የኔቶ አገራት ለሚሳዔል ልማት 50 ቢሊዮን ዶላር መደቡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 12 አገራት አውሮፓን ለመጠበቅ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለረጅም ርቀት ሚሳዔል 50 ቢሊዮን ዶላር ሊያወጡ ነው።
ፕሮጄክቱ በዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ይፋ የተደረገ ሲሆን በሚቀጥለው ሣምንት ረቡዕ በቱርክ አንካራ ከተማ በሚካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ኪር ስታርመር በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጨረሻቸውን የኔቶ ስብሰባ ለመታደም አንካራ ገብተዋል።
ባለፈው ዓመት በኔቶ አባላት ስምምነት የተደረገበትን የመከላከያ ወጪ ባለማሟላታቸው ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትችት ይገጥማቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ የፊታችን ረቡዕ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች መሪዎች ጋር ስለ አዲሱ የሚሳዔል መርሃ ግብር ለመምከር ይቀመጣሉ።
እጅግ የረቀቀ የጦር መሣሪያ የተባለው አዲሱ የኔቶ ፕሮጀክት ከ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዒላማዎቹን ለይቶ መምታት የሚችል እንዲሁም እስከ 2,000 ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘግ እንደሆነ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በዩናይትድ ኪንግደም የሚመራው መርሃ ግብሩ "የአውሮፓ አገራትን በማሰባሰብ ኔቶን በመጪዎቹ ዓመታት ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው" ብለዋል።
ይሁን እንጂ እንደ ሌሎቹ በእቅድ ላይ ያሉ ወታደራዊ ፕሮጀክቶች ሁሉ 'ዲፕ ስትራይክ' የሚል ስያሜ የተሰጠው መርሃ ግብር ከአውሮፓውያኑ 2030 በፊት ዝግጁ አይሆንም።
ባለፈው ሰኔ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በአውሮፓ የሚገኙ ኃይሎች ላይ የስድስት ወራት ግምገማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአውሮፓ የመከላከያ ወጪ ላይ የኔቶ አባል አገራት የበለጠ መዋጮ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በተደረገው የኔቶ ጉባኤ የጥምረቱ አባላት እስከ 2035 ድረስ ከጠቅላላ ምርታቸው አምስት በመቶውን ለመከላከያ እና ደኅንነት እንዲመድቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኪር ስታርመር የዩናይትድ ኪንግደምን እና አጋሮቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ "ቁርጠኛ" እንደሆኑ ተናግረዋል። "ጠንካራ እና አውሮፓዊ የሆነ ኔቶን ለማቅረብ መስራት አለብን" ብለዋል።
የዩኬ መንግሥት በመከላከያ እቅዱ እስከ 2030 ድረስ 300 ቢሊዮን ፓውንድ ገንዘብ መድቧል።
በኔቶ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ሩሲያ በዩኬ እና በኔቶ ላይ የደቀነችውን ስጋት በደንብ ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዩኬ መንግሥት ኔቶ የአየር ክልሉን የሚጥሱ የሩሲያ አውሮፕላኖችን ለመመለስ ከ700 ጊዜ በላይ ተዋጊ ጄቶችን ለማሰማራት እንደሞከረ እና በዩኬ የውሃ አካባቢዎች የሩሲያ ታደራዊ እንቅስቃሴ በ30 በመቶ መጨመሩን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ኔቶ ከሩሲያ ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥ ባይፈልግም አጋሮቹን ለመከላከል ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልገው ግን ያስረዳሉ ተብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በኔቶ ጉባኤ እያገረሸ ካለው የሩሲያ ጥቃት አገራቸውን ለመከላከል አጋሮቻቸው የአየር መከላከያ ስርዓት በአስቸኳይ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የኔቶ ጉባኤን በቅርበት እንደሚከታተሉ ተናግረዋል።
ኪየቭ ከኔቶ የምታገኘው አዲስ መሣሪያ ሩሲያ ግቧን ለማሳካት ከምትወስደው ወታደራዊ ተልዕኮ ወደ ኋላ የሚመልስ አይሆንም ብለዋል።















