የጋዛ ሰላም ቦርድ ልዩ ልዑክ የእስራኤልን ጥቃቶች እና የሐማስን ድርጊቶችን ተቸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያቋቋሙት የሰላም ቦርድ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ እስራኤል በጋዛ የምትፈፀመውን የአየር ጥቃት እንዲሁም የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ የሚወስደውን እርምጃ ተቹ።

በቦርዱ የጋዛ ልዩ ልዑክ የሆኑት ኒኮላይ ምላዴኖቭ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መፍረስ ለቀጣናው "የማይመለስ ነጥብ" እሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሐማስ ትጥቅ ስለሚፈታበት ሁኔታ በሰላም ቦርዱ የቀረበውን ባለ15 ነጥብ ፍኖተ ካርታ እስራኤል እንደማትቀበል ከገለፀች በኋላ ልዑኩ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ንግግር አድርገዋል።

የእስራኤል ወታደሮች በምዕራፍ በተከፋፈለ አካሔድ ከጋዛ የሚወጡ ከሆነ ሐማስ ትጥቁን ለማስረከብ ቃል ገብቷል። እስራኤል በበኩሏ፣ ጦሯ ከመውጣቱ በፊት ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል አቋም ይዛለች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀባይነት ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሜሪካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ እስራኤል በጋዛ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች 300 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 1,303 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ አራት የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጤማውያን ጥቃት መገደላቸውን የአገሪቱ ጦር ገልጿል።

የሰላም ቦርዱ የጋዛ ከፍተኛ ልዑክ፣ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ስብሰባቸው ላይ ቀሪ የኔታኒያሁ መንግሥት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት በሚችሉበት አካሔድ ላይ ተስማምተው እንደነበር እና ለዚህም ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ረቡዕ ዕለት ለፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።

ይህ ሂደት እንዳልቆመ የተናገሩት ምላዴኖቭ፣ ነገር ግን በእስራኤል ጥቃቶች ፍልስጤማውያን ሲቪሎች መገደላቸው በመቀጠሉ ስጋት መኖሩን አስረድተዋል።

"ሲቪሎች አሁንም የሚቀበሩበት የተኩስ አቁም ስምምነት የጋዛ ሕዝብ ሊቀበለው የሚችለው ነገር አይደለም። አፋጣኝ የሆነ የደኅንነት ስጋትን ያላማከለ እያንዳንዱ የኃይል እርምጃ የግጭት አፈታት ሂደቱን ለመመለስ የማያስችል ከባድ ዋጋ ያስከፍላል" ሲሉ አክለዋል።

ሐማስም እንዲሁ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹን ሙሉ በሙሉ የማቆም ግዴታውን ገና እንዳልተወጣ ምላዴኖቭ ተናግረዋል።

"[ሐማስ]የተሸከመው እያንዳንዱ መሣሪያ፣ አሁንም በሥራ ላይ ያለ እያንዳንዱ ምሽግ...ሂደቱን ወደኋላ ይመልሳል፤ ጦርነቱን እንደገና ለመጀመር ለሚፈልጉ ሰዎችም ምክንያት ይሆናል" ብለዋል።

በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ መሠረት የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ መውጣት "የሐማስ የጦር መሳሪያዎች በሰላም ቦርድ ቁጥጥር ስር ጋዛን ለሚያስተዳድረው የፍልስጤም ቴክኖክራቲክ ኮሚቴ ተላልፎ ከመሰጠቱ" ጋር እንደሚያያዝ ደግመው ተናግረዋል።

ይህ ሂደት "ቅደም ተከተላዊ እና እርስ በርስ የሚመጋገብ ነው" ብለዋል።

ልዑኩ ለፀጥታው ምክር ቤት ስለሂደቱ ያብራሩት፥ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ ልዑክ ጃሬድ ኩሽነር ከሁለት ሳምንታት በፊት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ከተገናኙ በኋላ ከሰጡት አስተያየት የተለየ ነው።

የእስራኤልን ጦር ከጋዛ የሚወጣው፣ ጋዛን ከወታደራዊ ኃይል እንቅስቃሴ ነጻ የማድረግ ሥራ "ከተጠናቀቀ" በኋላ ብቻ ነው ሲሉ ኩሽነር ተናግረዋል። ይህም የሰላም ቦርዱን ዕቅድ ከእስራኤል ፍላጎት ጋር በሚስማማ መልኩ የሚቀይር ይመስላል።

በፀጥታው ምክር ቤት የእስራኤል ተወካይ ባደረጉት ንግግር፣ የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ባለፈው ጥቅምት ወር በአሜሪካ አደራዳሪነት የቀረበውን ዕቅድ ለመተግበር አገራቸው ፈቃደኛ መሆኗን ገልፀዋል። ነገር ግን አሁንም ሐማስ የጦር መሳሪያዎች፣ ምሽጎች እና ሌሎች ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች እያሉት ሊሳካ እንደማይችል አጥብቀው ተናግረዋል።

"ትጥቅ ማስፈታት መቅደም አለበት" ብለዋል።

የፍልስጤም ተወካይ በበኩላቸው እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ሲቪሎችን ያለተጠያቂነት እየገደለች መሆኗን ገልፀው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለምንም መዘግየት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል ሐማስ በፈፀመው ጥቃት 1,200 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ ተከትሎ ነበር ጦርነቱ ተቀሰቀሰው።

እስራኤል በጋዛ በወሰደችው ከባድ አፀፋዊ እርምጃ ከ73,430 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።