ጋናዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስምንት ሚሊዮን ዶላር በማጭበርበር ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አቡ ትሪካ በሚል ስም የሚታወቀው ጋናዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፍሬድሪክ ኩሚ በፍቅር ማታለል ከአረጋዊ አሜሪካዊያን ስምንት ሚሊዮን ዶላር በማጭበርበር ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ።

ተጠርጣሪው የቀረቡበትን ክሶች አስተባብሏል።

ዓቃቢያነ ሕግ ተጠርጣሪው ሐሰተኛ የበይነ መረብ ማንነቶችን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ተጠቅሞ በመክፈት ተጎጂዎችን በማኅበራዊ የትስስር ገፆች እና የፍቅር አገኛኝ መድረኮች በማጥመድ አመኔታቸውን ካገኘ በኋላ ገንዘባቸውን ወስዷል ብለዋል።

ኩሚ ሐሙስ ዕለት ወደ አሜሪካ የበረረ ሲሆን የገንዘብ በማጭበርበር ሴራ እና ገንዘብ በማጠብ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 20 ዓመት እስር ሊጠብቀው ይችላል።

የኩሚ ጠበቃ ኦሊቨር ባርከር-ቮርማወር የደንበኛቸውን ተላልፎ መሰጠት ለማስቆም ሐሙስ ዕለት ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ወዲያው ጉዞ ላይ መሆኑን እንዳወቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃው የጋና መንግሥት የሕግ ክፍተት በመፈፀም ዜጋውን ያለ ፍርድ ቤት ብይን አሳልፎ ሰጥቷል ሲሉ ወቅሰዋል። ደንበኛቸውን አሳልፎ ለመስጠት የተደረሰው ውሳኔ "ትልቅ የሕገ መንግሥት ጥያቄ ያስነሳል" ብለዋል።

የጋና መንግሥት እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

ፍሬድሪክ ኩሚ ከ100 ሺህ በላይ ለሆኑት የኢንስታግራም ተከታዮቹ ቅንጡ ዕቃዎቹን በማሳየት ለረዥም ጊዜ ይታወቃል።

ይህም የገቢ ምንጩን በሚመለከት ጥርጣሬ ያሳደረ ነው።

የአሜሪካ አቃቢያነ ሕግ ተጎጂዎች በማኅበራዊ የትስስር ገፆች እና የፍቅር አገናኝ መድረኮች ዒላማ እንደተደረጉ እና በተደጋጋሚ እና በቅርብ ግንኙነት እንደተማረኩ ገልፀዋል።

ግንኙነቱ "አስቸኳይ ሕክምና፣ የጉዞ ወጪ ወይም የኢንቨስትመንት እድል በመሰሉ ሐሰተኛ ጥያቄዎች ገንዘብ ወይንም ዋጋ ያላቸው ቁሶችን ወደ መጠየቅ ያመራል።"

ከዚያም ገንዘቡ ወይንም ዋጋ ያላቸው እቃዎች ግብረ አበር ወደሆኑ ሦስተኛ ሰዎች ይተላለፋሉ። ተጠርጣሪው ገንዘቡን አሜሪካ እና ጋና ለሚገኙ ግብረ አበሮቹ ያከፋፍላል ተብሏል።

በደቡባዊ ጋና ስወድሩ የሚኖረው ኩሚ ባለፈው ዓመት በጋና እና አሜሪካ ሕግ አስከባሪዎች የጋራ ተልዕኮ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በኩሚ እውነተኛ እድሜ ላይ ግርታ ያለ ሲሆን ጠበቃው 28 ዓመቱ ነው ሲሉ፤ የአሜሪካ አቃቢ ሕግ ደግሞ 31 ዓመቱ እንደሆነ ይገልፃል።

መዝገቡ በአሜሪካ የአረጋዊያን በደል መከላከል እና ሕግ እየታየ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በቅርብ ወራት አረጋዊያንን በሚያጭበረብሩ በአገሪቱ እና በምዕራብ አፍሪካ የወንጀል መረቦች ላይ እርምጃቸውን አጠናክረዋል።

ባለፈው ሳምንት ጋናዊውን አጭበርባሪ ጆሴፍ ክዋዶው ባዱ ቦሬንግ ተላልፎ የተወሰደ ሲሆን በፍቅር ማጥመድ እና በውርስ ማታለል አሜሪካዊያንን ማጭበርበሩን አምኗል።

ባለፈው ታኅሳስ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ናይጄሪያዊውን አጭበርባሪ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በማጭበርበር በ20 ዓመት እስር ፈርዶበታል።