ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዴት ለተከፈተባት ጦርነት የአጸፋ መሣሪያ አድርጋ ተጠቀመችበት?

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በኢራን፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በእስራኤል መካከል ለ40 ቀናት የዘለቀ ጦርነት አስገራሚ ጉዳይ ይዞ ብቅ ብሏል። እጅግ ውጤታማው እና አደገኛው የኢራን መሣሪያ የኒውክሌር አቅሟ ሳይሆን የሆርሙዝ ወሽመጥ መሆኑን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።

ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን ውስጥ ከባድ የቦምብ ጥቃት በመፈጸም የአገዛዝ ለውጥ እንዲመጣ የማድረግ ሙከራ እንደነበር ይታሰባል።

ኢራን በአሜሪካ የባሕረ ሰላጤ አገራት አጋሮች ላይ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን በማስወንጨፍ ምላሽ ሰጥታለች።

ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሄድ ግን ትኩረቷን በጠባቡ የውሃ መስመር በኩል በማድረግ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የሚያገናኘውን ወሽመጥ ወደ ማስተጓጎል አዙራለች።

እርምጃው በፍጥነት ነበር በዩናይትድ ስቴትስ እና በባሕረ ሰላጤው በኩል የነዳጅ እና የጋዝ ግብይት በሚፈጽሙት አጋሮቿ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረው።

በእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (አይአርጂሲ) ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ይህንን የመርከብ መስመር መቆጣጠር ከተቻለ ከወታደራዊ ግብግብ የበለጠ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል ተገንዝበዋል።

ኢራን ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦቶችን በማስተጓጎል ዋሽንግተን አቅጣጫዋን እንደገና እንድታጤን አስገድዳታለች። በመጨረሻም መስመሩን እንደገና ለመክፈት እና የተኩስ ማቆም ድርድር ቅድመ ሁኔታ አድርጋ አስቀምጣዋለች።

ኢራን ጥቃት ከደረሰባት ወሽመጡን እንደምትዘጋ በተደጋጋሚ ብትዝትም ከዚህ በፊት በዚህ መልኩ ሙሉ በሙሉ ተዘግታው አታውቅም።

የነዳጅ ጫኝ ላይ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው በነበሩበት በአውሮፓውያኑ ከ1980 አስከ 1988 በተካሄደው የኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት እንኳን ወሽመጡን አልዘጋችውም።

አንዳንድ የኢራን አዛዦች እና ባለሥልጣናት አገሪቱ ወሽመጡ ላይ ስላላት ቁጥጥር ሲወያዩ ሰንብተዋል። የኢራን ፓርላማ፤ በተለይም የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚሽኑ በወሽመጡ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ቀረጥ ለመጣል ሃሳብ አቅርቧል።

አንድ የፓርላማ አባል ኢራን በወሽመጡ ለሚያልፈው ለእያንዳንዱ ሦስት በርሜል ነዳጅ አንድ ዶላር ማስከፈል እንዳለባት ጠቁመዋል።

የድል ምሥል

የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ የድል ምሥል አሰራጭተዋል።

"የአላህ ድል ሲመጣ እና ድል ሲደረግ" የሚል ርዕስ ያለው እና የኢራንን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ የሚያሳይ ቪዲዮ በኩዌት በሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ተለጥፏል።

ይህ ቪዲዮ አገሪቱ የውጭ ጫናን በተሳካ ሁኔታ ተቋቁማለች የሚለውን እና በኢራን በስፋት የሚሠራጨውን ​​አስተሳሰብ ያንፀባርቃል።

ከአብዮታዊው ዘብ ጋር ቁርኝት ያለው የፋርስ ዜና ወኪል "የኢራን የተኩስ አቁም ዕቅድ ማዕቀቦችን ማንሳት፣ የጦርነት ካሣ፣ የአሜሪካ ወታደሮችን ከቀጣናው ማስወጣትን ያካትታል" በማለት ዘግቧል።

የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ይህንኑ ስሜት አስተጋብተዋል። የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው የተኩስ አቁሙን በጦርነቱ መጀመሪያ ቀናት የተገደሉትን የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒንን በመጥቀስ "የኻሜኒ ዶክትሪን ድል" አድርገው አስቀምጠውታል።

የቀድሞው የአብዮታዊው ዘብ ኃላፊ እና የአዲሱ የኢራን መሪ አማካሪ የነበሩት ሞህሰን ሬዛይ በበኩላቸው የኢራን ኃይሎች "ጣቶቻቸው በቃታ ላይ ሆነው" በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።

ከድል መግለጫዎቹ ጀርባ ግን ደካማ እውነታ አለ።

የኢራን ጦር ኃይል ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል፤ በአሜሪካ የሚመራው እና ለዓመታት በዘለቀው ማዕቀብ ጫና ውስጥ ያለው ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ተሸመድምዷል።

በግጭቱ ወቅት ቢያንስ 13 ግለሰቦች በኢራን መንግሥት ተገድለዋል። ብዙዎቹ በስለላ የተወነጀሉ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጥር ወር በተካሄደው አገር አቀፍ ተቃውሞ ምክንያት የታሰሩ ናቸው።

ባለሥልጣናት ቁጥጥራቸውን እንደገና ለማስቀጠል በሚንቀሳቀሱበት በዚህ ወቅት እርምጃዎቹ በአገዛዙ ውስጥ ስላለው አለመረጋጋት ማሳያ ነው።

የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ እንደገና ማስከፈት ከሰላም ድርድር በፊት የቀረበ የአሜሪካ ቁልፍ ጥያቄ ነበር። ይህንን ማሳካት ግን ቀላል የሆነ አይመስልም።

ከአብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ፈቃድ ውጭ የሚያልፉ መርከቦች "ዒላማ እንደሚደረጉ እና እንደሚወድሙ" ኢራን ረቡዕ ዕለት አስጠንቅቃለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ተቀባይነት የሌላቸውን" ሪፖርቶች እንደሚያውቁ በመግለጽ ይህ ግን በግል ከሚነገረው የተለየ መሆኑን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሊቬት ተናግረዋል።

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰኢድ ካቲብዛዴህ ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢራን "አስተማማኝ የሆነ የመተላለፊያውን ደኅንነት ትሰጣለች"፤ ይህም ከኢራን ጋር ጦርነት እስኪጀምር ድረስ "ለሺህ ዓመታት ክፍት" እንደሆነው ዓይነት መሆኑን ተናግረዋል።

እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት በመጥቀስ ሆርሙዝ እንደገና የሚከፈተው ግን "ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን ጥቃት ካቆመች በኋላ" ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ካቲብዛዴህ አክለውም ኢራን "ዓለም አቀፍ ደንቦችን እና ሕጎችን" እንደምታከብር ገልጸዋል። የባሕር ወሽመጡ የዓለም አቀፍ የውሃ አካል እንዳልሆነ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ የሚሆነው "በኢራን እና በኦማን በጎ ፈቃድ" ላይ ተመሥርቶ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕር ወሽመጥ የሚተዳደረው በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነትሲሆን፣ ይህም ለሲቪል አገልግሎት ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ እንዲሆን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው።

አደገኛ ቅድመ ሁኔታ

ኢራን ቀጥሎ ምን ልታደርግ ትችላለች? የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን ለመቆጣጠር በኢራን ፓርላማ ፊት የቀረበው ሃሳብ ዘጠኝ ነጥቦችን ያካተተ ነው።

ከዋና ዋናዎቹ ሃሳቦች አንዱ "የጠላት መርከቦች እንዲያልፉ አይፈቀድላቸውም" ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢራን የመተላለፊያ አገልግሎቶችን ታቀርባለች።

ለዚህም ኩባንያዎች በኢራን ገንዘብ እንዲከፍሉ እና የኢራን የባንክ ሂሳብ እንዲኖራቸው ያስገድዳል። መርከቦችም ጭነታቸውን ማሳውቅም ይጠበቅባቸዋል።

ይህ በጣም ውስብስብ የሆኑ ሃሳቦች እና ነጥቦችን ያያዘው ኢራን ሆርሙዝ ላይ ተግባራዊ ልታደርገው ያዘጋጀችው አዲሱ ዕቅድ ብ እስካሁን ድምጽ አልተሰጠበትም።

ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ክፍያ ከጣለች ዩናይትድ ስቴትስ እና የአካባቢው አጋሮቿ እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ይቀበሉታል ወይ? የሚለው ጥያቄ ይነሳል።

በቅርቡ በተሰጡ ምላሾች መሠረት ሃሳቡ ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠመው ያሳያሉ። የመርከብ እንቅስቃሴ ነፃነት ለአሜሪካ እና ለአጋሮቿ ዋና መርኅ ሲሆን፣ ማንኛውም የክፍያ ሥርዓት አደገኛ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።

ኢራን ስኬታማ ከሆነች በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ወሳኝ የባሕር መስመሮች መካከል አንዱን የመቆጣጠር አቅሟን በማሳየት ጉልህ የሆነ ስትራቴጂካዊ እና ተምሳሌታዊ ድልን ትቀዳጃለች።

እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ የአሜሪካ አጋሮችን፣ የኔቶ አባላትን እና የጣናውን ኃይሎች በጋራ በኢራን ላይ እንዲነሱ ሊያደርጋቸው የሚችልብት አደጋ አለው።

ይህም ወደ የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ወታደራዊ አማራጮች ሊወስዳቸውም ይችላል የሚለው ስጋት ፈጥሯል።