በእስራኤል ሠፋሪዎች በተከበበ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ተነገራቸው

የእስራኤል ወታደሮች የእርምጃው ዓላማ ነዋሪዎችን ለመጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ወታደሮች የእርምጃው ዓላማ ነዋሪዎችን ለመጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የፍልስጤም ቤተሰቦች፣ እስራኤላውያን ሠፋሪዎችን ለማስወጣት በተደረገ ዘመቻ ወቅት ንብረቶቻቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ታዘዙ።

ሠፋሪዎቹ ከእሁድ ጀምሮ በመንደሩ ባሉ ሦስት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን የከበቡ ሲሆን የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦታቸውንም አቋርጠው ነበር።

የቁስራ ከንቲባ አብዱል አዚም ዋዲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መንደራቸው ዝግ ወታደራዊ ቀጠና ተብሎ ታውጇል፤ የእስራኤል ኃይሎችም አንዳንዶቹን የተለቀቁትን የፍልስጤም ቤቶች እንደ ወታደራዊ ሰፈራ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። የእስራኤል ወታደሮች ዓላማው "ነዋሪዎችን መጠበቅ" ነው ብለዋል።

አንድ የእስራኤል ቃል አቀባይ የሠፋሪዎቹ እርምጃ "አስጸያፊ" እና "ተቀባይነት የሌለው" መሆኑን ገልጸው መንግሥት ምርመራ እንደሚያደርግ እና ድርጊቱን የፈፀሙትን በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላያ ባለው የእስራኤል መንግሥት ስር የሰፈራ አካባቢዎች በፍጥነት መስፋፋታቸው ሠፋሪዎችን አደፋፍረዋቸዋል። ይህም ሠፋሪዎች ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው ለማባረር በሚያደርጉት ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሁሉም ሰፈራዎች ሕገወጥ ናቸው።

በቁስራ ከሚገኙት በሠፋሪዎች ከተከበቡ ቤቶች ውስጥ የአቡ ሪዲ እና የሃሰን ቤተሰቦች ባለቤትነት የተያዙ ሦስት ቤቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም በሁለቱ ቤቶች ያሉ ነዋሪዎች ሐሙስ ዕለት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል። ልቀቁ የተባሉት ነዋሪዎች ወደ ሦስተኛው ቤት መዛወራቸውንም ገልፀዋል።

በዚያው መንደር በሚገኝ ሌላ አካባቢ በ11 ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ 11 ቤተሰቦችም ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ በወታደሮች ተነግሯቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሀሙስ ዕለት ከቁስራ የተጋሩ ቪዲዮዎች ቡልዶዘርን ጨምሮ 12 የእስራኤል ደኅንነት ተሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱ ያሳያሉ።

በቀን የተቀረጸ አንድ ቪዲዮ፣ በረዥም ሰልፍ ወደ መንደሩ የሚጓዙ የእስራኤል የደኅንነት ኃይሎችን ያሳያል።

የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) "ሁለት ሕገወጥ መንደሮችን እንዳፈረሰ" ተናግሯል።

በናብሉስ አቅራቢያ በሚገኘው የቁስራ እና የጃሉድ አካባቢዎች ዳርቻ ላይ አንድ እስራኤላዊን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንደወሰደበትም አክሏል።

ከቤታቸው እንዲወጡ ከተጠየቁት መካከል አንዱ ቃሄር ኦዴህ ሲሆን ሐሙስ ጠዋት ከ20 በላይ ወታደሮች ወደ ቤቱ እንደገቡ ተናግሯል።

"እኔና ወንድሜ ጠዋት ተኝተን ነበር። ክፈቱ፣ በሩን ክፈቱ እያሉ ሰብረው ገቡ። አሁንም ከፊት ለፊቴ ሲሆን ያየሁትን ማመን አልችልም። ከ20 በላይ ነበሩ፣ ምናልባትም 30 ይሆናሉ" ብሏል።

"ወጥተን ወደ ሰፈሩ የታችኛው ክፍል መራመድ ቀጠልን። ብዙም ሳይቆይ አካባቢውን በሙሉ ዘግተውታል። ብዙ ሰዎች ከቤታቸው እየተፈናቀሉ ነበር" ሲል ኦዴህ አክሏል።

ከ10 ሰዓታት ገደማ በኋላ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የተፈቀደላቸው አንዳንድ ቤተሰቦች ቤታቸውን ተዘበራርቆ ነበር ያገኙት። ወታደሮቹ ምግቡን በሙሉ ከማቀዝቀዣው ውስጥ አውጥተው 1,500 ዶላር በጥሬ ገንዘብ እንደወሰዱ አንድ ግለሰብ ተናግሯል።

በቢቢሲ ጥያቄ የቀረበለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ለዚህ ክስ ምላሽ አልሰጠም።

ሆኖም፣ የቁስራ ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ለወታደሮቹ መመሪያ እንደተሰጣቸው ሠራዊቱ ገልጿል። ወታደሮች በሠፋሪዎች በተከበቡ የፍልስጤም ቤቶች ውስጥ እንቅስቃሴ እንደማያደርጉም አክሏል።

የእስራኤል "የግንኙነት መኮንኖች ከቁስራ የአካባቢ አመራር ጋር ቀጣይነት ያለው ግንኙነት እያደረጉ መሆኑን እና በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ችግር እንዳይፈጠር እየሰሩ መሆናቸውን" በአፅንዖት ገልጿል።

ከተያዙት የፍልስጤም ቤተሰብ አባላት አንዱ የሆነው ኩሳይ አቡ ሪዲ ለቢቢሲ እንደተናገረው ቤቱ በአንድ ሌሊት እንደገና ጥቃት እንደደረሰበት እና ጥቂት ሠፋሪዎች ከጦሩ እየተደበቁ በአካባቢው እንደቀሩ ተናግረዋል።

በቁስራ የነበረው ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው እሁድ ዕለት ሠፋሪዎች ወደ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት የኃይል እና የውሃ አቅርቦታቸውን ከዘጉ በኋላ ነው። ወደ ቦታው የመጡት የመጀመሪያዎቹ የእስራኤል ወታደሮች ከሰፋሪዎቹ ጋር ፀሎት ያካሔዱ ሲሆን በዚህ የተነሳ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የእስራኤል ጦር በኋላ ላይ አስታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሃዝ መሠረት፣ 18 ሕጻናትን ጨምሮ 76 ፍልስጤማውያን በዚህ ዓመት በዌስት ባንክ በእስራኤል ኃይሎች ወይም በሠፋሪዎች ተገድለዋል። በተመሳሳይ ጊዜ፣ አንድ ሲቪልን ጨምሮ ሦስት እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር በተፈጠረው ግጭት እና በዌስት ባንክ በፍልስጤማውያን በተፈፀመ ጥቃት ተገድለዋል።

እአአ ከ2023 ጀምሮ፣ በዌስት ባንክ ውስጥ 127 የፍልስጤም ማኅበረሰቦች መፈናቀላቸውን የመንግሥታት ድርጅት ገልጿል፤ ከእነዚህም ውስጥ 47ቱ ሙሉ በሙሉ የተፈናቀሉ ናቸው። በዚህም ባጠቃላይ ከ6,390 በላይ ፍልስጤማውያን ተጎድተዋል።

በ2026፣ ወደ 3,800 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን፣ በሠፋሪዎች ጥቃት፣ ቤታቸው በመፍረሱ እና በግዳጅ ተፈናቅለዋል። ከእነዚህም ግማሹ ሕጻናት ናቸው።

በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን በድርጅቱ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሠፈራዎች ለሰላም እንቅፋት ናቸው መባሉን ውድቅ አድርገዋል። አገራቸው የመሬቱ ባለቤት ለመሆኗ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቶች ስላሏት፣ እነዚህ ሰፈራዎች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት "አንድ ቀላል እውነታን መረዳት አለበት፡ ወደ የትኛውም አንሄድም" ብለዋል።