ከዓለም ዋንጫ የወጣችው ሴኔጋል የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኟን አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በዘንድው የዓለም ዋንጫ በ32ቱ የዙር ማጣሪያ ከውድድሩ መውጣቱን ተከትሎ አሰልጣኙ ፓፔ ቲያው ተሰናበቱ።
ከታኅሳስ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአሰልጣኙ ቲያው ሲመራ የቆየው ቡድን፤ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች በፈረንሳይ እና በኖርዌይ ተሸንፏል።
በሦስተኛው ጨዋታቸው ኢራቅን 5 ለ 0 ማሸነፋቸው ከምድቡ በጥሩ ሁኔታ ያጠናቀቁ ሦስተኛ ቡድን ስላደረጋቸው ወደ ጥሎ ማለፍ ተሻግረዋል።
32 ቡድኖች በተጫወቱበት የጥሎ ማለፍ ውድድር የተጋጠሙት ከቤልጂየም ጋር ነበር። ሴኔጋል በዚህ ግጥሚያ ቤልጂየምን 2 ለ 0 እየመራች ብትቆይም በኋላ ላይ በተቆጠረባቸው ሁለት ግብ እና በጭማሪ ሰዓት በተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምት የተነሳ ወድቃለች።
ከውድድሩ ከተሰናበቱ በኋላ የቡድኑ አማካይ ተጫዋች ፓፔ ጉዬ፤ አሁን ያለው የአመራር ኃላፊነት ላይ እስካለ ድረስ ለሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ከመጫወት "እረፍት እንደሚወስድ" ተናግሮ ነበር።
የሰኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ፤ "የብሔራዊ ቡድኑ ስፖርታዊ ውጤቶች እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ካደረገው ጥልቅ ምዘና በኋላ"፤ "ለሴኔጋል እግር ኳስ የተሻለ ጥቅም" ሲል አሠልጣኙን ቲያውን ማሰናበቱን አስታውቋል።
ሴኔጋል በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊነቷ ተነጥቆ ለሞሮኮ መሰጠቱን በመቃወም አቤቱታ ካቀረበች በኋላ ነበር። አሠልጣኙ ቲያው ለዚህ አፍሪካ ዋንጫ ውሳኔ የውዝግብ ማዕከል ነበሩ።
ጥር ላይ በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ በጭማሪ ሰዓት ለሞሮኮ ፍጹም ቅጣት ምት መሰጠቱት የተቃወሙት አሠልጣኝ ቲያው ቡድኑን ከሜዳ አስወጥተው ነበር።
ከ17 ደቂቃ መዘግየት በኋላ ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ ሲመለሱ የተመታውን ፍጹም ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ብራሂም ዲያዝ አድኖታል። አማካዩ ጉዬ ደግሞ በጭማሪ ሰዓት የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሯል።
በኋላ ላይ ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፤ የሴኔጋል ተጫዋቾች ከሜዳ በመውጣታቸው ውጤቱን የቀለበሰ ሲሆን አሸናፊነቱንም ለሞሮኮ ሰጥቷል።
ሴኔጋል ሻምፒዮንነቱን መልሳ ለማግኘት ለዓለም አቀፉ የስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) ይግባኝ አቅርባለች።















