በሕንድ የ11 ዓመት ሕጻን ተደፍራ መገደሏ ለቀናት የቀጠለ ተቃውሞ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው
የ11 ዓመት ሕጻን ተደፍራ መገደሏን ተከትሎ የሕንድ ማዕራብ ባንጋል ግዛት በተቃውሞ እየተናጠ ይገኛል።
የሕጻኗ አስከሬን ባለፈው እሑድ ኩሬ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል።
ሱስጃይፑር በተባለው መንደር ለቀናት በነውጥ የተሞላ ተቃውሞ ተነስቷል። አንድ ንጹህ ሰው በደቦ ሲገደል ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪ ገድሏል።
ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።
ሕጻኗ ተደፍራ መገደሏ እና ተጠርጣሪ የተባለው ሰው መገደሉ የፖለቲካ ውዝግብም አስከትሏል።
ተቃዋሚዎች ቢጄፒ ፓርቲ ሴቶችን መጠበቅ ተስኖታል ሲል ከስሷል።
ታዳጊዋ እንደወጣች ሳትመለስ ስትቀር ለፖሊስ ጠቆሙ። ወላጆቿ እና የመንደሩ ነዋሪዎች እንደሚሉት ፖሊስ ጥቆማውን በቁም ነገር አልወሰደውም።
በአካባቢው ባለ ሱቅ የደኅንነት ካሜራ ላይ ሕጻኗ ፕራዴሽ ማንዳል ከሚባል ሰው ጋር ስትጓዝ ከታየች በኋላ ፖሊስ ግለሰቡን ገድሏል።
እሑድ ጠዋት የመንደሩ ሰው ግለሰቡ ቤት ሄዶ መኖሪያውን በእሳት አጋይቷል። ከዚያም ለፖሊስ አሳልፎ ሰጥቶታል።
ግለሰቡ የሕጻኗ አስከሬን ወዳለበትን ቦታ ፖሊሶችን መርቶ እንደወሰደ ተዘግቧል።
የአስከሬን ምርመራ እንደሚያሳየው ሕይወቷ ያለፈው ውሃ ውስጥ በመስጠሟ ነው። ወደ ኩሬው ስትጣል በሕይወት ነበረች።
ዘመዷ "ፖሊስ ቀድሞ እርምጃ ቢወስድ ትተርፍ ነበር" ብለዋል።
ፖሊስ የቀረበለትን ቅሬታ አሻሽሎ ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ክስ አድርጎታል።
መንግሥት ጉዳዩን የሚመረምር ልዩ ቡድን አቋቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, PTI
የሕጻኗ አስከሬን ከተገኘ በኋላ ነዋሪዎች በቁጣ አደባባይ ወጥተዋል። መንገዶች፣ ሱቆች እና ባቡር ጣቢያ ላይ ጉዳትም አድርሰዋል።
በደቦ የተገደለ ወጣት ንጹህ ሆኖ መገኘቱን የአካባቢው ኃላፊ ሱቫንዱ አድሂካሪ ተናግረዋል።
አደባባይ የወጡትን ሰዎች ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ወቅት በርካታ ፖሊሶች ተጎድተዋል፤ ተሽከርካሪዎችም ወድመዋል።
ሦስት ተጠርጣሪዎች እንደተለዩ እና እስካሁን 40 ሰዎች እንደተያዙ ተገልጿል።
አካባቢው አሁንም በውጥረት እንደተሞላ ነው። ሰዎች እንዳይሰበሰቡ እገዳ የተጣለ ሲሆን፣ ፖሊሶችም በስፋት ተሰማርተዋል።
በምዕራብ ቤንጋል በቅርቡ ሥልጣን የያዘው ገዢው ቢጄፒ በገጠመው ተቃውሞ ፈተና ውስጥ ገብቷል።
በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት አካባቢው ለሴቶች ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሚሆን ቃል ሲገባ ነበር።
ከዚህ ቀደም የነበሩት ፖለቲከኞች የተሸነፉት ሴቶች ላይ በሚደርስ ጥቃት ምክንያት መሆኑን ተንታኞች ሲገልጹም ነበር።
ውጥረቱ በሙስሊሞች እና በሒንዱዎች መካከል የሚፈጠር ክስተት ተደርጎ ሃይማኖታዊ ገጽታም ተሰጥቶታል።
የአካባቢው ኃላፊ ውጥረቱን ለማርገብ የተጎጂዋን ቤተሰቦች ጎብኝተዋል።
"መንግሥታችን እንዲህ ያለ ክስተትን ለማቆም ቁርጠኛ ነው። ፖሊስ የሚጠበቅበትን እያደረገ ይገኛል። ተወዳጅ ልጃቸውን ያጡት ወላጆችን ስላነጋገርኳቸው ደስተኛ ሆነዋል" ብለዋል።
በፖሊስ የተገደለው ተጠርጣሪ ወደ ኩሬው ተወስዶ እንዴት ድርጊቱን እንደፈጸመ እንዲያሳይ ሲጠየቅ ከፖሊስ መሣሪያ ሊነጥቅ እንደሞከረ ተናግረዋል።
ፖሊስ ተኩሶበት ከተጎዳ በኋላ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱ አልተረፈም። ስለ ጥፋተኛነቱ ማስረጃ ባይቀርብም እናቱ ልጃቸው መሆኑን በመካድ አስከሬኑን ላለመቀበል ወስነዋል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ግድያው ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ አንስተዋል።















