ፍልስጤም በ1982 በፓሪስ የአይሁድ ምግብ ቤት ውስጥ ጥቃት ያደረሰ ተጠርጣሪን አሳልፋ ሰጠች

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፈረንሳይ በ1982 በፓሪስ በሚገኝ የአይሁድ ምግብ ቤት ላይ በተፈጸመው የቦምብ እና የጦር መሳሪያ ጥቃት ዋነኛ ተጠርጣሪ የተባለው የ72 ዓመት አዛውንት በቁጥጥር ስር አዋለች።

በዚህ ጥቃት ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።

ሂቻም ሀርብ የተባለው ተጠርጣሪው የፈረንሳይ ብሔራዊ የፀረ-ሽብርተኝነት አቃቤ ሕግ ቢሮ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ሐሙስ ዕለት በፍልስጤም ብሔራዊ ባለሥልጣን ተላልፎ ተሰጥቷል።

ትክክለኛ ስሙ ማህሙድ ካደር አቤድ አድራ የሆነው ሃርብ ጥቃቱን በመምራት እና በምግብ ቤቱ ላይ ከተኮሱት ታጣቂዎች አንዱ በመሆን ተጠርጥሯል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የፍልስጤም ባለሥልጣንን አመስግነው፤ ይህ የፍትህ ትብብር አገራቸው ባለፈው መስከረም ለፍልስጤም እውቅና በመስጠቷ የተገኘው ውጤት "ጠንካራ ማሳያ" ነው ብለዋል።

ተጠርጣሪው በፓሪስ አቅራቢያ በሚገኝ የአየር ኃይል ጣቢያ እንደደረሰ ወደ እስር ቤት ተወስዷል።

ስድስት ሰዎችን ለገደለው ጥቃት እና በታሪካዊ የአይሁድ ሰፈር በተፈፀመ እና 20 ሰዎችን ላቆሰለ ጥቃት እስካሁን ፍርድ ተሰጥቶ አያውቅም።

ጥቃቶቹ በመጀመሪያ ወደ ምግብ ቤቱ ቦምብ በመወርወር ቢያንስ ሦስት የሚሆኑ ታጣቂዎች ከምግብ ቤቱ ሰዎች ለመውጣት ሲሞክሩ በጥይት ደብድበዋቸዋል።

ባለፈው ዓመት የፈረንሳይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በሌሉበት የስድስት ሰዎች የክስ ሂደት እንዲጀመር ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የምግብ ቤቱ ጥቃት ከፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (ፒኤልኦ) ተነጥሎ በወጣው እና በአቡ ኒዳል የሚመራው ቡድን ፈፅሞታል ተብሎ ይታመናል። ይህ ቡድን እ.አ.አ በ1980ዎቹ በግድያ፣ አውሮፕላን ጠለፋ እና በአየር ማረፊያዎች እና መርከቦች ላይ በፈፀማቸው ጥቃቶች የ900 ሰዎችን ሕይወት እንደነጠቀ ይነገራል።

በፓሪሱ የምግብ ቤት ጥቃት ሁለት ተጠርጣሪዎች ፈረንሳይ ይገኛሉ።

ከፍልስጤም ተላልፎ የተሰጠው ሀርብ ልጅ የሆነው ቢላል አል አድራ ቤተሰባቸው ተላልፎ የተሰጠበትን መንገድ ሕገ ወጥ ነው ብሎ የሚያምን ሲሆን፤ ፍትኃዊነት ያለው የፍርድ ሂደት ያገኛል ብለውም እንደማይጠብቁ ተናግሯል።

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖዎል ባሮት ባለፈው ዓመት የሟች ቤተሰቦችን ሲያነጋግሩ ተጠርጣሪዎችን ለፍትህ ለማቅረብ ሁሉም ነገር ይፈፀማል ብለዋል።

ጥቃቱ ከተፀመ ከ44 ዓመታት በኋላ ፍትህ በመጨረሻ ይፈፀማል ተብሏል።

"ፈረንሳይ ፀረ ሴማዊነትን እና ሽብርን ስትጋፈጥ መቼም አትረሳውም፤ መቼም ተስፋ አትቆርምጥም" ብለዋል።