የአሜሪካ እና ኢራን ንግግርን አስቸጋሪ የሚያደርጉት አምስት ጉዳዮች

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አዳራሹ ተዘጋጅቷል፣ ጠባቂዎች በቦታው ተሰይመዋል፣ ወደ ድርድሩ አዳራሽ የሚያመራው መንገድም እንደ አዲስ ቢጫ እና ጥቁር ቀለም ተቀብቷል።

የፓኪስታኗ ዋና ከተማ ኢስላማባድ ታሪካዊውን ድርድር ልታስተናግድ እየጠበቀች ነው። ልዑኮቻቸውን አስከትለው ኢስላማባድ የደረሱት የኢራን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከሰዓታት በኋላ ንግግር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

ወሳኙን የኢራን እና አሜሪካ ንግግር የሚያስተናግዱት የፓኪስታን መንግሥት ባለሥልጣናት ጥሩ ውጤት ይገኛል የሚል ተስፈኛ ንግግራቸውን እያሰሙ ነው። ከብዙ አገራት በተለየ መልኩ ፓኪስታን በሁለቱም ወገኖች እምነት የሚጣልባት ሆናለች።

የአሜሪካውን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስም ተስፈኛ ይመስላሉ። "ኢራናውያን በቀና ልቦና ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆኑ፤ ያለ ጥርጥር ክፍት እጃችንን ለመዘርጋት ፈቃደኛ ነን" ሲሉ የፓኪስታን ጉዟቸውን ከመጀመራቸው በፊት ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያም ሳይሰጡ ግን አላለፉም። "ሊጫወቱብን የሚሞክሩ ከሆነ ግን ተደራደሪ ቡድኑ ምላሽ የማይሰጥ ሆኖ ያገኙታል" ሲሉ አሳስበዋል።

ለ40 ቀናት የተዋጉት አሜሪካ እና ኢራን ከፊታቸው የሚጠብቃቸው መንገድ በእንቅፋት የተሞላ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።

ሊባኖስ

እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በሚገኘው የኢራን አጋር ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ላይ የከፈተችው ዘመቻ የሰላም ንግግሩ ላይ ደመናውን ያጠላው ገና ድርድሩ ሳይጀመር ነው።

የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ "የእነዚህ ድርጊቶች መቀጠል ድርድሩን ወደ ትርጉም የለሽነት ያወርደዋል" ብለዋል።

"ጣቶቻችን ቃታው ላይ መሆናቸውን ይቀጥላሉ። ኢራን የሊባኖስ እህት እና ወንድሞቿን መቼም አትተውም" ሲሉም ጠንካራ አቋማቸውን አስታውቀዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ከሄዝቦላህ ጋር በተያያዘ የሚተገበር "ተኩስ አቁም የለም" ሲሉ ተደምጠዋል። እስራኤል በደቡባዊ ቤይሩት መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች፤ እስካሁን ግን ተጨማሪ እርምጃ አልወሰደችም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ የምትወስደው እርምጃ "በመጠኑ እንደሚቀንስ" ገልጸዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የሚደረገው ቀጥተኛ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ትራምፕ እንደተናገሩት የእስራኤል እርምጃ በአነስተኛ መጠን መቀነሱ ብቻ ኢራንን የሚያረካ ይሆን እንደሆን ይታያል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ

ድርድሩን ከጅምሩ የማደናቀፍ ዕድል ያለው ሌላኛው ጉዳይ ወሳኝ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች መተላለፊ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ነው።

ትራምፕ ኢራን በወሽመጡ በኩል መርከቦችን እንደምታሳልፍ ሲናገሩ ቢቆዩም ኋላ ላይ ሆርሙዝን በመለከተ እያከናወነች ያለችው "እጅግ ደካማ ሥራ ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

"የደስንበት ስምምነት ይሄ አይደለም" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው የጻፉት ትራምፕ፤ ኢራን "ክብረ ቢስ" ሆናለች ሲሉም ከስሰዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እና 20 ሺህ እንደሆኑ የሚገመቱ ባሕርተኞች አሁንም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ መንቀሳቀስ ተቸግረው ቆመዋል። እስካሁን በወሽመጡ በኩል ያለፉት ጥቂት መርከቦች ናቸው።

ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ መስመር በተሳካ ሁኔታ መዝጋት የቻለችው ኢራን፤ ይህንን እርምጃዋን በሕግ ልትደግፈው የቆረጠች ትመስላለች። ሆርሙዝን የኢራን ሉዓላዊ ውሃ በማለት እየጠራችው ሲሆን በሆርሙዝ በኩል ምን ማለፍ እንደሚችል እና እንደማይችል ሕጎችን እንደምታወጣ እየገለጸች ነው።

ሐሙስ ዕለት ከዚህ ቀደም መርከቦች ሲጓዙ ከነበሩባቸው ሁለት መስመሮች በስተሰሜን አዲስ የጉዞ መስመር መፍጠሯን ይፋ አድርጋለች። በመርከቦች ላይ የተፈጠረውን ስጋት ከግምት ውስጥ አስገብቶ በወጣው በዚህ መግለጫዋም፤ አዲሱ መስመር የተዘጋው "በዋናው የትራፊክ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ጸረ መርከብ ፈንጂዎችን ለማስቀረት" እንደሆነ አስታውቃለች።

ባለፉት ሳምንታት ያለፉ መርከቦች ሁለት ሚሊዮን ዶላር መክፈላቸውን የሚገልፁ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ትራምፕ፤ ኢራን "ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን እያስከፈለች ባይሆን ይሻላታል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ኒውክሌር

ለድርድር እንቅፋት ከሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ምናልባትም ትልቁ እና ለረጅም ጊዜ የቅራኔ አጀንዳ ሆኖ የከረመው የኒውክሌር ነገር ነው።

ትራምፕ ኦፕሬሽን 'ኤፒክ ፊውሪ' ተብሎ የተሰየመውን ወታደራዊ ዘመቻቸውን በከፈቱበት ወቅት ኢራን "መቼም የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራት እንደማይችል" እንደሚያረጋግጡ ሲናገሩ ነበር።

ኢራን የኒውክሌር ቦንብ መገንባት ፍላጎት እንደሌላለት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ብትቆይትም አብዛኛዎቹ የምዕራባውያን መንግሥታት ቃሏን አምነው ሊቀበሉት አልቻሉም። የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ላለማስፋፋት የተደረሰው ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ የሆነችው ኢራን፤ ለሲቪል ዓላማ የሚውል ዩራኒየም የማበልጸግ መብት እንዳላት አጥብቃ ትከራከራለች።

ኢራን ለድርድር ባቀረበችው እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ለድርድር መነሻነት ሊያገለግል ይችላል" ሲሉ በገለጹት ባለ 10 ነጥብ እቅዷ ላይ ካካተተቻቸው ጉዳዮች አንዱ ዩራኒየም የማበልጸግ መብቷ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ የሚጠይቅ ነው።

ትራምፕ አቅርበውታል የተባለው ባለ 15 ነጥብ የስምምነት እቅድ ደግሞ "በኢራን መሬት የሚደረግ ዩራኒየም የማበልጸግ ተግባር በሙሉ እንዲቆም" ይጠይቃል። በዚህ ሳምንት ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት፤ ኢራን "የኒውክሌር መሣሪያ ወይም ወደዚያ ሊያደርስ የሚችል አቅም ፈጽሞ አይኖራትም" ሲሉ ያለተጨማሪ ማብራሪያ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተደራዳሪዎች በአውሮፓውያኑ 2015 ከኢራን ኒውክሌር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በዝርዝር የያዘው የጋራ አጠቃላይ የድርጊት መርሃ ግብር ላይ ለመድረስ ዓመታት ፈጅቶባቸው ነበር።

አሁንስ ሁለቱ ወገኖች ስለ አዲስ የኒውክሌር ስምምነት ለመወያየት ዝግጁ ናቸው? የሚለው የዛሬው ድርድር አንዱ ጥያቄ ነው።

የኢራን ቀጣናዊ አጋሮች

ኢራን በቀጣናው የአጋሮች እና የተጣማጆች መረብ ዘርግታለች። ሊባኖስ ውስጥ ሄዝቦላህ፣ የመን ውስጥ ሁቲ፣ ጋዛ ውስጥ ሀማስ እንዲሁም ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች አጋሮቿ ናቸው።

እነዚህ ኃይሎች፤ ኢራን ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር ባላት ቁርሾ የተነሳ የምትከተለውን "ቅድመ መከላከል" እንድትተገብር እና በቀጣናው የጎላ ድምጽ እንዲኖራት አስችለዋል።

በመስከረም 2025 የጋዛ ጦርነት ከተነሳ በኋላ ኢራን 'አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ' ብላ የምትጠራው ይህ የአማጺያን መረብ ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙበት ነው። የቀድሞው የሶሪያ አምባገነነ ባሽር አል አሳድ አገዛዝም ወድቋል።

እስራኤል በበኩሏ 'አክሲስ ኦፍ ኢቭል' ብላ የምትጠራውን ይህንን ጥምረት የምትመለከተው ሙሉ በሙሉ መወገድ እንዳለበት የህልውና ስጋት ነው።

የኢራን ኢኮኖሚ እየተዳከመ ባለበት በዚህ ወቅት፤ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች መንግሥታቸው ከአገር ውጭ በሚገኘው የጥምረት መረቡ ላይ የሚያወጣውን ወጪ ቀንሶ ሕይወታቸውን ማቅለል ላይ ትኩረት ቢያደርግ ይመርጣሉ።

ነገር ግን ኢራን አጋሮቿ ላይ ፊቷን እንደምታዞር የሚጠቁም ምልክት እስካሁን አልታየም።

የማዕቀብ እፎይታ

የኢራን እስላማዊ አገዛዝ ኢኮኖሚውን ሽባ ባደረጉ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ለአስርት ዓመታት ሲሰቃይ ቆይቷል። አሁን በሚደረገው ድርድር ሁሉም የአሜሪካ እና ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሱለት እየጠየቀ ነው።

የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ፤ 120 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የሚገመተው እንዳይንቀሳቀስ የታገደ የኢራን ሀብት ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት መለቀቅ እንዳለበት አርብ ዕለት ተናግረዋል።

ይህ ጉዳይ እና የሊባኖስ የተኩስ አቁም ከዚህ በፊት ስምምነት የተደረሰባቸው እርምጃዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ላይ መደረሱን ይፋ ባደረጉበት የማክሰኞ ዕለቱ መግለጫ ላይ ግን የተያዙ ሀብቶችን ስለመልቀቅ የተጠቀሰ ነገር የለም። የኢራኑ አፈ ጉባኤ ያጣቀሱት ስምምነት የትኛው እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ባለፉት ቀናት የተስተዋሉት ሁኔታዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ንግግር እንዲጀመር ለማድረግ ሲል በዚህ ደረጃ መደራደሪያ ነጥቡን ዝቅ አድርጎ ይስማማል የሚለው ሀሳብ የማይዋጥ ነው።

በኢራን ላይ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች የመነሳታቸው እና በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብቷ የመለቀቁ ነገር የሁለቱ አገራት ልዑካን ዛሬ በሚጀምሩት ድርድር የሚታይ ሌላኛው አጣብቂኝ ጉዳይ ነው።