'ፎቢያ'፡ ስለአንዳንድ ነገሮች የተለየ ፍርሃት የሚፈጠርብን ለምንድን ነው? እንዴት ፍርሃታችንን ማሸነፍ እንችላለን?

የፎቶው ባለመብት, dlewis33 via Getty Images
ድንገት ቤት ውስጥ ሸረሪት ቢመለከቱ ምን ይሰማዎታል? በእርግጥ አብዛኞቹ ሸረሪቶች መርዛማ ቢሆኑም ለሰው ልጆች አደገኛ የሆኑት ግን ውስን ናቸው።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የአካባቢ ጥናት ተቋም እንደሚለው በየዓመቱ ከ10 ሰዎች ያነሱ በሸረሪት ንክሻ እንደሚሞቱ ይገመታል።
ሆኖም ግን ብዙዎች ሸረሪት ይፈራሉ። ሸረሪት ያለበት ክፍል ውስጥ መተኛትን ማሰብ አይችሉም።
ጉዳት የማያደርሱብንን ነገሮች መፍራት (ፎቢያ) የተለመደ ነው። ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ባይጎዷቸውም ይፈራሉ። ለምን ይሆን?
ፍርሃት ምንድን ነው?
በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኒው ጀርሲ የሥነ ልቦና ምሁር ቨኔሳ ሎቡ እንደምትለው ፍርሃት የተመለደ የሰው ልጆች ስሜት ዓይነት ነው።
"ፍርሃት አስፈላጊ ነው። ጎጂ ከሆኑ ነገሮች ይጠብቀናል" ትላለች።
ፍርሃት መጠኑን ሲያልፍ ኑሮን የሚያናውጥ ይሆናል። 'ፎቢያ' የሚል ስም የተሰጠው ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃት እንደሆነ በሀንጋሪ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፔክስ የዕይታ እና ስሜት ተመራማሪ አንድሬስ ዚስዶ ይናገራል።
"የተለመደ ዓይነት ፍርሃት አለ። ሁሉም ሰው የሚፈራው ነገር ይኖራል። ከዚህ ተነስቶ ስሜቱ ከፍ ይላል" ይላል።
ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃት ከሚፈራው ነገር የጉዳት መጠን ጋር የማይመጣጠን እንደሆነ ቨኔሳ ትናገራለች።
አብዛኞቹ የእባብ ዝርያዎች ጎጂ ቢሆኑም ምክንያታዊ ባልሆነ መጠን የሚፈሩ ሰዎች አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Art Images via Getty Images
ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው?
ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃት የተለመደ ቢሆንም ባለሙያዎች እንደሚሉት በተፈጥሮ የሚመጣ ስሜት አይደለም።
ቨኔሳ እንደምትናገረው ጨቅላ ሕጻናት ይሄ ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃት አይታይባቸውም።
"ፍርሃት በዚያ ዕድሜ ላይ አይስተዋልም። ፍርሃት አንድን ነገር አስቦ እና አገናዝቦ አስጊ ነው ብሎ መፈረጅ ይጠይቃል። ያንን ለማድረግ ደግሞ ዓለምን ማወቅ ያስፈልጋል።"
ሰዎች ሸረሪት ወይም እባብ በተፈጥሯቸው የማይፈሩ ከሆነ ለምን ዕድሜያቸው ሲጨምር ከልክ ያለፈ ፍርሃት ይይዛቸዋል?
በኦስትሪያ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቤና የሥነ ዕድገት ሥነ ልቦና ተመራማሪ ስቴፋኒ ሆይል በሠራችው ጥናት ጨቅላ ሕጻናት እባብ ወይም ሸረሪት ሲመለኩ የዐይን ብሌናቸው ይሰፋል። በተቃራኒው አበባ ወይም ዓሣ ሲመለከቱ ይሄ ስሜት አይነበብባቸውም።
የዐይን ብሌን መስፋት ወይም ዐይንን ማፍጠጥ አንዳች አደገኛ ነገር የመቃረቡ ምልክት ነው።
ሰውነት በፍርሃት መሸበቡን መልዕክት የሚያስተላልፈው የአንጎል ክፍል (ኖራድሪኢንሪጂክ ሲስተም) ሲነቃ የሚፈጠር ነው።
አደገኛ ነገር እንዳለ በማሰብ የልብ ምት ይጨምራል፣ የደም ግፊት ከፍ ይላል፣ አተነፋፈስም ይለወጣል። ሰውነት አደጋ ሲመጣ ሮጦ ለማምለጥ የሚያደርገው ዝግጅት ነው።
ስቴፋኒ እንደምትለው ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን በአካባቢያችን ያሉ ነገሮችን በመመልከት የተያየ ስሜት ይፈጠራል።
"አንዳንድ ነገሮችን መፍራት እንዳለብን እንማራለን" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Maskot via Getty Images
ቨኔሳ በበኩሏ እንደ እባብ እና ሸረሪት ያሉ እንሰሳት "እንግዳ ነገሮች" ስለሆኑ ከሌሎች እንሰሳት በተለየ ይፈራሉ።
"ለምሳሌ እባብን ብንወስድ የሚመስለው ሌላ እንሰሳ የለም። ልጆች እንሰሳት የሚላመዱት አራት እግር ያላቸውን የእንሰሳት ዓይነቶች በመመልከት ነው። እባብ እና ሸረሪት ከዚህ የተለዩ ስለሆኑ አንወዳቸውም።"
አንድሬስ እንደሚናገረው አንዳንድ ፍጥረታትን መፍራት ከዝግመተ ለውጥ ጋር የሚመጣ ነው።
"ቀደምት ሰዎች የተከበቡት ለመገመት በማይቻል አካባቢ ነበር። በሰው ልጆች እድገት ውስጥ ፍርሃት ወይም ከልክ ያለፈ ፍርሃት (ፎቢያ) ምክንያታዊ ነበር። ነገር ግን የሆነ ነጥብ ላይ ሲደረስ በዕለት ከዕለት ሕይወት ያለው አስፈላጊነት ጠፍቷል።"
በዝግመተ ለውጥ ምክንያት ፍርሃትን መማር (ፕሪፔርድነስ ቲዮሪ) አንደኛው ምክንያት ቢሆንም ከክል ያለፈ ፍርሃት ለማሳደር ብቸኛው መንስዔ አይደለም።
ከእንሰሳ ወይም ቁስ ጋር በተያያዘ አሉታዊ ተሞክሮ ሲኖረን ወደ ፍርሃት ያድጋል። በተለይ ደግሞ በዝግመተ ለውጥ ለፍርሃት መጋለጥ ላይ ተሞክሮው ሲጨምር ስጋትን ያባብሳል።
ቨኔሳ እንደምትለው አንድ ነገር ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ ማየት ሌላኛው የፍርሃት መንስዔ ነው።
"የተነከሰ ሰው ፍርሃት ይፈጠርበታል። ልጆች እናቶቻቸው 'ያ ነገር መጥፎ ነው' ሲሏቸውም ፍርሃትን ይማራሉ።"
በዚህ መንገድ ከልክ ያለፈ ፍርሃት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚሻገር ታስረዳለች።
ፊልም ፍርሃት ይፈጥራል?
አሉታዊ ተሞክሮ ፍርሃትን እንደሚያጭረው ሁላ በፊልም ወይም በሌላ የጥበብ ሥራ እባብ እና ሸረሪት የሚሳሉበት መንገድም ፍርሃት እንደሚያሳድር ቨኔሳ ትናገራለች።
"በፊልሞች ወይም በመጻሕፍት እባብ ወይም ሸረሪት እንደ በጎ ሲሳሉ አናይም" ትላለች።
ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ተፈጥሯዊ የሆኑ ነገሮችን መፍራት (ባዮፎቢያ) ላይ ጥናት የሠራው አንድሬስ በአንድ ሰው ተፈጥሯዊ አካባቢ እና በእንሰሳት ፍርሃት መካከል ያለውን ትስስር ይመለከታል።
ከተማ ቀመስ አካባቢዎች ውስጥ ተፈጥሯዊ የሆነን ነገር መፍራት የተለመደ መሆኑን በጥናቱ ደርሶበታል።
"ብዙ ጊዜ ከተፈጥሮ ጋር የሚያጠፉ ሰዎች እንሰሳት የመፍራት ዕድላቸው ጠባብ ነው" ይላል።
በመላው ዓለም በከተማ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ ሆኗል። እንሰሳትን መፍራት እየተለመደ ከመጣበት ምክንያት አንዱም ይህ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Flashpop via Getty Images
ከፍርሃት መውጣት ይቻላል?
ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃትን መቀልበስ ወይም ማጥፋት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
ራሳችንን ለምንፈራቸው ነገሮች በማጋለጥ ፍርሃትን ማጥፋት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
"አንድ ነገር ምቾች የሚነሳን ከመሰለን ራሳችንን ወደ እዚያ ነገር ማጋፈጥ ጥሩ መንገድ ነው" ስትል ስቴፋኒ ታብራራለች።
ቨኔሳ በበኩሏ የምንፈራውን ነገር ምሥል ከማየት መጀመር እንደምንችል ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Justin Paget via Getty Images
ስለምንፈራው እንሰሳ አወንታዊ የሆኑ ነገሮችን በመማር ቀስ በቀስ ራሳችንን ማለማመድ እንደምንችል ትገልጻለች።
አንድሬስ የሠራው ጥናት እንደሚያሳየውም ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃትን ማጥፋት ይቻላል።
"ፍርሃት የምናዳብረው ከግል ተሞክሯችን ተነስተን ነው። አወንታዊ ተሞክሮ ሲኖረን ወይም በልጅነታችን ስንማለው ፍርሃት አናዳብርም" ይላል።
ፍርሃት የሰው ልጆችን የሚጠብቅ አወንታዊ ስሜት እንደሆነ ቨኔሳ ትናገራለች። ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃትን መቆጣጠር እንደሚቻልም ታክላለች።
"አንድን ነገር በመፍራት መቀጠል የለብንም። ፍርሃትን ማቆም ከፈለግን አማራጭ መንገዶች አሉን" ትላለች።















