነው" ብሏል።
በማኅበረሰቡ ውስጥ ቀድሞ የነበረውን ልማድ በመስበር የእናቱን ስም ለመድረክ ስሙ በመጠቀም ከሚታወቁ ቀዳሚ ሰዎች መካከል ኬንያዊው ሙዚቀኛ ፒተር ኪጊያ አንዱ ነው።
ኪጊያ ዋ ኤስተር (የኤስተር ልጅ) አሁን ላይ በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ይገኛል። ፈጣን ምት ባለው በጊታር በታጀበ የኪኩዩ ሙዚቃው ይታወቃል።
"የእናትህን ስም ስትወስድ፣ እናትህን ትወዳለህ፤ ታከብራለህ ማለት ነው" ሲልም የሙዚቃ ድርጅቱን ሳይቀር 'የኤስተር ልጅ በሚል ስም እንዳስመዘገበ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ድርጅቱ አሁን ላይ በሙዚቃው ዘርፍ ስመ ጥር ሲሆን፣ ሌሎች ወጣት ወንድ ሙዚቀኞችም የእርሱን እርምጃ እየተከተሉ ነው።
ፖስተሮችም ልክ እንደ ዌታካ ዋ ጃኒ እና 90ኬ ካ ሚሶህ ያሉ በእናታቸው ስም የሚጠሩ ሙዚቀኞችን አስተዋውቀዋል።
እነዚህ ሙዚቀኞች ግን በመዝገብ ስማቸው በወንድ ስም ነው የሚጠሩት።
ጋዜጠኛ ሳይመን ማቻሪያ ዋንጉይ ደግሞ የእናቱ ስም ይፋዊ መጠሪያው እንዲሆን ሆነ ብሎ መወሰኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ዋንጉይ እንደሚለው አባቱ በአብዛኛው በሕይወቱ ውስጥ የለም። በሕይወት ስለመኖሩም የሚሰማውም በጭምጭምታ ነው።
"በሕይወትህ ለሌለ ሰው ይህንን ዋጋ ለምን ትሰጣለህ?" ሲልም ይጠይቃል።
ዋንጉይ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ እናቱ ከሞተች በኋላ ያደገው ከሴት አያቱ ጋር ሆኖ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እስከሚያጠናቅቅ እና የልደት ካርድ እስከሚያወጣበት ጊዜ ድረስም የሚጠራበት የአባት ስም አልነበረውም።
ጋዜጠኛው ኢቫንስ ኪቤ ዋሴኬም በእናቱ ስም ነው የሚጠራው።
አንዳንድ ኬንያውያን አሁንም ድረስ በአንድ ወላጅ ብቻ የሚያድጉ ልጆች "ሥነ ምግባር እንደሚጎድላቸው ያምናሉ" የሚለው ጋዜጠኛው፣ "በተለይ በእናት ብቻ በሚያድጉት ላይ ይህ እንደሚብስ" ለቢቢሲ አስረድቷል።
ኬንያ ውስጥ የእናት ስምን መጠሪያ ማድረግ በሚኖረው ጥቅም እና ጉዳት ዙሪያ የሞቀ ክርክር መደረግ የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት አነቃቂ ንግግር በማድረግ የሚታወቁት ሮበርት ቡራሌ "ልማዱ ወንድነትን ያሳንሳል" የሚል አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነበር።
ይህም ታዋቂው የቴሌቪዥን አቅራቢ ፍሬድ ሙይቲሪ በይፋ ወጥቶ በሴት ስም መጠራት ምን ያህል ችግር እንዳስከተለበት እና እንዴት የእናቱን ስም ትቶ የራሱን የእንግሊዝኛ እና የኪኩዩ የመጀመሪያ ስሞችን ብቻ ለመጠቀም እንደወሰነ እንዲናገር አድርጎታል።
"በሕፃናት በተሞላበት ክፍል ውስጥ በሴት ስም መጠራት ለወንድ ልጅ ምን ያህል የሚያሳፍር እንደሆነ ታውቃለህ?" ሲል የፈጠረበትን ዝቅተኛ በራስ መተማመን በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።
"እነዚህ ልማዶች በ23 ዓመቴ ለድብርት ዳርገውኛል" ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታዮች ያሏት ወጣቷ የኪኩዩ የባህል ባለሙያ ዋይሪሙ ሙኩሩ እንደምትለው በሴት ስም የሚጠሩ ሰዎች ቁጥር መጨመር ላጤ እናቶች የሚመሩት ቤተሰብ እየተለመደ ከመምጣቱ ጋር የሚገናኝ ነው።
ካላገቡ ሴቶች የሚወለዱ ልጆች በሚሰጣቸው የወንድ ስም የመጠራት ልማድ እንዳለ ባለሙያዋ ትናገራለች።
"እናታችሁ አባታችሁ ማን እንደሆነ ባልነገረቻችሁ ሁኔታ ወይም አባታችሁ ካልተቀበላችሁ የእናታችሁ ታላቅ ወንድም ያንን ሚና ይወስዳል" ስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።
ሙኩሩ እንደምትለው አንዳንዴ ንብረት የመውረስ መብትን ስለሚሰጥ ወንድሞች ይህንን ለመቀበል ሊያመነቱ ይችላሉ።
የኪኩዩ ኪያማ ኪያ ማ የባህል ቡድን መሪ የሆኑት ሙግዌ ዋ ንጁሂም በዚህ ይስማማሉ። የላጤ እናቶች ወንድ ዘመዶች የውርስ አለመግባባቶች እንዳይኖሩ ለማድረግ ስማቸው ለዚህ ጥቅም እንዲውል ላይፈቅዱ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
ሆኖም በአፈ ታሪክ ኪኩዩዎች የዘር ሐረጋቸው ከማኅበረሰቡ የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች ጊኩዩ እና ምሙቢ 10 ሴት ልጆች የተገኘ በመሆኑ በሴት ስሞች መጠራት ሊያስንቅ አይገባም ይላሉ።
"እኔ በጎሳ ሙምቡይ ነኝ [ከአስሩ ሴት ልጆቹ አንዷ ከሆነችው ዋምቡይ የተወሰደ] ከመጀመሪያው ጀምሮ ሁልጊዜም ስማችን ከሴቶች ጋር አብሮ ይሄዳል" ብለዋል።
እንዲያውም ኪኩዩዎች ብዙውን ጊዜ የሙምቢ ቤት ተብለው ይጠራሉ። ይህ በአፈ ታሪክ የመሥራች እናታቸው ስም ነው።
አንጋፋው ሙዚቀኛ ዋ ኤስተርም የኪኩዩ ወንዶች የሴት ስሞችን በመጠሪያነት መጠቀምን የሚተቹ ሰዎች "አኗኗራችንን የማይረዱ ናቸው" ብለዋል።
ጆርጅ ጋቲጊ የተባሉት ምሁር እንደሚሉት የኪኩዩ ወንዶች በተለምዶ ራሳቸውን የሚለዩት በእናቶቻቸው ነው። ይህ ግን መደበኛ አይደለም። አሁን ላይ ይህንን ወደ መደበኛ ስም ማምጣት አዲስ ክስተት ነው።
ከአንድ በላይ ሚስት ጋር ጋብቻ ይፈፀም በነበረበት ወቅት በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ግራ መጋባትን ለማስወገድ ልጆች የሚለዩት በእናታቸው ስም ነበር። በባህልም በቤተሰብ ውስጥ በመጀመሪያ ስም መጠራት እምብዛም የተለመደ አይደለም።
በሕይወት የሌሉት ኬንያዊው ታዋቂ ደራሲ ንጉግዊ ዋ ቲየንጎ፣ አባታቸው ቲየንጎ ንዱኩ አራት ሚስቶች እንደነበሯቸው እና በልጅነታቸው ንጉጊ ዋ ዋንጂኩ በሚል በእናታቸው ስም ይጠሩ እንደነበር 'ዲሪምስ ኢን ኤ ታይም ኦፍ ዋር' በሚለው ግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ጽፈዋል።
በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እና በኪኩዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ጋቲጊ በበኩላቸው የሴት ስሞችን መጠቀም በዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ በተለይ ወንዶች ኃላፊነታቸውን ትተው በሄዱባቸው ሁኔታዎች "የሴቶችን ጥንካሬ" የሚያንፀባርቅ ነው ብለው ያምናሉ።
"የባህል ለውጦች እና አሁን በሥራ ክፍፍል ላይ ካለው ዘመናዊ እውነታ ጋር መታረቅ አለብን" ብለዋል። ሴቶች የወንድ እንደሆኑ ይታሰቡ የነበሩ ሚናዎችን እየወሰዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ልጆች "በአባታቸው የማደግ ዕድል ሳያገኙ ሲቀሩ እናት፣ እናትም አባትም ትሆናለች" ይላሉ።
ይህ መደበኛ እየሆነ መምጣቱን ግን በበጎ አይመለከቱትም።
ይህ እሳቤ እየቀጠለ ያለውን ችግር ሊያሳይ እንደሚችል አስረድተዋል።
አንድ ብሎግ የሴት ስሞችን እንደ መጠሪያ የመጠቀም ልማድን "በወንዶች ላይ እንደተጫነ ቀንበር" አስመስሎ የገለፀው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ "የኪኩዩ ወንዶችን ሴታሴት የማድረግ እና ደካማ የማድረግ ጥረት" ብሎታል።
ጋዜጠኛ ዋንጉይም "በሴት ስም መጠራት ሁልጊዜም ቀላል ላይሆን ይችላል፤ የማንነት ቀውስ ያስከትላል" ይላል።
ነገር ግን በእናቱ ስም እንዲጠራ በወሰነው ውሳኔ እንደሚኮራ ተናግሯል።
ስምህ ምንም ይሁን ምን ስኬታማ ከሆነክ ሰዎች አሁን ያለህበት ቦታ ለመድረስ የገጠመህን ትግል ሁሉ እንዳሸነፍክ ይረዳሉ ብሏል።