ሁለት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ደቡብ ሱዳን ውስጥ በታጣቂዎች ተገደሉ

የኢትዮጵያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Embassy Juba

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮ 1,300 ገደማ ወታደሮችን ማዋጣቷን የተመድ የ2017 ዓ.ም. መረጃ ያሳያል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በፈጸሙት "የደፈጣ ጥቃት" ሰላም ማስከበር ላይ የተሰማሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

ወታደሮቹን "ዒላማ" እንዳደረገ በተገመተው በዚህ ጥቃት፣ ሌሎች ሦስት የሰላም ማስከበር ኃይሎችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ አባላት የሆኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው፣ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ትናንት ሰኞ ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም. ጆንግሌ ግዛት ውስጥ ወደሚገኝ 'ፓጁት' የተባለ አካባቢ እየተጓዙ በነበረበት ጊዜ ነው።

ወደታሮች የተሰማሩት "በአካባቢው በቀጣይነት የዘለቀውን የፀጥታ ችግር" ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት አካል ሆነው እንደነበር የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

"ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ጥቃቱ ሰላም አስከባሪዎቹን "ዒላማ ያደረገ እንደሚመስል" ገልጸዋል።

በዚህ ጥቃት "ሁለት ሰላም አስከባሪዎቻችን ተገድለዋል፤ ሰባት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብለዋል። "የተገደሉት ሁለት ሰላም አስከባሪዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው" ሲሉም አክለዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል የሆኑት ሦስት ሰላም አስከባሪዎች ዜግነት አልተገለጸም። ሌሎቹ ተጎጂዎች ሁለት የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አባላት እና ሁለት ሲቪሎች እንደሆኑ ተገልጿል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን ጥቃት ማውገዛቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ዋና ፀሐፊው ለተገደሉት "ሰላም አስከባሪዎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻሉ። የተጎዱት በሙሉ በቶሎ እንዲያገግሙም ይመኛሉ" ሲሉም መልዕክት አስተለልፈዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ በበኩሉ በተናጠል ባወጣው መግለጫ፤ የተፈጸመውን "የደፈጣ ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዝ" አስታውቋል። "ተልዕኮው የአካባቢውን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ለሚካሄደው የአደጋ ጊዜ ምላሽ እገዛ ለማድረግ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ኃይሎችን" እንዳሰማራ ገልጿል።

በደቡብ ሱዳን የተመድ ዋና ፀሐፊ ልዩ ተወካይ እና የሰላም ማስከበር ተልዕኮው ኃላፊ አኒታ ኪኪ ጌሆ "ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሰላምን ለማስፈን በሚያገለግሉ የተልዕኮው ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ እንዲህ ዓይነቱ ገዳይ ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

ተልዕኮው ባወጣው መግለጫ በተመድ ሰላም አስከባሪዎች ላይ የሚፈጸም ይህ ዓይነቱ ጥቃት "በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የጦር ወንጀል" ሊሆን እንደሚችል ጠቅሷል።

የተልዕኮው ኃላፊም፣ "የሚመለከታቸው አካላት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍትሕ እንዲቀርቡ ጥልቅ እና ፈጣን ምርመራ እንዲያካሂዱ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን በሰላም አስከባሪነት በተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች መገደላቸውን በተመለከተ እስካሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠ መረጃ የለም።

የተመድ መረጃ እንደሚያሳየው አሁኑ ጨምሮ ከጥር ወዲህ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ዘጠኝ የደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪዎች ተገድለዋል።

ደቡብ ሱዳን ነጻ አገርነቷ ማወጇን ተከትሎ ከ15 ዓመት በፊት በሐምሌ 2003 ዓ.ም. የተቋቋመው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ ሰላማዊ ሰዎችን የመጠበቅ እና በአገሪቱ ፖለቲካዊ አመጽ እንዳይባባስ የመከከላል ኃላፊነት አለበት።

የተባበሩት መንግሥታት በ2017 ዓ.ም. ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮ 1,300 ገደማ ወታደሮችን አዋጥታለች።