የኡጋንዳ ዳኞች በቅኝ ግዛት ስያሜ አይጠሩ መባሉን ተቃወሙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኡጋንዳ ጠበቆች ማኅበር ዳኞችን ከቅኝ ግዛት በተወረሰ ስያሜ እንዳይጠሩ ለጠበቆች ያስተላለፈውን ትዕዛዝ የአገሪቱ ዳኞች ተቃወሙ።

የቅኝ ግዛት አጠራር የሆኑትን 'ጌታዬ' ወይም 'My Lord' እና 'እመቤቴ' ወይም 'My Lady' ጠበቆች እንዳይጠቀሙ ማኅበሩ ቢያሳስብም ዳኞች ግን በውሳኔው ደስተኛ አልሆኑም።

የጠበቆች ማኅበር እንዳለው እነዚህ አጠራሮች "የፊውዳል እና የቅኝ ግዛት ቃል አክብሮት" ሲሆኑ ዳኞችን "ከዜጎች በላይ" የሚያደርጉም ናቸው።

ማኅበሩ "እውነታው ዳኞች የዜጎች አገልጋይ መሆናቸው ነው" ብሏል።

የዳኞች ቃል አቀባይ ጄምስ ኤርማይ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የጠበቆች ማኅበር ዳኞች "ምን ማድረግ እና መናገር እንዳለባቸው" ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን የለውም።

"ጠበቆች በሚታወቀው ስያሜ እንዲጠሩን እንፈልጋለን" ብለዋል።

እንደ ሌሎች በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር እንደነበሩ አገራት ሁሉ የኡጋንዳ ፍርድ ቤቶች የሕግ ሥርዓት ከእንግሊዝ የተወረሰ ነው።

የኡጋንዳ ጠበቆች ማኅበር "ያረጀ ያፈጀ" የቅኝ ግዛት ሥርዓት ለአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት "ውድቀት" ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።

ማኅበሩ እንደሚለው ከቅኝ ግዛት የተወረሱ የፍርድ ቤት ሥርዓቶች "ኡጋንዳውያን ራሳቸውን እንዲያዋርዱ የሚያስገድዱ እና ኃያላን ሥልጣናቸውን እንዲያጣጥሙ የሚያመቻቹ" ናቸው።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሴሜካዴዴ ፈርመውበት የወጣው መግለጫ "የማኅበሩ አባላት ማጎንበስ እና ሌሎችም ተዋረድን የሚያሳዩ ክንውኖችን እንዳይፈጽሙ ተከልክለዋል" ይላል።

የፍትሕ ሥርዓቱን "ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለማላቀቅ" የሚወሰዱ እርምጃዎች "የሕዝቡን ክብር እንደሚመልሱ" ገልጿል።

ዳኞችን 'ጌታዬ' እና 'እመቤቴ' ማለትን ማገድም የዚህ ለውጥ አካል ነው ብሏል።

ጠበቆች ዳኞችን 'ክቡር ዳኛ' ወይም 'ክብርት ዳኛ' በማለት ወይም በስማቸው መጥራት እንዳለባቸው ማኅበሩ አሳስቧል።

"ፍርድ ቤት የሚቀርቡ የሕግ ባለሙያዎች እንደ ነጻ ዜጋ መናገር አለባቸው" ሲልም ማኅበሩ አቋሙን ገልጿል።

የዳኞች ቃል አቀባይ በበኩላቸው ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ እንደመሆናቸው ከውጭ አካል ትዕዛዝ ሊሰጣቸው እንደማይችል ተናግረዋል።

"በአስተዳደር ውስጥ አጀንዳ መቅረጽ ያቃታቸው ወጣቶች ናቸው" ሲሉም ማኅበሩን አጣጥለዋል።

"ጠንካራ ነጥብ ካላቸው በተገቢው መድረክ ማቅረብ ይችላሉ፤ ከዚያም የፖሊሲ አካል ይሆናል" በማለትም አክለዋል።

በሌሎችም የአፍሪካ አገራት የቅኝ ግዛት አጠራርን መጠቀም አወዛጋቢ ነው።

በፍርድ ቤት ሰው ሠራሽ ፀጉር ማድረግ እና ካባ መልበስ እንዲቀር ሲጠየቅም ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2011 ኬንያዊው ዳኛ ዊሊ ሙቱንጋ የዳኞችን አለባበስ በመተቸት ቃለ መሐላ ሲገቡ ሱፍ ለብሰው ተገኝተዋል።

በዚምባብዌ፣ ማላዊ እና ጋናም የቅኝ ግዛት አለባበሶች በዘመናዊት አፍሪካ ቦታ የላቸውም የሚሉ ትችቶች ቀርበዋል።