ሊቀ ጳጳስ ሊዮ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት የሚያወጡ 'አምባገነኖች'ን ተቹ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሊቀ ጳጳስ ሊዮ በካሜሮን ጉብኝታቸው ወቅት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት የሚያወጡ መሪዎችን ተቹ።
ዓለም "በጥቂት አምባገነኖች እየተናጠች ነው" ሲሉ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ ለጦርነት በቢሎዮኖች የሚያወጡ የዓለም መሪዎችን ባልተለመደ ሁኔታ ተችተዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በጦርነት ክፉኛ በተጎዳው ቀጣና እያደረጉት ባለው ጉብኝት ወቅት "የእግዚአብሔርን ስም" ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚጠቀሙ ሰዎችን አውግዘዋል።
ይህ የጳጳሱ አስተያየት የተሰማው ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ከተፈጠረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
ትራምፕ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ወታደራዊ ዘመቻን አጥብቀው የሚያወግዙትን ሊቃነ ጳጳስ የሚነቅፍ ረዘም ያለ መልዕክት በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።
ሊቃ ጳጳሱ ኢራን ጦርነቱን ለማቆም የአሜሪካን መደራደሪያዎች ካልተቀበለች እና የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ካልከፈተች "ሙሉ ስልጣኔዋ ይወድማል" ማለታቸውን ተከትሎ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተሾሙት አሜሪካዊው ሊዮ፣ የትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ረገድ ስላለው አቋም ቀደም ሲል ጥያቄ አንስተው ነበር።
"ሊዮ እንደ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እርምጃቸውን ማጤን አለባቸው" ሲሉ ትራምፕ በወቅቱ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ለጥፈው ነበር።
ሊቃ ጳጳሱ በአፍሪካ ጉብኝታቸው መጀመሪያ ላይ ለጋዜጠኞች ከትራምፕ ጋር ክርክር ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ ተናግረው ነገር ግን ሰላምን ማበረታታታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ በካሜሩን ንግግር ሲያደርጉ "በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለግድያና ለውድመት ሲውል እንዳላየ የሚያልፉ" መሪዎችን ተችተዋል።
አክለውም "ነገር ግን ለፈውስ፣ ለትምህርትና ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልጉ ሀብቶች የትም አይገኙም" በማለት ያለውን ተቃርኖ በንግግራቸው ውስጥ ለማሳየት ሞክረዋል።
"የጦርነት ጌቶች ለማፍረስ ቅጽበቶች ብቻ እንደሚፈጅ የማያውቁ ያስመስላሉ፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደገና ለመገንባት የሕይወት ዘመን ብቻ በቂ አይሆንም" ሲሉ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ ሊዮ ለአስር ዓመታት ያህል በጦርነት የሚታመሰውን የካሜሩን ክልል ውስጥ "ማለቂያ የሌለው አለመረጋጋት እና የሞት ሽክርክሪት" በማለት አውግዘዋል።
"መሬታችሁን ሀብቶቻችሁን የሚዘርፉ ሰዎች አብዛኛውን ትርፍ በጦር መሳሪያዎች ላይ ያፈሳሉ፤ በዚህም ማለቂያ የሌለውን የብጥብጥ እና የሞት ሽክርክሪታቸውን ያስቀጥላሉ" ሲሉ በሰሜን ምዕራብ ከተማ ባሜንዳ በሚገኝ ካቴድራል ለተሰበሰቡት ሰዎች ተናግረዋል።
በአካባቢው ለዓመታት በቀጠለው ግጭት ቢያንስ 6,000 ሰዎችን ለሞት እና ለብዙዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
"ሰላም የምንፈጥረው ነገር አይደለም፤ ጎረቤታችንን እንደ ወንድም እና እንደ እህታችን በማየት ልንቀበለው የሚገባ ነገር ነው" ሲሉ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ ተናግረዋል።
በካሜሮን ሁለት እንግሊዘኛ ተናጋሪ ክልሎች ከፈረንሳይኛ ተናጋሪ መንግሥት ለመነጠል እአአ ከ2017 ጀምሮ እየተዋጉ ይገኛሉ።
የሊዮን ንግግር ተከትሎ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ሳራ ሙላሊ "ለሰላም መንግሥት ባደረጉት ድፍረት የተሞላበት ጥሪ" ከሊቀ ጳጳሱ ጎን እንደቆሙ ተናግረዋል።
በኢራን የተቀሰቀሰው ጦርነት ጳጳሱን እና የትራምፕ አስተዳደርን ወደ ቃላት ግጭት ከትቷቸዋል።
ፖፕ ሊዮ የመጀመሪያው አሜሪካዊ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፤ በኢራን የተከፈተውን ጦርነት በተደጋጋሚ ተችተዋል።
ፖፕ ሊዮ የትራምፕን አስተዳደር ወይም የወንጌሉን መልዕክት ጮክ ብለው መናገር ላይ "ምንም ፍርሃት" እንደሌላቸው ሰኞ ዕለት ተናግረው ነበር።
ትራምፕ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ላቀረቡት ትችት ይቅርታ አልጠየቁም።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ጳጰሱ ኢራን በተለይ የኒውክሌር መሣሪያ ካገኘች "ለዓለም ስጋት መሆኗን" ማወቅ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ በዋይት ሐውስ "ጳጳሱ የሚፈልጉትን ማለት ይችላሉ፤ እኔም የሚፈልጉትን እንዲናገሩ እፈልጋለሁ፤ ነገረ ግን ልስማማ አልችልም" ብለዋል።
ጳጳሱ በአፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታ በአራት አገራት 11 ከተሞችን ይጎበኛሉ። ከዓለም አንድ አምስተኛው የካቶሊክ እምነት ተከታይ፣ 288 ሚሊዮን ያህሉ የሚገኘው በአፍሪካ ነው።















