ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሙቀት ምክንያት ከ2,700 በላይ ሰዎች ሞተው ሊሆን እንደሚችል ተገለጸ

ፀሐይ ስትጠልቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በግንቦት እና ሰኔ ወራት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በተመዘገበው እጅግ ከፍተኛ ሞቃት አየር ሁኔታ፤ ከ2,700 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ግምታቸው አስቀመጡ።

ከኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን፣ የሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት እንዲሁም ለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜድስን የተወጣጡ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት ይህ ቁጥር ከፍተኛ ሙቀት የሚያስከትላቸው አደጋዎችን በተመለከተ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

በርካታ ሞቶች ተከስተው ሊሆን የሚችለው በእንግሊዝ ታሪክ ከፍተኛ የሆነው 37.7 ዲግሪ ሴሊሺዬስ ሙቀት በተመዘገበበት ሰኔ ወር እንደሚሆን ተገልጿል።

በዚያ ወቅት ባልተለመደ ሁኔታ በተወሰኑ የእንግሊዝ እና ዌልስ አካባቢዎች 'ቀይ' ደረጃ የተቀመጠ የሙቀት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር።

ግንቦት ላይ የታየው 35.1 ዲግሪ ሴሊሺዬስ ሙቀት በአውሮፓውያኑ 1922 እና 1944 ከፍተኛ ሆኖ ከተመዘገበው 32.8 ዲግሪ ሴሊሺዬስ የበለጠ ነበር።

በእነዚህ ወራት ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበው በከፍተኛ ግፊት ምክንያት ሞቃት አየር በአንድ አካባቢ ላይ ተከማችቶ እንዲቀር በሚያደርግ የአየር ሁኔታ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። እንደ ባለሙያዎች ገለጻ፤ ይህ የሙቀት ክምችት የተባባሰው በሰው ሰራሽ አየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ምድር የኢንዱስትሪ አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት ከነበረችበት ደረጃ ከፍ ባለው በ1.4 ዲግሪ ሴልሺየስ ሞቃት እያደረጋት ነው። በግንቦት እና ሰኔ ወራት የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ደግሞ የሙቀጥ መጠኑን ከ3 እስከ 4 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዲጨምር ማድረጉን ተመራማሪዎች ያምናሉ።

በርካታ የዩናይትድ ኪንግደም መኖሪያ ቤቶች ይህንን ዓይነት ሙቀት ለመቋቋም የተሰሩ ባለመሆናቸው ሰዎች ለተራዘመ እና ከፍተኛ ሙቀት ተጋልጠዋል።

ሙቀት በሰውነት ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጫና የሚፈጥር ሲሆም በሰውነት ውስጥ ያለው የፈሳሽ መጠን ከቀነሰ ሁኔታው ይባባሳል። የዚህም አንዱ ምክንያት ሰውነታችን ለመቀዝቀዝ ሲል የልብ ምት ጥንካሬ እና ፍጥነትን የሚጨምር መሆኑ ነው።

ለዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ህጻናት እና አረጋውያን እንዲሁም ሌላ የጤና ሁኔታ ያለባቸው ሰዎች ናቸው።

የሙቀት መጨመር የልብ ድካም፣ ስትሮክ እና ሌሎች ለሞት የሚዳርጉ ክስተቶች ሊያጋልጥ ይችላል።

ከፍተኛ ሙቀት የተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው እና ጤነኛ ሰዎችን ጭምር አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሚያሳያቸው ምልክቶች ችላ ሊባሉ የሚችሉ ስለሆኑ 'ዝምተኛው ገዳይ' ተብሎ ይጠራል።