አሜሪካ በቴህራን ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ስትገልጽ፣ ኢራን በባሕረ ሰላጤው የሚካሄዱ የነዳጅ ግብይቶችን ለማቋረጥ ዛተች

የፎቶው ባለመብት, AP
አሜሪካ፣ የኢራንን የንግድ አጋሮች ዒላማ ያደረጉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ሰኞ ዕለት ለመጣል ስትዘጋጅ፤ "እስካሁን ከተደረጉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛው የፋይናንስ ጥቃት" ብላ በጠራችው እርምጃ ኢራንን አስፈራራች።
ኢራን በበኩሏ “የምጣኔ ሃብት ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ” በባሕረ ሰላጤው የሚካሄዱ የትኛውንም የነዳጅ ግብይቶች እንደምትዘጋ አስጠንቅቃለች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ሰኞ ዕለት ረፋዱ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካ አሁን ለመጣል እየተዘጋጀች ያለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ እስላማዊ አብዮቱ እአአ በ1979 ከተመሰረተ ወዲህ አጋጥሞት የማያውቅ ነው ተብሏል።
ቤሴንት በፋይናንሻል ታይምስ ላይ እሁድ ዕለት በታተመላቸው ጽሑፍ ላይ “[ሰኞ] ማለዳ አንድ ወሳኝ የኢኮኖሚ ጥቃት ይጀመራል፤ ይህም በአንድ ተቀናቃኝ ላይ እስካሁን ከተሰነዘሩት ሁሉ እጅግ የከፋው የፋይናንስ ጥቃት ነው።” ብለዋል።
አሜሪካ እና ኢራን ለሳምንታት የተኩስ ልውውጥ ያላደረጉ ቢሆንም ለስድስት ወር የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም ተጨባጭ የሆነ ንግግር አላደረጉም።
እሁድ ዕለት የኢራን የደኅንነት ኃላፊ አዲሱን የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚደግፉ አገራት በእስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን ላይ ”ጦርነት እንዳወጁ” እንቆጥረዋለን ሲሉ ዝተዋል።
ሞህሰን ረዛኢ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ትራምፕ እርምጃ መውሰድ ከፈለጉ ተመጣጣኝ ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ ዝተዋል።
ኢራን በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ዒላማ እንደምታደርግም ዝተዋል።
ቤሰንት በፋይናንሻል ታይምስ ላይ በወጣው ጽሑፋቸው ላይ ዝርዝር እርምጃዎችን ሳይሰጡ የኢራን ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ላይ በመሳተፍ “የሚያባብሉ” ያሏቸውን “ፈሪ አገራትን” አሜሪካ ዒላማ እንደምታደርጋቸው አስታውቀዋል።
“ይህን ማስቀጠል የሚያስከትለውን ውጤት ቢያጤኑት መልካም ይሆናል” ሲሉም በፋይናንሻል ታይምስ ላይ ጽፈዋል።
ኢራን በበኩሏ ከአሜሪካ ሊሰነዘርባት ለሚችል የኢኮኖሚ ማዕቀብ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች።
የኢራን ከፍተኛ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሞህሰን ረዛኢ፣ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “የኢኮኖሚ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ በሆርሙዝም ሆነ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ውስጥ ከየትኛውም ሥፍራ አንድም የነዳጅ ጠብታ ወደ ውጭ አይላክም” ብለዋል።
“ኢራን፣ የትኛውም አገር በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው የኢኮኖሚ ጦርነት ውስጥ ቢሳተፍ ወይም ድጋፍ ቢሰጥ፣ ድርጊቱን እንደ ጦርነት ተግባር ትቆጥረዋለች” ሲሉም አክለዋል።
ቤሰንት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የነዳጅ ምርት ከኢራን የምትገዛውን ቻይና ከአሜሪካ ጋር እንድትተባበር አሳስበው ነበር።
በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እንድትከተል ጥሪ በማቅረብ "ማዕቀቦች እና ጫናዎች ችግሩን ለመፍታት አይረዱም።" ብለዋል።
