በሰሜን አየርላንድ ሱዳናዊው ስደተኛ የፈጸመውን የስለት ጥቃት ተከትሎ ከባድ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

በላንድሪክ ጎዳና የቆሻሻ ገንዳዎች፣ መኪናዎች እና ቤቶች በእሳት ተያይዘዋል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜን አየርላንድ ቤልፋስት ከተማ በስለት የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣት መገደዳቸው ተገለጸ።

ቤቶች እና መኪኞች ሲቃጠሉ የሕዝብ ትራንስፖርት በከተማዋ ተቋርጧል።

ሰኞ ምሽት በስለት ጥቃት በመፈጸም የመግደል ሙከራ አድርጓል በሚል የተጠረጠረው የ30 ዓመቱ ሱዳናዊ ረቡዕ በሰሜን ቤልፋስት ፍርድ ቤት ይቀርባል።

ግለሰቡ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ስለት ይዞ በመገኘት እና ለመግደል በማስፈራራት ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶበታል።

ጥቃት ደረሰበት የ40 ዓመት ሰው በዓይኑ እና አንገቱ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት እና በሆስፒታል ሕክምና እየተከታተለ መሆኑ ተገልጿል።

በስፋት በበይነ መረብ የተሠራጨ የጥቃቱ ቪዲዮ እንደሚያሳየው ፖሊስ ወንጀሉ ወደ ተፈጸመበት አካባቢ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ሰዎች ተሰብሰብበው አጥቂውን ባገኙት ነገር ሁሉ ለመከላከል ሞክረዋል።

የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ ጥቃቱን ተከትሎ "በውስን አካባቢዎች በተፈጠረው ነውጥ" መረጋጋት እንዲሰፍን ጠይቋል።

ጥቃቱን የተቃወሙ በለንደንዴሪ፣ አንትሪም፣ ኒውታውንአቤይ፣ ባሌሜና፣ ባንጎር እና ቤልፋስት የሚገኙ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተወሰኑ ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ቢያሰሙም አንዳንድ ቦታዎች ግን ወደ አመጽ ተቀይሯል።

በምሥራቅ ቤልፋስት ሌንድሪክ ጎዳና ላይ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ "በመንገድ ላይ የነበሩ መኪናዎች ተቃጥለዋል። ቤቴም ተቃጥሏል፤ ጭምብል የለበሱ ሰዎች በሮችን ሲገነጥሉ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የፊት ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች በኒውታወንራድስ መንገድ በሮችን እና መስኮቶችን ሲሰባብሩ ታይተዋል።

በርካቶቹ ታዳጊዎች መሆናቸውን የአልስተር ዩኒየኒስት ፓርቲ መሪ ጆን በሮውስ ተናግረዋል።

ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ የቆሻሻ ገንዳዎች እንዲሁም አውቶብሶችም በእሳት እንዲቀጣጠሉ አድርገዋል።

የአውቶብስ ትራንስፖርት ለከተማዋ የሚያቀርበው ትራንስሊንክ የተባለው ኩባንያ በአውቶብሶቹ ላይ የደረሰውን ውድመት አውግዞ አገልግሎት መስጠቱን አቋርጧል።

ማክሰኞ ምሽት ፍትሕ ሚኒስትሯ ናኦሚ ሎንግ በሰሜናዊ አየርላንድ "ጭምብል ላጠለቁ ወንበዴዎች" ቦታ የለንም ሲሉ ተናግረዋል።

"በሰሜን ቤልፋስት የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ያላችሁን ስጋት ብረዳም ለማሸነፍ ጥላቻ አይፈቀድም" ሲሉ አክለዋል።

የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ ምክትል አዛዥ የሆኑት ኮንስታብል ራየን ሃንደርን "ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረግ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ድምጽ መሆንን መደገፍ ይገባል፤ ነገር ግን አመጽን እና አለመረጋጋት ላይ መሳተፍን ማበረታታት የለብንም" ብለዋል።

የሰሜን አየርላንድ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ማክሰኞ ምሽት ብቻ 62 የአደጋ ጥሪዎች መቀበሉን እና ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል።

የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ጆን ቦቸር በሚቀጥሉት ቀናት በመንገዶች ላይ የሚሰማራው የፖሊስ ቁጥር እንደሚጨምር ተናግረዋል።

በሌላ አካባቢ የፖሊስ ላንድሮቨር እንዲሁም በክሩምሊን ጎዳና ላይ ቤቶች እና መኪኖች ተቃጥለዋል።

ማክሰኞ ዕለት የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ ጥቃቱን በሚመለከት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መሠረት ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ ሶማሊያዊ ነው ተብሎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ሱዳናዊ መሆኑ ተረጋግጧል።

ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ ቢላዋ መገኘቱም ይፋ ተደርጓል።

የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቢሮ ጥቃቱን መፈጸሙ የተጠረጠረው ግለሰብ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እስከ 2028 ድረስ መቆየት የሚያስችለው ፈቃድ አለው ብሏል።

ወደ ዩናየትድ ኪንግደም የገባው በ2023 ሲሆን፣ በዚያው ዓመት የስደተኝነት መታወቂያ ተሰጥቶታል።

የቢሮው ቃል አቀባይ "ግለሰቡ በተለመደው የጉዞ መንገድ ወደ አገሪቱ መግባቱን ነው የገለጸው" ብለዋል።

የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ አዛዥ ተጠርጣሪው መጀመሪያ ከሱዳን ወደ ፓሪስ ከዚያም ወደ ደብሊን በመብረር ወደ ቤልፋስት በአውቶቡስ በየካቲት 2023 መጥቷል ብለዋል።

በዚያው ቀን የጥገኝነት ጥያቄ አቅርቧል ሲሉም ተናግረው፤ ከዚህ በፊት ፖሊስ ክትትል ያደርግበት ያልነበረ መሆኑን እና በምንም ዓይነት ወንጀል ተጠርጥሮ ወይንም ተፈልጎ እነደማያውቅ ተናግረዋል።