ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቃል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Xinhua
የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ የሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ሁለተኛ ቀኑን በያዘበት ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቃል ገቡ።
ዢ ጂንፒንግ ጉብኝታቸው ለሁለቱም አገራት የወደፊት ግንኙነት መልካም ዕድልን ይፈጥራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ኪም በበኩላቸው አገራቸው ከቻይና ጋር የምታደርገው ግንኙነት "ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ" መሆኑን መናገራቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ኤሲኤንኤ ዘግቧል።
ዢ ከ2019 ወዲህ የመጀመሪያው ጉብኝታቸው መዳረሻ ፒዮንግያንግ መሆኗ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያሳያልም ብለዋል።
ኪም ጨምረውም የቤጂንግን አንድ ቻይና ፖሊሲ እንዲሁም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን ፖሊሲዎች እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
የቻይና መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ዢ ሁለቱ አገራት መዳረሻቸው አንድ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን ከኪም ጋር ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።
ዢ ሰኞ ዕለት ሰሜን ኮሪያ ሲገቡ በኪም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ዛሬም መሪዎቹ በኮሪያ ጦርነት ሲዋጉ የሞቱ ቻይናውያን ወታደሮች መታሰቢያን እንዲሁም የአገሪቷን ከፍተኛ የፖለቲካ ትምህርት ተቋም ጎብኝተዋል።
ቤጂንግ የራሷ ሞዴል የሆነውን የኮሚኒስት አመራር ሰሜን ኮሪያም እንድትቀበል ለረዥም ጊዜ ስታበረታታ ቆይታለች።
በቻይና እና በሰሜን ኮሪያ ያለው የረዥም ጊዜ ግንኙነት የጥርስ እና የከንፈር ያህል እንደሆነ ይገለፃል። ሆኖም ግንኙነታቸው እጅግ ውስብስብ ነው።
አንድ ሺህ ኪሎሜትር የሚሸፍን ድንበር የሚጋሩት ሁለቱ ጎረቤታሞች በመከላከያ ረገድ በጋራ ይሰራሉ።
ይህም ቻይና ከሌላ አገር ጋር ያላት ብቸኛው ስምምነት ነው። ስምምነቱ ከሁለት አንዳቸው ላይ ጥቃት ቢፈፀም በጋራ እንዲከላከሉ ይፈቅዳል። ይህ ስምምነት 65ኛ ዓመቱን ይዟል።
ከዚህም በተጨማሪ ቻይና የሰሜን ኮሪያ ትልቅ የንግድ አጋር ነች። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰሜን ኮሪያ ዓለም አቀፍ ንግድ ከቻይና ጋር የሚደረግ ነው። ይህም በኒውክሌር ፕሮግራሟ የተነሳ ሰፊ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ላጋጠማት ፒዮንግያንግ የህልውናዋ መሠረት ነው።
ምንም እንኳን ቻይና ለሰሜን ኮሪያ በቀጥታ የጦር መሣሪያ ባትሸጥም፣ ለሲቪልም ሆነ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሣሪያዎችን ለአገሪቷ እንደምታቀርብ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ቤይጂንግ ከፒዮንግያንግ እና ጎረቤቷ ሞስኮ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ቢኖራትም፣ ዢ በኪም እና በሩሲያው ፕሬዚደንት ፑቲን መካከል ያለው ግንኙነት በፍጥነት እየተጠናከረ በመምጣቱ ስጋት እንደገባቸው የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።
ለቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ሰሜሪን ኮሪያ መቆጣጠር የማትችላት ወይም ልታጣት የማትችላት ጎረቤቷ ናት።
ሁለቱ አገራት በተደጋጋሚ ወዳጅነታቸውን "በደም የተመሰረተ" ሲሉ የኮሪያን ጦርነት በመጥቀስ ይናገራሉ።















