የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት ባልተለመደ መልኩ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ገለፁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ንቺምቢ፣ ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደገቡ ከተዘገበ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ።

የ54 ዓመቱ ንቺምቢ፣ አጭር የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። የፕሬዝደንቷን ፍላጎት ማክበር እንደሚፈልጉ በደብዳቤያቸው ላይ ገልፀዋል።

የቢሮአቸው እና የፕሬዝደንቷ ጽህፈት ቤት ምንጮች ምክትል ፕሬዝደንቱ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማቅረባቸውን አረጋግጠዋል።

ንቺምቢ ከተሾሙ ከ10 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ገልፀዋል። ይህ ውሳኔ ግለሰቡን በምሥራቅ አፍሪካዋ አገር ታሪክ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጓቸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ጥቅምት ወር በነበረው አወዛጋቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የሳሚያ ተጣማሪ ሆነው ነበር የተሳተፉት።

ሁለቱ መሪዎች 98 በመቶ ድምፅ አግኝተው ማሸነፋቸው ከተገለፀ በኋላ ባለፈው ኅዳር ወር ቃለ መሀላ ፈፅመዋል።

ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ በተነሳ ሁከት ሳቢያ ቢያንስ 500 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን ይፋዊ ምርመራ አረጋግጧል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የፀጥታ ኃይሎች መንግሥትን ተቃውመው በወጡ ሰልፈኞች ከመጠን ያለፈ እርምጃ ወስደዋል በማለት ከሰዋል።

"ፕሬዝዳንቷ ለውጥ እንደሚፈልጉ ያለ ጥርጥር አምናለሁ፤ ስለዚህም የገባሁትን ቃል ለመፈጸም ወስኛለሁ" ሳሚያ ሌላ ምክትል ከፈለጉ እንደሚለቁ ከዚህ ቀደም የገቡትን ቃል በማስታወስ ንቺምቢ በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ ጽፈዋል።

ፕሬዝዳንቷን እና ገዢውን "ቻማ ቻ ማፑንዱዚ (ሲሲኤም/CCM)" ፓርቲ ስለጣሉባቸው እምነት እንዲሁም ታንዛኒያውያንን አሳይተውኛል ስላሉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ንቺምቢ ሥልጣናቸውን የሚለቁት የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሚፈቅደው መልኩ መሆኑን እና በቀጣይነትም "የታንዛኒያ መልካም ዜጋ" ሆነው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ከሳሚያ አስተዳደር ጋር አለመግባባት መፈጠሩን ሊያመለክቱ የሚችሉ አወዛጋቢ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

ባለፈው ወር ታንዛኒያውያን "ለአዲስ ሕገ-መንግሥት እንዲፋለሙ" ጥሪ አቅርበዋል። ከአውሮፓውያኑ 2030 በፊት ይህን ማሳካት እንደሚቻልም ተናግረው ነበር።

አዲሱ ሕገ-መንግሥት ኢፍትሃዊነትን ለመቅረፍ፣ የሰብዓዊ መብቶችን፣ መልካም አስተዳደርን እና ዲሞክራሲን ለማጠናከር እንደሚረዳም በወቅቱ ገልፀዋል።

ንቺምቢ፣ ከዚህ ቀደም የገዢው ፓርቲ የሲሲኤም ዋና ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል። የማስታወቂያ እና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትርን፣ እንዲሁም በብራዚል እና በግብፅ የታንዛኒያ አምባሳደርነትን ጨምሮ በሌሎችም ከፍተኛ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።