የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ላይ የቴስቶስትሮን እጥረት ምርመራ ሊደረግ ነው

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት 30 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወታደሮች ላይ የቴስቶስትሮን እጥረት ምርመራ እንደሚደረግ አስታወቁ።

ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ቪዲዮ፣ "ትክክለኛ የቴስቶስትሮን መጠን እንዳለ ለማረጋገጥ" በወታደሮቹ ላይ ለሚደረገው የምርመራ ፕሮግራም ፈቃድ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ምርመራው የሠራዊቱ አባላት ዓመታዊ የጤና ምርመራ አካል እንደሚሆን ተናግረዋል።

ዝቅተኛ የቴስቶስትሮን መጠን ያላቸው ወታደሮች ፈቃደኛ ከሆኑ ሆርሞናቸውን የሚተካ ሕክምና ይሰጣቸዋል።

ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ምርመራውን እንዲያደርጉ የማይገደዱ ሲሆን በምርጫቸው ግን ምርመራውን ማድረግ ይችላሉ።

ሄግሴት፤ ምርመራው ዕድሜያቸው ሲጨምር የቴስቶስትሮን መጠናቸው በሚቀንሰው ሴቶች ላይ ይደረግ እንደሆነ አልገለጹም።

" ለተዋጊዎቻችን በዓለም ላይ በጣም ጥሩ የሆነ ሕክምና እንሰጣለን፤ እናም ይህ ፕሮግራም ይህንን ግዴታ ይወጣል" ሲሉም ሄግሴት ረቡዕ ዕለት ባጋሩት ቪዲዮ ላይ ገልጸዋል።

"ጤናችሁን በዘላቂነት መጠበቅ ጠንካራ፣ ችግር የሚቋቋም እና ብቁ መሆናችሁን ያረጋግጣል። ለቀጣይ ስምሪታችሁ ብቻ ሳይሆን ለቀሪው ሕይወታችሁ። ስለዚህ ከውትድርና ከተገለላችሁ በኋላም ብዙ መቆየት ትችላላችሁ" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ጦር፤ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ጡንቻ ለማፈርጠም እና ለሌሎች ሕክምና ላልሆኑ አገልግሎቶች ቴስቶስትሮንን መውሰድን ጥብቅ ይከለክላል።

ሄግሴት፤ አዲሱ ፕሮግራም ሰው ሰራሽ የጡንቻ ማፈርጠሚያ እንዳልሆነም በለቀቁት ቪዲዮ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሲን ፓርንል በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት አስገዳጅ የሆነው የቴስቶስትሮን እጥረት ምርመራ እድሜያቸው 30 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ በሥራ ላይ ላሉ እንዲሁም ተጠባባቂ ለሆኑ ወታደሮች መመሪያው ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል።

መመሪያው መሥሪያ ቤቱ የተሟላ መሠረት እና ለሚያስፈልጋቸው ወታደሮች የቴስቶስትሮን ሕክምና ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ይህም "ጤናማ ፣ ብቁ እና የማይገር ጠንካራ ተዋጊ ኃይል እንዲፈጠር ያደርጋል" ሲሉም አክለዋል።

ሴቶችም፣ ወንዶቹም ምርመራ ይደረግላቸው እንደሆነ የተጠየቁት ቃል አቀባዩ፣ ሴት ወታደሮች ወደ እርጣት ጊዜያቸው ሲቃረቡ የኦስትሮጅን መጠናቸው ላይ ምርመራ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በኢራቅ ጦርነት ተዋጊ የነበሩት እና የጦር አገልግሎት ኮሚቴ አባል የሆኑት ዲሞክራቱ ሴናተር ታሚይ ደክዎርዝ፣ የሆርሞን ምርመራው ለሴቶችም ለወንዶችም ተደራሽ እንዲደረግ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የፔንሲልቫኒያ የዲሞክራት ተወካይ እና የቀድሞ አየር ኃይል ተዋጊ ክሪሲይ ሆውላሃን፣ 'የባህል ጦርነት ሱስ' ያሉትን የሄግሴትን እቅድ አጣጥለዋል።

ባለፈው ዓመት በወታደራዊ አገልግሎት ውስጥ የቴስቶስትሮን አጠቃቀምን በተመለከተ በተደረገ ውይይት የባለሙያዎች ቡድንን የመሩት የአሜሪካን ምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር ዶክተር ሞሂት ክሄራ በበኩላቸው፣ ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች ምርመራ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የአንድን ግለሰብ አሁናዊ እና የወደፊት የጤና ሁኔታን ከሚወስኑ ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉም ወንዶች ምርመራ ሊደረግላቸው ይገባል" ብለዋል።

በባይለር የሕክምና ኮሌጅ የዩሮሎጂስትፕሮፌሰር የሆኑት ኬራ " እዚህ ላይ ያለው ቁልፍ ጉዳይ በርካታ ወጣት ወንዶች ዝቅተኛ የቴስቶስትሮን መጠን አላቸው፤ ይህም ጡንቻን የሚያላላ እና ጉልበትን የሚያዳክም ሲሆን በውጊያ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል" ሲሉ አስረድተዋል።

ሆኖም የእጥረት ምልክት ላልታየባቸው ቴስቶስትሮን እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚያብራሩት ሆርሞኑን ለመተካት የሚሰጠው ሕክምና ጡንቻን ያፈረጥማል፤ የስብ ክምችትን ይቀንሳል እንዲሁም ለድብርት የመጋለጥ ዕድልን ይቀንሳል።

በጊዜ ሒደትም የአጥንት ጤናን ለመጠበቅ ይረዳል ብለዋል።

" ወጣት ወንዶች ቴስቴስትሮን ከወሰዱ መካን ሊያደርጋቸው ይችላል" የሚሉት ኬራ፣ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ እና ሆርሞኑን መውሰድ የሚፈልጉ ወጣት ወንዶች የሚያስከትለው ችግር አስቀድሞ ሊነገራቸው እንደሚገባ መክረዋል።

ከመካንነት በተጨማሪም ለአጥንት እና ለነርቭ ሥርዓት እክል ሊያጋልጥም ይችላል።

ሄግሴት በጦራቸው ውስጥ የቴስቶስትሮን ምርመራ እንደሚደረግ ያስታወቁት የአሜሪካ የጤና ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጀር እና ሌሎች የአስተዳዳሩ ባለሥልጣናት የጤና ባለሙያዎች ለወንዶች የቴስቶስትሮን ማዘዣ ለመስጠት የሚገጥማቸውን እንቅፋት ማስወገድ እንደሚፈልጉ ከገለጹ በኋላ ነው።

የጤና ሚኒስትሩ ይህ በአገሪቱ ያለውን "የመካንነት ቀውስ" መፍትሔ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፈው ወር የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደሩ በቴስቴስትሮን መተኪያ ሕክምና ላይ የተቀመጠው የደኅንነትና ውጤታማነትን የተመለከቱ መግለጫዎች እንዲነሱ የጠየቀ ሲሆን ይህም የቴስቴስትሮን ምርቶችን ለማዘዝ ያሉ ገደቦችን ያላላል ብሏል።