ደቡብ አፍሪካ ሕገወጥ ስደተኞች ላይ ዘመቻ ከከፈተች ወዲህ 53,000 የውጭ ዜጎች ተባረሩ

ተቃዋሚ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, EMMANUEL CROSET / AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በደቡበ አፍሪካ የተለያዩ ከተሞች በአገሪቱ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች ለቅቀው እንዲወጡ የሚጠይቁ ሰልፎች ተካሄደዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአምስት ሳምንታት በፊት "የስደተኞች አስተዳደር" ላይ ዘመቻ ከከፈተ በኋላ ከ53,000 በላይ የውጭ ዜጎች ከአገር መባረራቸውን ወይንም እንዲወጡ መደረጋቸውን አስታወቀ።

እነዚህ ስደተኞች ከማላዊ፣ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ የመጡ መሆናቸውን የገለጹት ባለሥልጣናቱ፤ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ለተከታታይ ሳምንታት ጸረ ስደተኛ ሰልፎች ከተካሄዱ እንዲሁም አለመረጋጋት፣ ማስፈራራት እና ዘረፋ ከተፈጸመ በኋላ በአገሪቱ ያለ ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሚገኙ ስደተኞች ላይ ሰፊ የተባለ ዘመቻ እያካሄደች ትገኛለች።

ተቃዋሚዎች በአገሪቱ ለተፈጠረው በርካታ የሥራ አጥ ቁጥር፣ የወንጀል መስፋፋት እና የሕዝብ አገልግሎቶች መዳከም ሰነድ አልባ ስደተኞችን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ጥብቅ የሆነ የድንበር ቁጥጥር እንዲኖር እንዲሁም በርካቶች ከአገር እንዲወጡ ይፈልጋሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስደተኞችን ለደቡብ አፍሪካ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደ ሰበብ መጠቀምን አስጠንቅቋል።

ጸረ ስደተኛ አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች መንግሥት ጥያቄያቸውም እስኪመልስ ድረስ ጫና ለመፍጠር በየሳምንቱ ሰልፎችን እንደሚያካሄዱ ዝተዋል። ተቃውሞዎቹ ወደ አመጽ ሊቀየሩ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ጨምረዋል።

ሰልፈኞቹ ሁሉም ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እስከ ሰኔ 23 2018 ዓ.ም. ድረስ "ይፋዊ ያልሆነ የጊዜ ገደብ" ሰጥተው ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙ የውጭ ዜጎች ብጥብጥ እና ማስፈራሪያዎችን ለማምለጥ በፍጥነት ለቅቀው ወጥተዋል።

ባለፊት ሳምንታት ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ እና ኬንያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ዜጎቻቸውን ወደ አገራቸው አጓጉዘዋል።

የፍትህ እና የሕገ መንግሥት ልማት ሚኒስትር ምማሞሎኮ ኩባዪ እሁድ ዕለት እንዳስታወቁት 53,499 የውጭ ዜጎች ከአገር እንዲወጡ እና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፤ "የማላዊ፣ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ ዜጎች በብዛት ይገኙበታል" ብለዋል።

"በአገራችን ውስጥ ያሉ ሰዎች የዜግነት እና የኢሚግሬሽን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የሰብዓዊ መብቶችን እና ክብርን በጠበቀ ሁኔታ ሕዝባችን ለሚያነሳቸው ስጋቶች ተገቢውን ትኩረት የሚሰጥ ሥርዓት ያለው እና መደበኛ ፍልሰት እንዲኖር ለማድረግ እየጣርን ነው" ሲሉ ኩባዪ በፕሪቶሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ከአገር ማስወጣቱ ሂደት በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ የሚፈለጉ ሰዎችን ለመያዝ እንደረዳቸው ጨምረው አስረድተዋል።

ባለሥልጣናት የኢሚግሬሽን ሕጎቹን ማስፈጸማቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረው ተቃዋሚዎች ሰነድ አልባ ስደተኞችን በማስጠለል የተጠረጠሩ ቤቶችን እና የንግድ ድርጅቶችን ያለፍቃድ መፈተሽ እንደሌለባቸው አስጠንቅቀዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሕዝቡ ስለ ስደተኞች ስጋት እንዳለው ተናግረው ነገር ግን ዜጎች ሕጉን በራሳቸው እጅ እንዳያስፈጽሙ በማስጠንቀቅ በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ውስጥ እጅግ ሀብታም ከሚባሉ አገራት መካከል ስትሆን ለረዥም ጊዜ የተሻሉ ሥራ እና ኢኮኖሚ የሚፈልጉ ስደተኞችን ስትስብ ቆይታለች።

አንዳንዶቹም በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ናቸው።