ቀጥታ, የአሜሪካ ጦር ኢራንን መደብደቡን ሲቀጥል፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤው አገራትን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አስፋፋች

አሜሪካ እሁድ ሌሊት ኢራን ውስጥ በፈጸመችው ድብደባ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ይውላል ያለችውን የሚሳዔል ክምችት መምታቷን አስታወቀች። ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጠው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በፈጸማቸው የአጸፋ ጥቃቶችን በርካታ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አውሮፓ ያላት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ያነሰ መሆኑ ተዘገበ

    የአውሮፓ አገራት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    አውሮፓ ለአውሮፕላን የምትጠቀምበትን ነዳጅ እያስገባች ያለችው ከአሜሪካ እና እስያ ሲሆን ይህም ያላት ክምችት እንዲሳሳ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል።

    በመካከለኛ ምሥራቅ ዳግም ያገረሸው ግጭት አውሮፓ የአውሮፕላን ነዳጅ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ዳግመኛ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።

    በተለይ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ በመስተጓጎሉ የበለጠ ተጎጂ የሆኑ አገራት ናቸው።

    የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመት፤ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በመቀስቀሱ ተዘግቶ ቆይቷል።

    ወሽመጡ በሰኔ ወር ላይ በከፊል ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ዳግም ያገረሸው ግጭት የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።

    በሐምሌ ወር ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም አሜሪከ እና ኢራን ዳግም መታኮስ በመጀመራቸው የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።

    የአውሮፓ ኮሚሽን በአውሮፓ ያለው ነዳጅ መመናመኑን ገልጾ ሁኔታው በነሐሴ ወር የበለጠ ሊባባስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

    በየካቲት መጨረሻ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ጦርነት እስኪጀመር ድረስ የአውሮፓ አገራት ግማሽ የሚሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ ያገኙ የነበረው ከመካከለኛ ምሥራቅ አገራት ነበር።

    ተንታኞች የአፍሪካ አገራት መጋቢት ላይ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተንብየው ነበር።

    ቢሆንም ከናይጄሪያ የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ እዲሁም ሕንድ እና ኦማን ማስገባት በመጀመራቸው እጥረቱ ተቃልሏል።

    በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገራት ከካናዳ ነዳጅ መግዛት መጀመራቸው ተሰምቷል።

    አሜሪካ እና ናይጄሪያ ወደ አውሮፓ ነዳጅ የሚልኩ ዋነኞቹ አገራት ናቸው። ነገር ግን ኩዌት፣ ካናዳ፣ ሕንድ እና ደቡብ ኮሪያ የአውሮፕላን ነዳጅ ያቀርባሉ።

  2. ኢራን “በአሜሪካ ጫና” ምክንያት ሆርሙዝን በተመለከተ ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ አለመድረሷን ገለጸች

    ኢራን እና ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ያደረጉት “በአሜሪካ ጫና” ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ቴህራን አስታወቀች።

    በኢራን እና አሜሪካ ጦርነት እንዲሁም ድርድር የክርክር ማዕከል የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ከዓለም ነዳጅ እና ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ገደማው ይተላለፍበት የነበረ የወሳኝ የባሕር መስመር ነው። ከጦርነቱ ወዲህ በወሽመጡ ላይ ያላትን ቁጥጥር ያጠናከረችው ኢራን፤ በሆርሙዝ ሌላኛው ጫፍ ከአሁን በኋላ ከምትገኘው ኦማን ጋር በመነጋገር እንደምታስተዳድረው ስትናገር ቆይታለች።

    የኢራን እና ኦማን ባለሥልጣናት ትናንት ቅዳሜ ዕለት የባሕር መስመሩን ትራፊክ አስተዳደር በተመለከተ መወያየታቸው ተገልጾ ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባቃኢ ዛሬ ሰኞ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በኦማን ዋና ከተማ በተካሄደው ውይይት ስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቀዋል። ቃል አቀባዩ፤ “ቅዳሜ ዕለት ሙስካት ውስጥ የተደረገው ንግግር [ከአሜሪካ ጋር በተፈረመው] የመግባቢያ ስምምነት አንቀጽ 5 ላይ በሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር” ብለዋል።

    አክለውም፤ “አሜሪካ ግልጽ እና ድብቅ በኦማን ላይ ባሳደረችው ጫና ምክንያት መከናወን የነበረበት ነገር ባለመሳካቱ እና ባለመፈጸሙ እናዝናለን" ሲሉ ዋሽንግተንን ተጠያቂ አድርገዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኢራን ሆርሙዝ በድጋሚ መዘጋቱን ካስታወቀች በኋላ ከትናንት ምሽት አንስቶ እስካሁን ምንም መርከብ በወሽመጡ እንዳላለፈ ‘ማሪን ትራፊክ’ ከተሰኘው የመርከቦች ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ አሳይቷል።

    ኢራን የአሜሪካ ጦር በሚያደርገው “ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ” ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በሆርሙዝ በኩል ጉዞ ማድረግ “የማይቻል” መሆኑን በትናንትናው ዕለት ገልጻ ነበር።

    አሜሪካ በበኩሏ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ክፍት ነው በሚል አቋሟ ጸንታለች። የአሜሪካ ማዕከላዊ እዛ በወጣው መግለጫ ሆርሙዝ ክፍት እንደሆነ እንዲሁም ጦሩ የመርከብ ጉዞ ነጻነትን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

  3. የአሜሪካ ጦር ኢራንን መደብደቡን ሲቀጥል፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤው አገራትን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አስፋፋች

    አሜሪካ እሁድ ሌሊት ኢራን ውስጥ በፈጸመችው ድብደባ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ይውላል ያለችውን የሚሳዔል ክምችት መምታቷን አስታወቀች።

    ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጠው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በፈጸማቸው የአጸፋ ጥቃቶችን በርካታ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጿል።

    ካለፈው ሳምንት ወዲህ በድጋሚ ያገረሸው የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት፤ ወደ ሌላ ሳምንት ተሸጋግሯል። ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ በመላው ኢራን የሚገኙ ከ140 በላይ ዒላማዎችን መምታቷን አስታውቃ ነበር። እንደ አሜሪካ ገለጻ ይህ ጥቃት የተፈጸመው የኢራን ኃይሎች በሆርሙዝ ወሽመጥ ይጓዙ የነበሩ መርከቦችን በማጥቃታቸው ነው።

    መርከቦቹ በትክክለኛው የጉዞ መስመር ላይ እንዳልነበሩ የገለጸችው ኢራን በአንጻሩ፤ ከእሁድ ዕለት አንስቶ በድጋሚ እስኪገለጽ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን አስታውቃለች። በተጨማሪም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በትናንትናው ዕለት በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና አጋሮቿ ጋር ጥቃት አድርሷል።

    በዚህ መልኩ ከፍ ወዳለ ደረጃ የደረሰው የሁለቱ አገራት ግጭት፤ ትናንት ሌሊትም ቀጥሏል። የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እሁድ ሌሊት ኢራን ላይ በከፈተው አዲስ ዙር ጥቃት የቴህራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ ጥቃት የማድረስ አቅም ይቀንሳል ያለውን ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ኃይሎች ኢራንን አየር መከላከያ ሥርዓቶችን፣ የባህር ዳርቻ የራዳር ማዕከላትን፣ የሚሳዔል እና የድሮን አቅሞችን እንዲሁም አነስተኛ የጦር መርከቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጿል። በዚህ ወደታራዊ ዘመቻ ላይ የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች፣ የባህር ኃይል መርከቦች እንዲሁም ለዚህ ዘመቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የባሕር ኃይል አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ዘርዝሯል።

    ማዕከላዊ ዕዙ ባወጣው መግለጫ፤ “ሆርሙዝ ወሽመጥ ለዓለም አቀፍ ንግድ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ነው። ኢራን አትቆጣጠረውም” ብሏል። የአሜሪካ ኃይሎች “የንግድ መርከቦችን የጉዞ ነጻነት ለማረጋገጥ ዝግጁ” መሆናቸውንም አክሏል።

    በተመሳሳይ መግለጫ ያወጣው ኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩሉ የአሜሪካ ጦር ይዞታዎችን ይዘዋል በተባሉ በቀጣናው አገራት ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል። ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ጥቃት የተፈጸመባቸው አገራት እንደሆኑ ተጠቅሷል።

    አብዮታዊ ዘቡ፤ "ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው ፕሪንስ ሀሰን የአየር ኃይል ጦር ሰፈር በርካታ ትላልቅ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና የነዳጅ ታንከሮች በሚሳዔል እንዲሁም ድሮን ጥቃቶች በእሳት ጋይተዋል" ብሏል።

    እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት ለአሜሪካ ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት መሆኑን የገለጸው አብዮታዊ ዘቡ፤ ባሕሬን ውስጥ ደግሞ “ወሳኝ የአሜሪካ ጦር የሄሊኮፕተር ጥገና ማዕከላትን፣ የፒ8 የኤሌክትሮኒክስ የጦር አውሮፕላን ማቆሚያዎችን እንዲሁም የድሮን ዕዝ እና ቁጥጥር ማዕከልን” መምታቱን ገልጿል።

    ለአብዮታዊ ዘቡ ቅርበት ያላቸው የዜና ወኪሎች ኩዌት ውስጥ ፍንዳታ መሰማቱን የዘገቡ ሲሆን፤ አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ ፍንዳታው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግሯል።

    እንደ የተጀመረው ጥቃት አሜሪካ እና ኢራን ተፈራርመውት የነበረውን የጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ውስጥ ጥሎታል። ይህ ስምምነት ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እንዲሁም ግጭቱ በቋሚነት እንዲቆም የማድረግ ዓላማ ነበረው።

    ይሁን እንጂ አደራዳሪዎች ስምምነቱን በድጋሚ ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።